ረቡዕ 30 ኦክቶበር 2013

የቆሻሻ ወደብ ______(ኄኖክ ሥጦታው)

የቆሻሻ ወደብ
______(ኄኖክ ሥጦታው)

የስልጣኔ ዝቅጥ መጣያ፣ የጥራጊያቸው ወደብ ነን፤
የጣሉትን የምንለቅም፣ ካልጣሉልን የምንለምን፤
ፈረስም ነን ለነዚሁ፣ እንዳሻቸው የሚያደርጉን፤
ካሻቸው የሚለጉሙ፣ ካሻቸውም የሚጋልቡን፤
ካሻቸው የሚጭኑ፤ ካሻቸውም የሚዋጉብን፡፡

የገደልም ማሚቶዎች ነን፤ የጮኹትን የምንደግም፤
በለኮሱት ስንቃጠል፤ በቃ ሲሉን የምንከስም!

በስማ በለው ተብትበውን፣በቁሳቸውእንዳጨቁን፣
ስንዳክር ዳናው ጠፍቶን፣ እስከ መቼ እንዘልቃለን!?

ሲጋልቡን ስንጋለብ፣ የጫኑንን ስንሸከም፤
የጣሉትን ስንለቅም፣ የሚሉትን ስንደግም!
እንደ አራስ ልጅ በሰው ጀርባ
እስከ መቼስ እንዘልቃለን!?
እስከ መቼስ እንከርማለን!?
______________
መስከረም 2005.

ኄኖክ ሥጦታው - "-ሞት" የግጥም መጽሐፍ

ዓርብ 25 ኦክቶበር 2013

በእጅ ያልተቀረፀው የአበበ ቢቂላ ሐውልት - በግሱ - ከሀገረ-እንግሊዝ

በእጅ  ያልተቀረፀው የአበበ ቢቂላ ሐውልት




PDF


ልክ የዛሬ አርባ ዓመት፣ ከማራቶኑ አምበል ሻምበል አበበ ቢቂላ ቀብር መልስ፤ ኢትዮጵያዊው ባለቅኔ ጸጋዬ ገብረመድህን "አበበ እንጂ መቼ ሞተ!!" ሲል የፃፈው ሥነግጥም  እንዲህ ብሎ ይጀምራል፣ እንዲህ እያለ በዜማ ይፈሳል

በቅፅበት ፀንሶ ሞቱን
ድፍን አለም ደፍቶ አንገቱን                              
በልቡ ቀርፆት ፀሎቱን
በህሊናው ነድፎት ስሙን
በገፁ ፅላት ታሪኩን፡፡
አእዋፍን በደመና፣ ጀግናን በምድር ያስደነቀ
ማራቶን ጮራው ጠለቀ
                          በራሪው ኮከብ ወደቀ፡፡
በቃ ጀግናው ተከተተ
ይኸው የማይሞት ሰው ሞተ
ብለን አንበል እባካችሁ፤
 አበበ ተስፋ ነውና
ተስፋ አይቀበርምና፡፡

“ከእንጨት መርጦ ለታቦት፣ ከቃል መርጦ ለኪነት” እንዲል ስመጥሩ ብዕረኛ ዮሐንስ አድማሱ፤  በቅፅበት ፀንሶ ሞቱን የሚሉት የግጥሙ የመክፈቻ ቃላት የዚያን ታላቅ ሯጭ ህይወት በምልዐት ለመወከል የሚችል ጉልበት አላቸው፡፡  ቅፅበት ማለት ፍጥነት ነውና፤ አቤም ክብረወሰን ሰባሪ ፈጣን  አትሌት ነበረና። በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ሩጫው ሁሉ ህይወቱም ቅፅበታዊ ነበረች፤ ብልጭ ብላ ድርግም ያለች። በራሪ ኮኮብ ነበረና፡፡ በነሐሴ 30 ቀን 1925 ዓ.ም በጃቶ ቀበሌ (ደብረብርሃን አውራጃ) እትብቱ ተቀብሮ፤ ጥቅምት 15 ቀን 1966 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ የመጨረሻ ትንፋሹን ሲጨልጥ፤ ገና አርባ አንድ አመቱ ነበር፡፡ ከአራት አመታት በላይ አሰቃይቶ ወደሞቱ የወሰደው ጎዳና አሁንም የፍጥነት ነገር አለበት -የቅፅበት! ሰሎሞን ተሠማ ጂ እንደሚከተለው ይተርከዋል፤

 “መጋቢት 14 ቀን 1961 ዓ.ም ቀትር ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አምስት ኪሎ ካምፓስ የአሁኖቹ የተማሪዎች መኖረያ ሕንፃዎች የተሠሩበት ቦታ ላይ መሠረት ለመጣል ጉድጓድ ተቆፍሮ ነበር፡፡ ሦስት የፖሊስ ባልደረቦችን ተኩስና ዱላ የሚሸሹ ተማሪዎች እየሮጡ የአበበ ቮልስ ላይ ሊወጡባት ተጠጓት፡፡ አበበ በፍጥነት መሪውን ጠመዘዘ፡፡ ሆኖም በስተቀኙ በኩል የነበረውን ለግንባታ የተቆፈረ ጉድጓድ አላስተዋለውም ነበር፡፡ ነገሮች በፍጥነት ተከሰቱ፡፡….. የአበበ አከርካሪ አጥንት (Spinal Cord) ተቀጨ፡፡”

