2013 ጁላይ 24, ረቡዕ

የኔዋ ምርጥ ቮልስ /ዩሴን ቦልት/ በ-ኄኖክ ስጦታው


ከዚህ ቀደም በዚህቹ ጉደኛ ቮልስ መኪናዬ ዙሪያ በጥቂቱ አውርቼላችሁ ነበር፡፡፡ እስቲ ዛሬ ደግሞ ጥቂት ትውስታዎቼን ላካፍላችሁ፡፡

ያው መቼስ የቮልስ ባሉካ የሆንኩ ሰሞን የወረት ነገር በጥቂቱም ቢሆን ደባብሶኝ ነበር፡፡ መኪናዋን ማሽከርከር እንደጀመርኩ ወዳጅ ዘመዶቼን ሁሉ በመኪናዋ መስኮት ነበር ሰላም የምለው፡፡ መሬት የምረግጠው ከቤት ስወጣና እቤት ስገባ ነው፡፡ ቁርስ፣ ምሳ ፣እራት የምመገበው እዚህቹ መኪና ውስጥ ነበር፡፡ ጥቂት ጓደኞቼ በጣም ስናፍቃቸው ይደውሉና “ኧረ በጣም ናፍቀኸናል፤ መቼ ነው በአካል የምናገኝህ?” ይሉ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በአካል እንደማያገኙኝ ቁርጡን ሲያውቁ ይህን ውሳኔ አስተላለፉ፡፡“በተገኘበት ቦታ ከመኪናው ላይ ተጎትቶ እንዲወርድ!!!” 

ደግነቱ እነሱ ጎትተው እኔን ከማውረዳቸው በፊት የፍሪሲዮን ካቦ ተበጠሰና ቮልሴን እያስጎተትኩ ጋራጅ ገባሁ፡፡ ያኔ በአካል ጋራጅ ድረስ መጥተው አገኙኝ፡፡ መኪናዋ ተሰርታ እስክታልቅ ድረስ ከጋራጅ አልወጣም ብዬ ነበር፡፡ ሜካኒኩ “ሲያልቅ እንጠራሀለን፡፡ በቃ፣ ሂድ” በማለቱና በእነሱ ጉትጎታ እጅግ አዝኜ ወጣሁ፡፡ መኪናዬ ተጠግና ስትወጣ በድጋሚ ጠፋሁባቸው ፡፡ 

ለቮልሴ የዘመኑን ሲዲ ማጫወቻ ያስገጠምኩላት ሰሞን ጓደኞቼ ብቻ ሳይሆኑ አገርም “ጉድ!” አለ፡፡ ጥቂቶች “ለቮልሱ ሲዲ ማጫወቻ ገጠመለት” አሉ፡፡ ብዙዎቹ ደግሞ “ለሲዲ ማጫወቻው ቮልስ ገጠመለት፡፡”

ከሁሉም የሚገርመኝ አንድ ሰሞን ወንድሜ ይነዳት ነበር፡፡ ከግቢ ውስጥ አውጥቶ መቶ ሜትር ያህል ያሽከረክርና የዋናው አስፓልት መንገድ ላይ አቁሞ በታክሲ ይንቀሳቀስ በነበረበት ሰሞን ይህቺው ቮልስ ቅፅል ስም ወጥቶላት ጠበቀኝ፡፡ እሱንም የነገረኝ ወንደሜ ነው፡፡ 

“እንዴት ናት ቮልሴ?” ብዬ ስጠይቀው፡-
“ምን እዚህ ሰፈር መች ያስነዱና!?? ቁጭ ብለው ቅፅል ስም መስጠት ነው ስራቸው፡፡ መኪናዋን ማን እንዳሏት አልሰማህም!? ” 
“ማን አሏት!?”
“ዩሴን ቦልት” 
እንደዚህ ጊዜ ስቄ አላውቅም፡፡ ወንድሜ መቶ ሜትር እየነዳ በመቶ ሜትር ጃማይካዊ ሯጭ ስም አስጠርቶልኝ አረፈው፡፡  

ይችው መኪና አንድ ከባድ ችግር አለባት፡፡ ጭንቀት አትችልም፡፡ ልብ ድካም ያለባት ይመስለኛል፡፡ በቃ፣ የተጨናነቀ አደባባይ መሀል ገባታ ቀጥ ነው! ጭንቀቷ ሌሎችን መኪና ይበልጥ እስኪያጨናንቅ ድረስ የአደባባዩን ውጥረቱን ታንረዋለች፡፡ እንደዚህ ሲሆን ከሶስት ያላነሱ ትራፊኮች ወደኔ ይመጣሉ፡፡ ያው ከቆመች መምጣታቸው እንደማይቀር ስለማውቅ የሞተር ቀሚሷን/ኮፈኗን/ ከፍቼ “ፖምፔታዋን/ ፊውል ፓምፕ” በውሃ እያቀዘቀዝኩ እጠብቃቸዋለሁ፡፡

