እሑድ 24 ማርች 2013

“የሁለት የረሃብ ግጥሞች ረዥም ጉዞ”

ለፕሮፌሰር ሱራፍኤል ግርማ /
Professor Sourafel Girma

Professor of Industrial Economics

School of Economics

The University of Nottingham

Nottingham NG7 2RD

United Kingdom
------

“የሁለት የረሃብ ግጥሞች ረዥም ጉዞ”


የተሰኘውን ጥናት እንዳነበው ለላኩልኝ

ምስጋናዬ ባሉበት ይድረስዎ

ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ግጥም እንደፈርጥ የሚያበሩ ሥራዎቹን ትቶልን ቢያልፍም እኛ የጥበብ አድናቂዎች በሕይወት እስካለን የባለቅኔውን መልካም ሥራዎች ስናወድስ እና ስንመረምር እንኖራለን፡፡

“የሁለት የረሃብ ግጥሞች ረዥም ጉዞ” በሚል ርእስ የላኩልኝ መልዕክት ጠቃሚነቱ ለሌሎች መሰሎቼ እና የጥበብ አድናቂዎች ጠቃሚነቱን ከግምት በማስገባት የፒ.ዲ.ኤፍ ቅርጹን ሳይለቅ እንደላኩልኝ ላስነብበው ወደድኩ፡፡ በድጋሚ ምስጋናዬ ይድረስዎት!!

                                                                                                                           ሄኖክ ስጦታው
“የሁለት የረሃብ ግጥሞች ረዥም ጉዞ” 

ቅዳሜ 9 ማርች 2013

ረሃብ ስንት ቀን ይፈጃል?- ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን



ረሃብ ቀጠሮ ይሰጣል?
ወይስ ቀን ቆጥሮ ይፈጃል?
"የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል"
ይባላል፡ ድሮም ይባላል፡
ይዘለዝላል ይከትፋል
ብቻ እስከሚጨርስ ድረስ፣ ሆድ ለሆድ ጊዜ ይሰጣል?
ወተት አንጀት ነጥፎ ሲላብ
ሆድ ዕቃ ደርቆ ሆድ ሲራብ
ተሟጦ አንጀት በአንጀት ሲሳብ . . . .
የጣር ቀጠሮው ስንት ነው
ለሰው ልጅ ሰው ለምንለው 

እሑድ 24 ፌብሩዋሪ 2013

እንዳይነግርህ አንዳች እውነት ! - ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን


እንዳይነግርህ አንዳች እውነት ! - ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን

ደንስ ጎበዝ ! ደንስ ጀግና
ክራቫትህን አውልቅና
ሃሳብህን ልቀቀውና
ኮትክን ሸሚዝክን ጣልና
ርገጥ ፣ ጨፍር ፣ ደንስ ጀግና !

ያን የሙዚቃህን ናዳ ፣ የኮንትራባሱን መብረቅ
ልቀቀውና ይድብለቅለቅ
ምድር በሆይታ ይጥለቅለቅ !
ምንም-ምንም እንዳታስብ ፣ ሁሉን-ሁሉን እንድትረሳ
ደንስ ! ካካታው ይነሳ
ጨፍር ፣ ወለሉ እስኪበሳ ....

ሃይ-ሃይ ! ዋይ ! ሃይ-ሃይ ! በልበት
የጃዝ ፋንፋር አንኳኳበት
ራስክን እንዳታስብበት ፤
ሆ ! በል እሪ ! በል ምታበት
ፎክርበት ፣ አቅራራበት
አናፋበት ፣ ሸልልበት
የሲቃ ሳቅ አስካካበት
ሆያ-ሆዬ ! በል ጩኽበት
ኡኡታህ መንኮራኩርክን ፣ እስኪያሰጥመው አጓራበት
ጭንቅላትክን ግዘፍበት ፣ ውቀጥበት ፣ ውገርበት ፣ ....
ዝግ ብሎማ ያሰበ እንደሁ ፣ ይነግርሃል አንዳች እውነት !
-----------
ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን

እሑድ 17 ፌብሩዋሪ 2013

የሁለት ግጥሞች ወግ ፤ ብቻዬን እና ብቻውን



ብቻዬን /ታገል ሰይፉ

-------
ሰዎች ርቀው ካጠገቤ-
ዙሪያዬን ከቦኝ ፀጥታ
በፀጥታው መሐል ስጓዝ-
ናፍቆቴን ውጬ በዝምታ. . .
ቅጠሎች ተንሾካሾኩ-
ገባኝ እኔም ሀሜታቸው
ከብቸኝነት በርሃ-
ብቻውን ቀረ ማለታቸው፡፡
ጥላዬም ይህን ሰማና
በዝምታ ተከተለኝ
ሁሉም ቢከዱህ እንኳን
እኔ አልከዳህም እያለኝ. . .
እባክህ ተወኝ ጥላዬ
አትሞግተኝ በሽንገላ
ማየቴ አይቀርም ከቆየሁ-
አንተም ስትከዳኝ እንደሌላ…
---------
ታገል ሰይፉ(የካቲት 3-1986)
,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,

ብቻውን / ወንድዬ አሊ
-------
ብን . . . እብስ
ብን . . . እብስ
ከጥላው ተጣልቶ … ከራስ ተሰራርቆ
ከራስ ጠረን ሸሽቶ … እስትንፋስን ርቆ
በመብረቋ ደቆ
ብን . . . እብስ
ብን . . . እብስ
ሌት ቀን . . . ደንብዞ
በ'ጣ ተክሏ መሮ - ሕመሟን ደንዝዞ
ማመን . . . መተማመን
ቅዠቷን . . . ደንግጦ
ቀጋ ጡቷን . . . መጦ
ብን . . . እብስ
ብን . . . እብስ
አለኋችሁ ላይል … አለሁ ባይም አጥቶ
ጠሪ ባያገኝም … እሱም ለወይ ታክቶ
በሰው ጫካ መሐል … ቀልብያው ሸፍቶ
የመሐል አጠገብ … እሩቅ ተሰውሮ
ባይተዋርነትን … ሰቀቀኗን ነፍሮ
ነጠላውን ቀዞ
በቅንዓት … ነብዞ
ሌላ ምንም አይደል
ታሽቶ - መታሸቱ
ብን . . . እብስ ማለቱ
ብቻው ብቻ … ሲቀር
ብቻ ሲቀር አይደል!? … በብቸኝነቱ!
------
ወንድዬ አሊ፣ ወፌ ቆመች መጽሐፍ

ዓርብ 15 ፌብሩዋሪ 2013

“ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ አጭር የሕይወት እና የጽሑፍ ታሪክ” መጽሐፍ ታተመ!!!

የምስራች!!!!
ዮሐንስ አድማሱ ለአራችን ዘመናዊ ሥነጽሑፍ እድገት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው፡፡ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ በኋላ ግጥሞቹን እና የምርምር ስራዎቹን ለአደባባይ እንዲበቁ ታላቁ መምህር፣ የስነጽሑፍ ተመራማሪና ገጣሚ ደበበ ሰይፉ እና ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ ብሎም የባለቅኔው ወንድም ዶ/ር ዮናስ አድማሱ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡
ዮሐንስ አድማሱ “ሰውየውና ሥራው - አጭር የሕይወቱና የሥነጽሑፍ ሥራው ታሪክ” በሚል ርዕስ ከፍተኛ ጥናት እና ምርምር ያደረገበት የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ መጽሐፍ ከአራት አስርት ዓመታት በኋላ “ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ አጭር የሕይወት እና የጽሑፍ ታሪክ” በሚል ስያሜ የሕትመት ብርሐን አግኝቷል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ የታተመው ይህ መጽሐፍ የካቲት 13 ቀን 2005ዓ.ም ከቀኑ 10፡30 ሰዓት በብሔራዊ ቴአትር ይመረቃል፡፡