ህይወትን በቅፅበት፤ በቅፅበትም ወደሞት፡፡ በቅፅበት ፀንሶ ሞቱን ማለት ይኼው ነው፤ በህይወት እና በሞት መካካል ልዩነት የሌለ እስኪመስል ድረስ። ታላቁ ከያኒ ገብረክርስቶስ ደስታ በስንኝ እንደተፈላሰፈው

በመኖር በመሞት
ልዩነት የሌለው
ቢኖርም ልዩነት
ከነፋስ ከውሃ መልኩ የቀጠነ
አይን የማይጨብጥው።
ህይወትን ሲያነቡት ወደግራ ሞት ነው።

በ1952 ዓ.ም የመጨረሻ ቀን የዕንቁጣጣሽ ዋዜማ ዕለት፤ ሮም ላይ በኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ተንቆጥቁጦ፤ ይኼንንም ገድል ከአራት አመት በኋላ ቶኪዮ ላይ በመድገሙ -- ያውም ትርፍ አንጀት ለማስወጣት ቀዶ ጥገና ከአደረገ ስድስት ሳምንታት በኋላ! -- ብቻ አይመስለኝም አእዋፍን በደመና፣ ጀግናን በምድር ያስደነቁ  እግሮቹ በሞት ሲታበቱ፤ “አበበ እንጂ መቼ ሞተ!!” ብለን እንድንል የጸጋዬ ብዕር የሚማፀነው። እርግጥ ነው አበበ አብቧል። ራሱን በእጥፍ ድርብ አባዝቷል። ከምሩፅ ይፍጠር እስከ መሃመድ አማን፤ ከደራርቱ ቱሉ እስከ ጥሩነሽ ዲባባ ድረስ ያሉትን የአገራችንን ውድ ልጆች ስፖርታዊ ድሎች ስንቆጥር፤ የአበበንም  ዘር ፍሬዎች አብረን እንቆጥራለን። ነገር ግን አበበ ቢቂላ ከሜዳሊያ ሠንጠረዥ በላይ ነው፣ በተራ አኃዝ ከቶም የማይለካ። ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው የአበቦችን ውበት ለማድነቅ የተጠቀሙበትን ሐረግ ልዋስና፤ አቤ “ከሥፍር ባሻገር’’ ነው።

ለምን ይሆን ግን አበበ ቢቂላ ምናባችንን ሰቅዞ የመያዝ አቅሙ ዘመን የማያደበዝዘው፣ የጊዜም ሂደት የማያበልዘው? ማራቶን በባዶ እግሩ  ሮጦ ማሸነፉን፥ በባዶ እግራቸው ቆንጥር ለቆንጥር ተፋልመው ነጻነታችንን በደማቸው በዋጁልን አባቶቻችን አምሳል ቀርፀን የጀግንነት ጥንፍ አርገን ማየታችን? ወይንስ ቢኒቶ ሙሶሊኒ ፋሺስታዊ ጦሩን ወደ ኢትዮጵያ በላከባቸው የሮም አደባባዮች፡ ቀጥ እና ኮራ ብሎ በድል አድራጊነት መንፈስ መሮጡን ባሰብን ቁጥር፥ ከቶም ሞቶ የማይሞተውን የአገር ፍቅር ስሜታችንን ማላወሱ? አሊያስ ለጥቁር አፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ፣ በወቅቱ በቅኝ አገዛዝ ቀንበር ሲማቅቁ የነበሩት አፍሪቃውያን ወንድሞቻችንን በ “ይቻላል” ስሜት  አንቅቶ፤ የልባቸውን መቅረዝ በተስፋ ዘይት መሙላቱን ከታሪክ ስላነበብን? ወይስ የአትሌቲስክ ድሎቻችንን ወደሌላ መስክ “መመንዘሩ” አንደማይገደን አልፎ አልፎ የሚታየን ጣፋጭ ራዕይ  ቀዳማዊ ደራሲ ስለሆነ?

“አበበ ተስፋ ነውና” የሚለው የጸጋዬ ሐረግ፤ ወዲ ቢቂላ ሯጭ ብቻ ሳይሆን የዘመኑ መንፈስ (zeitgeist) አብይ አካል እንደነበር ያመለክታል። ከአዝማሪ ቤቱ ሆይሆይታ (“ያገባሻል ያገባሻል፤ አበበ ቢቂላ ያገባሻል፤ጥላሁን ገሠሠ ይድርሻል’’ የሚለውን ህዝባዊ ዘፈን ያስታውሷል) እስከ ለውጥ አራማጅ የተማሪዎች ንቅናቄ ድረስ ያ ብጡል (mighty) አትሌት ስሙን ለድፍን አገር አውሶ ነበር። ለዚህ አባባል ማስረጃ ያህል፤ በኅዳር 1957 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ተማሪዎች ለጀግናው አትሌት የክብር ግብዣ ባደረጉበት ዕለት፤ ትንታጉ ገጣሚ ኃይሉ ገብረዮሐንስ (ገሞራው) ምነው አገራችን እንደአበበ ያሉ በርካታ ሁነኛ ሰዎች በኖራት በሚል የቁጭት መንፈስ “ኧረ የወንድ ያለህ!” ብሎ ካሰማው የብዕር እንጉርጉሮ  በጥቂቱ እንንጠቅ