“ከሥራ ክፉ ኩርኩር ግፉ” እንዲሉ . . . በጣም ጥቂት ሰው በቀር “መሀል አደባባይ ላይ ቮልስ ብንገፋ ስማችን ይጠፋል” ብለው ስለሚያስቡ ትራፊክ ፖሊስ እስኪመጣ ድረስ ከመጠበቅ በቀር አማራጭ እንደሌለኝ በሹፍርና አጭር ዘመኔ የቀሰምኩት ጥበብ ነው፡፡ ቮልስ ለመግፋት ዝንባሌ ያላቸው ጥቂቶቹም ቢሆኑ ከገፉ በኋላ እጃቸውን ዘርግተው በተራዬ ብር ወደነሱ እንድገፋ ስለሚጠይቁ አይመቹኝም፡፡ትራፊኮቹ ግን ገንዘብ የሚጠይቁኝ ሞተር ሲጠፋ ሳይሆን እኔ ሳጠፋ ነው፡፡ ከእነሱ ብዙዎቹ፣ “የቮልስ ሹፌር የሆነው በጣም ቢቸግረው ነው” ብለው ስለሚያስቡ መክረው የሚለቁ ናቸው፡፡ /አቦ መካሪ ትራፊክ አትጡማ/

እንደምንም ከተጨናነቀው መንገድ በተራፊክ እያስገፋሁ ልክ ነፃ መንገድ ሳገኝ ሞተሩ በራሱ ጊዜ ተረክ ብሎ ይነሳል፡፡  
  
የገዛኋት ሰሞን ባትሪዋ የኋላ መቀመጫ ስር ነበር፡፡ የመቀመጫው ታች ጥምዝምዝ ሽቦዎች አሉ፡፡ ከእነሱ በላይ እንደ እንቅብ የሚመስል የደረቀና የሳር ባህርይ ባለው ግብዓት መቀመጫው ተደልድሎ ጨርቅ ለብሷል፡፡ ይሄ ጥምዝምዝ ሽቦ ከመቀመጥ ብዛት በመላላቱ ሰው ሲቀመጥበት ወደ ባትሪው ወርዶ ከ“ኔጋቲሽ” እና ከ“ፖዘቲቭ” አካሉ ጋር እየተነካካ “ማሳ” (እሳት) ይፈጥራል፡፡ ይህን “ጥበብ” ያወቅኩት በተግባር ነው፡፡ ሁለት ጓደኞቼን . . . አንዱን ከፊት ሌላውን ከኋላ ጭኜ ስዘውር ከኋላ የተቀመጠው ጋደኛዬ በተረብ መልክ እንዲህ አለ፡-

“መቀመጫው በጣም ይሞቃል፡፡ ሃሃሃ . . . "ኤሲ" አስገጠምክለት እንዴ!?”

“ሞተሩ ከኋላ ስለሆነ ሙቀት ወደውስጥ ገብቶ ይሆናል፡፡” አልኩት በባለሙያ አገላለፅ ልበ ሙሉ ሆኜ፡፡

“አይመስለኝም” አለ እየትቁነጠነጠ፡፡ “ወደዳር አድርገውና እንየው፡፡ መቀመጥ አልቻልኩም . . .” እያለ ሳለ መኪናዋ ጨሰች፡፡ የኋላ በር እንኳን አልኖራት፡፡ ተፈጥፍጦ አንድ ነገር ይሆን ነበር ፡፡ድንጋጤ አስፈንጥሮ እላያችን ላይ ጣለው፡፡ እንዴት እንዳቆምን ትዝ አይለኝም፡፡ ጥቂት ሮጥ ሮጥ ብለንም ነበር፡፡ የሆኑ ሰዎች ለዚሁ ጉዳይ ያጠራቀሙት የሚመስል እጅግ የቆሸሸ ውሃ እያመጡ ወደውስጥ ይረጩ ጀመር፡፡ ብቻ እሳቱ "ወደሌሎች" ሳይዛመድ በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡ 

ታዲያ ያኔ (መኪናዋ እየተቃጠለች ሳለ) እኔ ባልለውም ዛሬ ድረስ እንዲህ ብሎ ነበር ይባላል፡፡ ውሃ እየደፉ እሳቱን ሊያጠፉ የሚረባረቡትን ሰዎች፡-

“ተውዋት! ትቃጠል! እኔንም እንዲህ ነበር ያቃጠለችኝ!!!”

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