ዮፍታሔ ንጉሴ
[1897 - 1939]
የደራሲው ሥራዎች
1. እኔ አይኔን ሰው አማረው(ግጥምና ቅኔ)
2. ዐጥንቱን ልልቀመው፥ መቃብር ቆፍሬ(ግጥምና ቅኔ)
3. ወላድ ኢትዮጵያ ለልጆቿ ብላ(ግጥምና ቅኔ)
4. ጎበዛዝቴ ሆይ ወይ ቆነጃጅቴ(ግጥምና ቅኔ)
5. ሰውን ሰው ቢወደው አይኾንም እንደራስ(ግጥምና ቅኔ)
6. አወይ ጥርሴ ሞኙ ዘወትር ይሥቃል(ግጥምና ቅኔ)
7. ሙናዬ(ግጥምና ቅኔ)
8. የኛማ ሙሽራ(ግጥምና ቅኔ)
9. አንተ ባለጐዛ(ግጥምና ቅኔ)
10. ድንግል አገሬ ሆይ ጥንተ ተደንግሎ(ግጥምና ቅኔ)
11. የእኛማ ሀገር(ግጥምና ቅኔ)
12. ሰለኢትዮጵያ(ግጥምና ቅኔ)
13. ትንሽ ዐማርኛ(ግጥምና ቅኔ)
14. የሥነ- በዓል መዝሙር...እንደመፋቂያ(ግጥምና ቅኔ)
15. ጉሰማዬ(ግጥምና ቅኔ)
16. ተነሱ ታጠቁ(ግጥምና ቅኔ)
17. አብሪ ብርሃንሽን(ግጥምና ቅኔ)
18. የባሕር ዳር ጨፌ(ግጥምና ቅኔ)
19. ባገር ገዳይ፥ቋጥኝ ድንጋይ...(ግጥምና ቅኔ)
20. በለስ ለመለመች(ግጥምና ቅኔ)
21. እስክትመጣ ድረስ...(ግጥምና ቅኔ)
22. ጎሐ ጽባሕ(ግጥምና ቅኔ)
23. አገሬ ኢትዮጵያ...ሞኝ ነሽ ተላላ...(ግጥምና ቅኔ)
24. የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር(ግጥምና ቅኔ)
25. የሰንደቅ ዓላማ መዝሙር ደሙን:ያፈሰሰ፥ተጣማጅ: አርበኛ(ግጥምና ቅኔ)
26. አፋጀሽኝ(ተውኔት)
27. እያዩ ማዘን(ተውኔት)
28. ስለአያ ከምሱና ስለአያ እነባንት ይቀጡ(ተውኔት)
29. እለቄጥሩ / ጎበዛዝት(ተውኔት)
30. ጥቅም ያለበት ጨዋታ(ተውኔት)
31. የሕዝብ ፀፀት፥የእመት በልዩ ጉዳት(ተውኔት)
32. የሆድ አምላኩ ቅጣት(ተውኔት)
33. ዕርበተ ፀሐይ(ተውኔት)
34. ምስክር(ተውኔት)
35. ያማረ ምላሽ(ተውኔት)
36. ዳዲቱራ(ተውኔት)
37. ሞሽሪት ሙሽራ(ተውኔት)
38. መሸ በከንቱ፥ ሥራ ለፈቱ(ተውኔት)
39. ጠረፍ ይጠበቅ(ተውኔት)
40. ዓለም አታላይ(ተውኔት)
41. የደንቆሮዎች ትያትር(ተውኔት)
42. ንጉሡና ዘውድ(ተውኔት)

ስለደራሲው በጥቂቱ
" ኮከብ እምኮከብ ይኄይስ ክብሩ" የሚል የኖረ የግእዝ አባባል አለ:: አንዱ ኮከብ በብርሀኑ፤ በግዘፉ፤ መጠቅላላ ተፈጥሮው ከሌላው ኮከብ ይበልጣል:: እኔን የሚያስገርመኝ ይኽ አይደለም:: እንዳንድ ከዋክብት አሉ--በተለየ አጠራር ተወርዋሪ የምንላቸው:: በሌሊቱ ኅዋ ውስት ከአንዱ መአዘን ሰማይ ወደ ሌላው ተወርውረው ብልጭ ብለው ይጠፋሉ:: ይህ ሁሉ የሚሆነው በቀፅበት ነው::ያንን በጨለማው ግርማ የተዋጠውን ኅዋ በብርሃን ጎርፍ ሰንትቀው አጥለቅልቀውት ይጠፋሉ:: ተመልካችም ከመገረም በሚመነጭ ዝምታ ይዋጣል:: በኢትዮዽያም የሥነ ጽሑፍ ኅዋ ውስጥ ዮፍታሔ ንጉሤ አንድ ተወርዋሪ ኮከብ ነበር።