ለወገኑ እሚቆጭ ሁለተኛ ሙሴ
አንደአበበ ያለ የማይል ለራሴ
ብታገኝ አገሬ ምንኛ ደስ ባላት ውስጣዊቷ ነፍሴ።
…..
እንዳበበ ያለ ጀግናና ጎበዝ ልጅ ቢኖር ኖሮ ለሀገር
የጎሳ ልዩነት መች ያናጥር ነበር?
የተዋረድ ኑሮስ መች ይሰፍን ነበር?
እውነትን ውሸት መች ያደባይ ነበር?
ፉራፉሬስ ሆነን መች እንዞር ነበር?

በየካቲት 1999 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ ቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ለአበበ ቢቂላ እና ለማሞ ወልዴ መታሰቢያ የቆሙት ሐውልቶች ባልታወቁ ወንጀለኞች እጅ መፍረሱ አስደንጋጭ እና አሳዛኝ ዜና ሆኖ ነበር። ቢሆንም የአበበ ቢቂላ ገድል “ከሥፍር ባሻገር’’ ነውና፤ እልፍ አዕላፍ ዜጎች በእጅ ያልተቀረፁ በጊዜም ሆነ በውለታ ቢስ ወገን መዶሻ የማይናዱ ቋሚ ሐውልቶች በልባቸው ፅላት አኑረውለታል፡፡ ሩሲያዊው ገጣሚ አሌክሳንደር ፑሽኪን ለነገስታት እና ለምድር ኃያላን  ማስታወሻ ከቆሙት ግዙፍ ሐውልቶች ይልቅ፤ ለሰው ልጆች ነፃነት ወግኖ የጻፋቸው ግጥሞቹ በእጅ ያልተሰራና ከቶም የማይፈርስ ሐውልት ሆነው ዘመንን ተሻግረው እንደሚዘልቁ  የተነበየውን፤ አያልነህ ሙላቱ እንደዚህ አርጎ ወደ አማርኛ መልሶታል

ግርማ ሞገስ ያለው እጅግ የሚያኮራ
በእጅ ያልተቀረፀ በሰው ያልተሰራ
ሐውልት አቁሜያለሁ ለመታሰቢያዬ
ለሚመጣው ትውልድ ለወደ ኋላዬ።

ለአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ከቆሙ በእጅ ያልተቀረፁ ሐውልቶች መካከል፣ የጸጋዬ ገብረመድህን “አበበ እንጂ መቼ ሞተ!” ሥነግጥም እጅግ ውቡ እና ጠንካራው ይመስለኛል።

                          የጎበዝ ነባቢት ነፍሱ
የሰው መዝርዕቱ አርአያ፤ የማይታጠፍ መንፈሱ
በጥራት የታጠፈለት፤ የምድር አጥናፍና አድማሱ
የየብስ የአየሩ ነበልባል
የማራቶን እፁብ አይጣል
የምድር አለሙ ገሞራ
አገሩን በክብር ያስጠራ
ሳተናው እግረ ጆቢራ
ሎጋ ቢቂላ ዋቅጂራ፤
የጎበዛዝ ንጥረ ወዙ
የተስፋ ብርሃን መቅረዙ።
ስሙን ላገር ስም ሰይሞ፤ የምስራች ያስደወለ
ስንቱን ስንቱን ልበ ሙሉ፤ ከአድማስ አድማስ ያስከተለ፡፡
የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ
ያረጋት የኦሎምፒክ አርማ
በወገኖቹ ልቦና፤ ቀና ኩራት ያሳደረ
እንደፍላፃ በአክናፉ፤ የአየርን ሰርጥ የሰበረ
የፍስሃዋን አዋጅ ለአለም፤ በአቅመ ወዙ ያስነገረ
በአገር ፍቅር ልቡን ሞልቶ፤ ላቡን ነጥቦ የዋተተ
የአለምን ጀግና በአድናቆት፤ በቅን ቅናት ያስሸፈተ
አልሞተም እንበል እባካችሁ፤ “አበበ እንጂ መቼ ሞተ!”        
            
ግሱ
ጥቅምት፤ 2006 ዓ.ም
ሀገረ-እንግሊዝ

(የወደር የለሹን አትሌት አርባኛ የሙት ዓመት፣  በባዶ እጅ ላለማዘከር የተደረገ ግለሰባዊ መፍጨርጨር)

ሐሙስ 24 ኦክቶበር 2013

አሸባሪው ማነው? --በኄኖክ ስጦታው

አሸባሪው ማነው?

በቀይዋ ብዕሬ፣ የከተብኩት ሁሉ፤
አንዴ ከኔ ወጥቷል፣ እስቲ ተቀበሉ።

እውነትን ሊናገር፣ አፉን የከፈተ፤
ንቅዘቶችን ነቅሶ፣ ድክመትን ያተተ፤
በዚህች ጉስቁል አገር፣ ምሣር በበዛባት፤
በሚቀጥለው ቀን፣ ለርሱ ወየውለት!!

ለምን!?
ፈራጅ ነው ዘራፊ፤ ተዘራፊው ሌባ
ትችት ያሳስራል፤ በማሸበር ደባ

የታል!?
"ነፃ አውጪው" የታል!?
ሆኗል ጨቋኝ መሪ
"ለምን" ባዩን ፈራጅ፤ "በሽብር ፈጣሪ"
ደፍሮ የሚናገር፣ ዘብጥያ ታሣሪ።

ማነው!?
ፀረ—ሠላም ማነው!? ማነውስ ነፃ አውጪ!?
አሸባሪ ማነው!? ማንኛው ነው ቀጪ!?
ወንጀለኛው ማነው!? ማነውስ ታሳሪ!?
ፀረ—ሠላም ከሣሽ፣ እራሱ መስካሪ፤
"ለምን" ባይ ተከሣሽ፣ ላገር ተቆርቋሪ!!

2004 ዓ. ም.


(ከ "ሀ-ሞት" የግጥም መጽሐፍ/ በኄኖክ ስጦታው)

ተጠየቁ ዳኞች! ~በ ኄኖክ ስጦታው —

ተጠየቁ ዳኞች!
  
~በ ኄኖክ ስጦታው —

ችሎት እንዴት ዋለ?!
          ማን ተፈረደበት?!
          ማንስ ተቀጠረ?!
ይህ ሁሉ እስረኛ ወኅኒ የታጎረ
በፍርዱ ረካ?! ወይስ ተማረረ?!
ተጠየቁ ዳኞች! መልሱልኝ እውነት….
የነገር ግራ ቀኝ፣ የምትመረምሩት
ግዜው ምን ያህል ነው?! ቀናት ወይስ ሳምንት?!
ዓመት ሁለት አመት?!
ሰምታችሁ ምትፈርዱት?!
ይግባኝ!
ይግባኝ!
ይግባኝ!
ይግባኝ ደረጃ አንድ፣ ይግባኝ ከፍተኛ
ይግባኝ ዐቃቤ ሕግ፣ ይግባኝ ሰሚ ዳኛ!
ተጠየቁ ዛሬ፣ መልሱልኝ እውነት
ግዜ አላችሁ ወይ ሰምታችሁ ለመፍረድ?!
ምን ያህሉ ሰው ነው ወኅኒ የተጣለ?!
ሰሚ ጆሮ አጥቶ ፍትህ ያልታደለ፡፡
ባላጠፋው ጥፋት በሀሰት ውንጀላ
ክርክር ረትቶት የአግቦ ፍተላ
“ይግባኝ!” ብሎ ሲጮኽ፣ “ልስማኽ” የማይሰኝ
ምን ያህል ነፍስ ነው፣ ወኅኒ ውስጥ የሚገኝ?!
ይግባኝ!
ይግባኝ!
ይግባኝ!
ይግባኝ ደረጃ አንድ፣ ይግባኝ ከፍተኛ
ይግባኝ ዐቃቤ ሕግ፣ ይግባኝ ሰሚ ዳኛ!
  
“ሀ -ሞት”  የግጥም መጽሐፍ
 ኄኖክ ስጦታው —


ረቡዕ 16 ኦክቶበር 2013

ትዝታ ዘ-ገብረ ክርስቶስ ደስታ ፡ ገጣሚ - ሰዓሊ? ወይስ ሰዓሊ - ገጣሚ? - በዶክተር ፍቃደ አዘዘ


ይህ ጽሑፍ በመጠኑም ቢሆን ስለገብረ ክርስቶስ ደስታ ማንነት የሚያትት ሆኖ ስላገኘሁት የዶክተር ፍቃደ አዘዘን ንግግር በፎቶ መልክ ገጼ ላይ ለጥፌዋለሁ፡፡ርግጥ ውይይቱ የተካሄደው የዛሬ አስር ዓመት ገደማ ቢሆንም ቅሉ ፣ ካለው ኪነጥበባዊ ፋይዳ አንጻር ለአጥኚዎች እንደ አንድ ግብዓት ማገልገሉ እሙን ነው፡፡ ውድ የእልፍኜ ታዳሚያን ፣ በገጣሚና ሰዓሊ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ሥራዎች እና የሕይወት ጉዞ ላይ ተጨማሪ መረጃ ካላችሁ በኢሜል አድራሻዬ ትልኩልኝ ዘንድ መልካም ፍቃዳችሁን እለምናለሁ፡፡

[PDF]

 






ዓርብ 20 ሴፕቴምበር 2013

አላዋቂ ሳሚ . . . .! በ-ኄኖክ ስጦታው



የዚህ ጽሑፍ መነሻ ጳጉሜ 3 ቀን 2005ዓ.ም በዋልታ ኢንፎርሜሽን ድረ ገጽ ላይ “ሥነ-ጽሑፍ እና ትምክህተኝነት” በሚል ርዕር፣ “ቢላል” በሚል ብዕር ስም (ኋላ ላይ ማንነቱን የሚገልፅ ፍንጭ በመስጠት ማንነቱን የደረስኩበት ጸሐፊ) አማካኝነት የቀረበ ጅምላ ጨራሽ ዳሰሳ ነው፡፡