ብሩህ ነጸብራቁ፤
ውበቱና ድምጹ አንድነት ተሰማ
ተው አንድነት ቢበርቁ፤ የመያው
ቅለት ጠፍቶ፤ ምስጢሩን አካቶ፤
ተወርዋሪ ኮከብ በራሱ ነበልባል
በራሱ ነዲድ ተቃጥሎ የጠፋ፤
ተወርዋሪ ኮከብ በምናየው ሰማይ
ነበረ በይፋ።

አዎን፤ ነበረ። በዚያን ቅጽበት በሆነው የጽሁፍ ዘመን ዮፍታሔ፤ የኢትዮዽያን የስነጽሁፍ ኅዋ በቅኔ ፤ በግጥም ፤በመዝሙርና በተውኔት የብርሃን ጎርፍ ሰንጥቆ አጥለቅልቆት ጠፍቷል። ዛሬ የሚያሳዝነው የዚህ ተወርዋሪ ኮከብ ተጽእኖ በዘመናችን መጥፋቱ ነው።

ስለ ዮፍታሔ ንጉሴ በሕፃንነቴ እናት አባቴ ሲያወጉ፤ ሲወያዩ፤ አንዳንዴም ሲከራከሩ እሰማ ነበርበተለይ አባቴ ከዮፍታሔ ንጉሴ ተውኔቶችና መዝሙሮች በቃሉ የሚያስታውሳቸውን ስንኞች ሲያንጎራጉር እየሰማሁ የዮፍታሔ ፍቅር በሕፃን ልቦናዬና ስሜቴ ተሳለብኝ ። ያኔ ከሰማኋቸው ትዝ የሚሉኝ "አንተ ባ...ጎራዴ ግዛ" እና "ወላድ ኢትዮዽያ ለልጆቻ ብላ እጅግ ሳይትሩባት ሳይዘሯት አብቅላ" የተባሉት መዝሙሮች ናቸው። ሁለተኛው በጣም ጠሊቅ መዝሙር ነው። ጠሊቅነቱ የተገነዘብሁት ካደግሁ በኋላ ነው። ያኔ መዝሙሩ ይመስጠኝ የነበረው በቃላቱ ጣእመ ዝማሬ ነበረ። የፊተኛውን መዝሙር ግጥሙን በሙሉ ላገኘው አልቻልሁም። የኋለኛው ግን "ብርሃንና ሰላም" ይባል በነበረው ጋዜታ በሙሉ ተጽፎ ስላገኘሁት ከዚህ ቀጥሎ ጽፌዋለሁ፤

ወላድ ኢትዮዽያ ለልጆቿብላ፤
እጅግ ሳይጥሩባት ሳይዘሯት አብቅላ፤
ስንዴውን ጠብቃ እንክርዳዱን ነቅላ፤
ስትመግበን አየን በፀሐይ አብስላ።

ምሳሌ ዘርእ አገራችን፤
ንጹሕ ዝናብ መንግሥታችን።
በመልካሙ ዘርእ ላይ እንክርዳቸ ሲዘራ፤
ታሳድገውና ከእንክርዳዱ ጋራ፤
ገለባ ሲቃጠል ገበሬ ሲያመራ፤
ታቃጥለዋልች እንክርዳዱን አብራ።
ምሳሌ ዘርእ አገራችን፤
ንጹሕ ዝናም መንግስታችን ።
አይዞህ የኛ ጌታ ነገርህን አትርሳ፤
አለስልሰህ ዝራ የስንዴውን ማሳ፤
የተዘራችው ዘርእ ፈርሳና በስብሳ ፤
ታፈራልቸ ፍሬ ሙታ ስትነሣ።
ምሳሌ ዘርእ አገራችን፤
ንጹሕ ዝናም መንግስታችን ።
በጊዜው የዘራ መልካም ዘር አትርፎ፤
ከበሮቹ ጋራ ማታ ከትላ አርፎ፤
ብርነት ታትቆ በቅን ተሰልፎ፤
በቸርነት ታጥቆ በቅን ተሰልፎ፤
ደግሞ ዘሩን ዘራ መክር አሳልፎ።
ምሳሌ ዘርእ አገራችን፤
ንጹሕ ዝናም መንግስታችን ።