ርግጡን ለመናገር “ሥነ-ጽሑፍ እና ትምክህተኝነት” በተሰኘው ርዕስ ሥር ያለውን ጭብጥ ለመረዳት ጽሑፉን ደጋግሜ አንብቤዋለሁ፡፡ በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ድረ-ገጽ ላይ መውጣቱ ትኩረቴን ባይስበው ኖሮ ተራ የስም ማጥፋት ድርጊት ነው ብዬ ባለፍኩት፡፡ እንዲህም የተቆርቋሪነት ስሜቴን ባላንጸባረቅኩ፡፡ ሆኖም እንዳሰብኩት አልሆነም፡፡ እናም ለውይይት ይሆን ዘንድ በር ከፈትኩ፡፡

ርግጥ ነው ጽሁፉ “ሥነ-ጽሑፍ እና ትምክህተኝነት” ርዕሱ ነው፡፡ አላማው እና ጭብጡ ግን ከሥነ-ጽሑፍም ባሻገር የጸሐፊውን ትምክህት በግልፅ የሚያሳይ፡፡ ሙሉ ሀተታውን በዚህ አድራሻ ያገኙታል፡- http://www.waltainfo.com/index.php/2011-09-07-11-57-06/10279-2013-09-08-20-31-21

ሀተታውን በማነብበት ሰዓት የተሰማኝን በመግለጽ ወደዋናው ጉዳይ ልግባ፡፡

ተጀመረ!

ከርዕሱ እንደምንረዳው “ሥነ-ጽሑፍ እና ትምክህተኝነት” ደፋር ርዕስ ነው፡፡ ምን ለማለት ነው እንዲህ አይነት ርዕስ የመረጠው?? በሚል ውስጣዊ ውዝግብ ፈጥሮ የመነበብን ጉልበት ይፈጥራል፡፡ “ሥነ-ጽሑፍ እንዴት ትምክህተኛ ይሆናል?? ትምክህተኛ እንዲሆንስ ማነው የሾመው?? ሥነ-ጽሑፍ የጽሑፍ ውበት ሆኖ ሳለስ እንዴት በትምክተኝነት ይፈረጃል??” በሚሉ መሰረታዊ ጥያቄዎች እየተናጥኩ አነበብኩት፡፡ በመጀመሪያው ንባቤ ርዕሱና ጭብጡ ተጣረሱብኝ፡፡


ጉድ እኮ ነው፡፡ “አንድ ሰው የተወሰኑ ጸሐፍትን ለመተንኮስ እንዴት ዙሪያ ጥምጥም ይጋልባል??” ብዬ ራሴን ጠየቅኩ፡፡ ለጥቆም፣ “ከተወሰኑ ጸሐፍት ባሻገር አገራዊ አጀንዳ ማንሳቱ ካልቀረ እንደምንስ ጭፍን ግንዛቤውን ልብ በሚደልቅ ርዕስ ይጀምራል??” የሚል አንፃራዊ ጥያቄ ወጥሮ ያዘኝ፡፡ ጉዳዩን ለመረዳት ለሶስተኛ ጊዜ አነበብኩት፡፡ ይህኔ ግን የተረዳሁት ይህን ነው፡፡ “እንዴት እራሱን “ዋልታ” ነኝ ምሎ የሰየመ የመረጃ ማዕከል እንዲህ ያለ ተልካሻ የስም ማጥፋት ዘመቻ በድረ-ገፁ ላይ ,ሊያስነብበን ፈለገ??” ወደሚል ጥያቄ ተሸጋገርኩ፡፡

መልስ ምት!!

የጽሑፉ ጭብጥ የማይነካካው ነገር የለም፡፡ ዓለም ስትፈጠር ጀምሮ የነበረውን የሥነ-ጽሑፍ ሂደት አሻሚ በሆነና በደፍናናው ሊነግረን ይሞክርና (መነሻውን አታውቅም ፣ አርፈህ ተቀመጥ እንዳንለው ነው መሰል¡) ነፃው ፕሬስ ፖለቲካዊ ተፅዕኖው ከአፍራሽ ፓርቲዎች ግፊት የመነጨ ነው ከማለት አንስቶ የግለሰቦችን ስም እየጠቀሰ “እከሌ ፀረ-ኢህአዴግ ነው፣ እከሌም ጨለምተኛ ነው ፣ እንቶኔ የቅንጅት ቅብርጥሶ ነው ፣ እከሌም የደርግ ወታደር ነበር . . .” የሚሉ ተልካሻ ሃሳቦችን አስደግፎ ከዓለም ዓቀፋዊ አጀንዳ ወደ አገራዊ አጀንዳ ፤ ከአገራዊ አጀንዳ ወደ ፖለቲካዊ አጀንዳ ፤ ከፖለቲካዊ አጀንዳ ወደ ግለ-ሰብዓዊ አጀንዳ፤ ከግለ-ሰብዓዊ አጀንዳ ወደ ግል ብሶት ይሸጋገርን እንዲያ ቀልባችንን የሳበውን ርዕስ የብሶት መወጫ ያደርገዋል፡፡

ከመጨረሻው ልጀምር!

ይህን ጭብጥ በ“የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ላይ የተቃጣ ጦር” ብዬ ሰይሜዋለሁ፡፡ የዚህ ጽሑፍ አጠናቃሪ፣ አቶ ሰለሞን ሽፈራው (ይቅርታ) አቶ “ቢላል” ፣ የደራሲያን ማህበሩ ያሉበትን መሰረታዊ ችግሮችን እና መፍትሔዎችን ከማመላከት ይልቅ ለርሳቸው የቀለላቸው፣ የማህበሩ አመራሮች እና አባላቶችን የፖለቲካ አቅዋም “በመናገር” በሌሎች ዘንድ ማሳጣት ነው፡፡

እዚህ ላይ እንዲሰመርበት የምፈልገው ነጥብ አለ፡፡ የዚህ መልስ ምት ጸሐፊ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር አይደለሁም፡፡ የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ አካል ግን ነኝ፡፡ እንደ ብዙ ገለልተኝ ጸሐፍት የኢትዮጵያን ደራሲያን ማኅበር እንቅስቃሴ ድክመት ግን ለባለሙያው ሊሰጠው ከሚችል ድጋፍ አንጻር እያነሳሁ ከሚተቹ ሰውች አንዱ እንደሆንኩ አረጋግጣለሁ፡፡ ታዲያ አቶ ሰለሞን (ይቅርታ) አቶ “ቢላል” በጻፉት ትችት ላይ ለምን ቅሬታዬን አሰማለሁ?? . . . ነገሩ ወዲህ ነው፡፡

በአንድ ሙያዊ ማኅበር የታቀፉ ሥራ አስፈጻሚዎችም ሆኑ አባላት የፖለቲካ አመለካከት የማኅበሩ ጉዳይ እንዳልሆነ አምናለሁ፡፡ እንዳልኩት አንድ ነገር ያስማማናል ብዬ አምናለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር እንደ ሙያ ማኅበርነቱ መሥራት ያለበትን እንዳልሠራ ርግጥ ነው፡፡ (ወዳኋላ ተመልሰን ከዚህ ቀደም በነበሩ አመራሮች የተሠሩትን ማተት የርዕሰ ጉዳዩን መስመር ያስታልና መጥቀሱ ፋይዳቢስ በመሆኑ አልፌዋለሁ፡፡)

የአቶ ቢላል ሃተታ በደራሲ ማህበሩ የሚስተዋለውን ከአቅም በታች ያለን አተገባበር በማስረጃ አስደግፎ በማቅረግ መፍትሔውን እንደማመላከት ፣ የአባላቱን የፖለቲካ አቅዋም ላይ በመዘበት የደራሲያንን ብቃት በአንቶ ፈንቶ የመንደር ወሬ ጭቃ መቀባቱን ግን እቃወማለሁ፡፡ ተቋውሜንም እንዲህ እቀጥላለሁ፡፡ ልብ በሉልኝ፡፡ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር አባል አይደሉም፡፡ አለመሆኔ ግን የአቶ ቢላል (ይቅርታ) የአቶ ሰለሞንን ጽሑፍ ከመቃወም አያግደኝም፡፡ እንድቃወም ያደረገኝ ምክንያትም ይሄው ሚዛን በማይደፋ ማስረጃ የተጻፈ ጽሑፍ ነው፡፡

“የሥነ-ጽሑፍ ትምክህተኝነት” በሚል ርዕስ የተጻፈው ይህ ሀተታ፣ ከመነሻው ጀምሮ የሚስተዋሉበት መሰረታዊ እርስ ራሳቸው የሚጣረሱ አሉባልታዎችን መሠረተ-ቢስነት ማጋለጥ ግድ ነውና!

ጥያቄ 1

(ከዚህ በታች ለጻፍከው የቀረበ)

------------------------

“….የሀገራችን ስነፅሁፍ ዛሬም ከመቼውም ጊዜ በላይ ለጥላቻ ፖለቲካ ማራመጃ እየተደረገ እንደሚገኝ ተጨባጭ ማስረጃዎችን በዋቢነት እያጣቀስኩኝ ልቀጥል፡፡ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በዚህ ረገድ እያበረከተ ያለውን አሉታዊ አስተዋፅኦ ላስቀድምና ከዚያም ወደየአሁኖቹ “ደፋር” የግል ፕሬስ ውጤቶች እመለሳለሁ፡፡
በተለይም ከ1990ዎቹ መጀመሪያ ወዲህ በኢትዮጵያችን የስነፅሁፍ ታሪክ ውስጥ ተወልደው በማደግ ላይ ከሚገኙት ወጣት ደራሲያን መካከል፣ እንደለጌታ ከበደ አንዱ ነው፡፡ በዚህ መሰረትም የአንጋፋው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ዋና ፀሐፊ ሆኖ ከተመረጠ ከስምንት ዐመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ እናም ይሄው ወጣት ደራሲያችን የሙያ፣ ማብሀሩ የሰጠውን ስልጣን በመተገን ስነፅሁፋችንን ጭፍን ጥላቻ ለተጠናወተው የፅንፈኛ ተቃዋሚዎች ድብቅ ዓላማ ማስፈፀሚያ ሊያደርገው የማይፈነቅለው የትምክህተኝነት ድንጋይ፣ የማይቆፍረው የጠባብነት ጉድጓድ፣ እንደሌለው በተደጋጋሚ መታዘቤን እነሆ ከዚህ እንደሚከተለው በተጨባጭ ምክንያታዊነት አስደግፌ አወጋችሁ ዘንድ እገደዳለሁ፡፡
ለወትሮው በተለያዩ የፈጠራ ፅሁፎቹ (አጫጭርና ወጥ የልቦለድ ድርሰቶቹ) የምናውቀው እንደለጌታ ከበደ “ፍትሕ” በሚል ርዕስ ይታተም ከነበረው የምፅዓት ቀንን ናፋቂ የግል ጋዜጣ ጀምሮ እስከአሁኑ “ፋክት” መፅሔት ድረስ የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጋሻ ጃግሬ እንደሆነ የዘለቀ ቋሚ የፀረ ኢህአዲግ ፅሁፍ አቅራቢ፣ ወይም “አምደኛ” ከመሆኑም ባሸገር፣ የደራሲያን ማህበር ዋና ፀሐፊነቱን ተተግኖ የሚፈፅመው ደባ ግን ከሁሉም የከፋና “ሀይ!” ሊባል የሚገባው አስነዋሪ ተግባር ሆኖ ነው ያገኘሁት፤ እኔ በግሌ፡፡
ለዚህ አባባሌ የተሻለ አብነት ሊሆነኝ የሚችለው ደግሞ፣ ህዳር 27 ቀን 2004 ዓ/ም “የዓባይ ዘመን” በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በብሔራዊ ቴያትር አዳራሽ አዘጋጅቶት የነበረው የኪነጥበብ መድረክ ነው፡፡
እንደእኔ እምነት ከሆነ በዚያ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴሩ ክቡር አቶ አሚን አብዱልቃድር በክብር እንግድነት ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ኪነጥበባዊ ዝግጅት ላይ፣ መድረክ መሪ የነበረው እንደለጌታ ከበደ ያሳየው እጅግ በጣም ቅጥያጣ ንቀት፣ የእርሱን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አመራር አካላትና እንዲሁም ከበስተጀርባቸው ሆነው “ጎሽ..! የሚላቸውን ነውጥ ናፋቂ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጭምር የከፋ ትዝብት ላይ የሚጥል ቅንነት ማጣት ይመስለኛል፡፡ …..”

---------------------------

እኔ ምለው . . . ማኅበሩ የሚታማው በጥላቻ ፖለቲካ አራማጅነት ሳይሆን የገዢውን መንግስት በመደገፍ እንደሆነ ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው፡፡ ታዲያ ይህን መንገር የአባላትን የፖለቲካ አቅዋም እንዴት ከማኅበሩ ጋር ማቆራኘት ተቻለህ??

ለመሆኑ፣ በዚህ ጥላቻ በሚዘራ አመለካከትህ ላይ ሕገ-መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ከአገራቸው ሳይሰደዱ፣ የክስ እና ውክቢያ ተፅዕኖን ተቋቁመው እየጻፉ ያሉትን ጋዜጠኞችን በደፍናናው ማበሻቀጥ ከስም ማጥፋት ወንጀል ተለይቶ የሚታይ ይመስልሃልን?? (ወይስ አንተም ሃሳብ የመግለጽ መብትህን ለዘለፋ እያዋልከው ነው??)

ኧረ ለመሆኑ፣ “ፀረ-ኢህአዲግ ናቸው” ማለት በአንተ መዝገበ-ቃላት ትርጓሜው ምን ይሆን?? የሥርዓት ብልሹነትን ነቅሶ ማውጣትና ድክመትን ማተት ኢ-ልማታዊ ሊያስብልስ እንዴት ይቻለዋል?? ልማታዊ ጸሐፊ መሆን ማለት እኮ የግድ መልካሙን ነገር ብቻ መልሶ መላልሶ ማተት አይደለም፡፡ የመናገር ነፃነት በማንቆለጳጰስ ላይ ብቻ ይገደብ ያለውስ ማነው??

“ምጽዓት ቀን ናፋቂ” ብለህ ያበሻቀጥካቸው ጋዜጠኞች እንደ ተስፋይቱ ምድር ኢትዮጵያም “ማር እና ወተት የሚፈልቅባት አገር ናት” ለምን አላሉም ብለህ ከሆነ ተሳስተሃል፡፡ እንኳን ከፊል ዲሞክራሲን ቆንጥራ በምታቀርበው አገራችን ቀርቶ የዲሞክራሲና መልካም አገዛዝ ማማ ላይ ተፈናጠናል በሚሉት ያደጉት አገራትም ብልሹ አሰራርን ተቃውመው የሚዘግቡ ጋዜጠኞች ይህ ስያሜ አልተሰጣቸውም፡፡

ጥያቄ 2
------------------------

“….ህዳር 27 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር “በራሱ ተነሳሽነት” እንዳዘጋጀው እያንዳንዱ የአመራር አካላት በነቂስ የተናገረለትን ያን የድበበቆሸ መድረከ በአጋፋሪነት እንዲመራ በዝግጅት ኮሚቴው መመረጡን አስቀድሞ የነገረኝ ዋና ፀሐፊው እንዳለ ጌታ ከበደ፣ የዶ/ር በድሉን ማንነት ለታዳሚው ያስተዋወቀበት የወገንተኝነት ስሜትና አኔ መጨረሻ ላይ ወደ መድረከ ወጥቼ “ተወራራሽ ሕልሞች” በሚል ርዕስ የፃፍኩትን የህዳሴ ዘመን ግጥሜን ሳነብ ከየት እንደመጣሁ እንኳን ሊናገር አለመፈለጉ ምን ያህል ቅስሜን እነደሰበረውም በዚሀ አጋጣሚ ልገልፅለት እወዳለሁ፡፡….”

----------

ጸሀፊው (አቶ ሰለሞን) ይቅርታ (ቢላል) . . . ስለ ኢትዮጵያ ደራሲያን ሲያትት . . . እራሱን የማኅበሩ አባል እንደሆነ ጠቅሶ እንደ ሙያ ማኅበር ያለበትን ድክመት ሳይጠቅስ፣ የፖለቲካ አቅዋም እንደ አጀንዳ ማንሳቱ ለምን አስፈለገ?? “እከሌ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ነው፣ እንቶኔ “ፍትህ” ላይ ይጽፋል፣ በድሉ ‹እውነት ማለት . . .› የሚለው ግጥሙ ጨለምተኛ ነው፣ አባይ ግድብን አስመልክቶ በተዘጋጀ መድረክ ላይ ልማት የሚያደናቅፍ ግጥም አነበበ፣ . . . እንዳለጌታ “. . . ወደ መድረከ ወጥቼ “ተወራራሽ ሕልሞች” በሚል ርዕስ የፃፍኩትን የህዳሴ ዘመን ግጥሜን ሳነብ ከየት እንደመጣሁ እንኳን ሊናገር አለመፈለጉ ምን ያህል ቅስሜን እነደሰበረውም በዚሀ አጋጣሚ ልገልፅለት እወዳለሁ፡፡” ማለትን ምን አመጣው??

የዚህ ሁሉ ሃተታ ፍፃሜ የጽሑፉን ጭብጥ የግል ቂም ከማስመሰል የዘለለ ፋይዳውስ ምንድነው??

እጅግ በሥራቸው አንቱ ያልናቸውን ጸሐፊያን ላይ ክብረ-ነክ በሆነ መንገድ ድንገት ተነስቶ መዘርጠጡ በራሱ ትምክህት አይደለምን??

ቅዳሜ 31 ኦገስት 2013

Reading Culture in Ethiopia. a paper presented in PEN Ethiopia International Conference


PEN ኢትዮጵያ ባዘጋጀው የመጀመሪያው የደራሲያን/ያት ዓለም አቀፋዊ ጉባዔ ላይ የቀረበ ነው፡፡ ሙሉውን ጽሑፍ በ ፒ.ዲ.ኤፍ ያገኙታል እና ቢያነቡት እወዳለሁ፡፡ ፔን ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ፔን አባል የሆነው በ2008(እ.ኤ.አ.) ሲሆን ከመጀመሪያው ብሔራዊ የጸሐፍት ጉባዔ ላይ “ንባብን ማስፋፋት” የተሰኘው ዘገባ ጉባኤ መጽሔት በሁለተኛው የጸሐፍት ጉባኤ በተሳተፍኩበት ወቅት እጄ ሊገባ ችሏል፡፡ በመጽሔቱ ላይ ያሉ መረጃዎች በስፋት ይነበቡ ዘንድ ከለኝ ጉጉት የተነሳም የባለሙያዎችን የጥናት ወረቀት በፒ.ዲ.ኤፍ ማግኘት እችል እንደሆን ለፔን ኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ለአቶ ሰለሞን ኃ/ማርያም ጥያቄዬን አቅርቤ ስለተባበሩኝ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ ኄ.ስ 
   
  -----------------------------------

የማንበብ - መጻፍ ባህል በኢትዮጵያ ፡- አበረታችና አድካሚ አዝማሚያዎች


(አብርሃም ዓለሙ፤ አ.አ.ዩ)

ከአፍሪካውያን እይታ ልትደብቀው የምትፈልገውን ነገር መጽሐፍ ውስጥ አስቀምጠው” የሚል የፈረንጆች አባባል አለ፡፡ ማንበብ በአፍሪካውያን ሕይወት ውስጥ ምንም ቦታ እንደሌለው ለማመልከት የሚናገሩት ነው፤ 'አፍሪካውያን እና ንባብ አይተዋወቁም' ዓይነት ንቀት አዘል አስተያየትም ሊሆን ይችላል፡፡  . . . .

Reading Culture in Ethiopia. a paper presented in PEN Ethiopia International Conference