ኋላም ትምህርት ቤት ከገባው በኋላ፣ በተለይም መሁለተኛ ደረጃ በነበርሁበት ጊዜ ፣ በብላታ መርስዔ ሐዘን ስዋስው ውስጥ የዮፍታሔ ቅኔዎች፣ ግጥሞችና መዝሙሮች አልፎ አልፎ ተጠቅሰው በማግኘቴ በቃሌ አትንቼ እንደ ዳዊት እደግማቸው ነበረ። መጀመሪያ ምናቤን የመታው ፤ ስሜቴን የነካው የዮፍታሔ የቋን ቋው ኀይልና ውበት ነበር።ኋላም ስለ ቅኔም ሆነ ስለግጥም አንዳንድ ነገር ከገረጫጨፍሁ በኋላ ያን መጀመሪያ ምናቤን የመታውን፣ ስሜቴን የነካውን የቋንቋ ኀይልና ውበት መመርመር ጀመርሁ። የዮፍታሄ ስንኞች መቀነባበር፤ የዘይቤው ወይንም የስለምኑ መተባበርና መዋሐድ ፤ በስተቅኔውም በኩል የሰምና ወርቁነ፤ የውስተ ወይራው፤ የሰም ለበሱ ፤ የኅብሩና የምርምሩ አካሄድ እስከ ዛሬ ከተነሱት ገጣሚዎች ሁሉ ዮፍታሔን የተለየ ያደርጉታል። የዮፍታሔ ርቀቱ ፤በኪነት ሥራው ሁሉ ከሀብተ ትንቢት ጋር የተሳላው የዘይቤው ወይንም የስለምን ስልቱ ልዝብ በመሆኑ አይኮሰልም፤ ወይንም ሌላ ሊቀዳው አይችልም። ወጥነቱ የተመሠረተው በዚህ ላይ ነው። ---ንጹሕ የኪነት ወጥነት ነው።
ምንጭ፡-http://ethioreaders.com/authorbook.php?fl=192&lg=A

እሑድ 10 ፌብሩዋሪ 2013

እውነት አሁን አንቺ እሷ ነሽ! ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን


እውነት አሁን አንቺ እሷ ነሽ! ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን
---------
እሷ ነኝ በዪኝ ግድ የለም! . . . .
ሁሉ ላፍ አልተፈጠረም
ቢሉም አፍ አይለው የለም።
ልወቀውና ላውጣ እርሜን፥
የስንት ዘመን ረሃቤን
ልጋረጠው በዓይንሽ አይኔን።
ልጅነቴን የዳኽኩበት፥ የስንት ዘመን ፈለጌ
በናፍቆት ቋት ተሰግስጌ
በእግረ ሕሊና ጠርጌ
በትዝታ በዳሰሳ፥ በፈለግሽ የናዳ ዳር
ስዋትት ስማስን በጣር
ዛሬ ያገኘሁሽ ባሣር
በስንት ዘመን የዕድሜ ምጥ
እውነት አንቺ እሷ ነሽ እርግጥ?!
መምሰል ትመስያለሽ
ማከልማ ታክያለሽ
የደም ግባቷን ተላብሰሽ
መጠሪያዋን ተሰይመሽ . . . .
ያቺን የኔን .... ያቺን የኔን
የኔን የመጀመሪያዬን
የጥንቴን የልጅነቴን
የስንት ዘመን ሕመሜን
የሕልም ዓለም ሰመመኔን
የት አረግሻት? የት ደበቅሻት?
ዋጥሻት? . . . .
አጥንቷን በአጥንትሽ ለብሰሽ
ወዟን በላቦትሽ ታጥነሽ
በልጅነቷ ልጅ ሆነሽ
ገጿን በግንባርሽ ነድፈሽ
አበቧን አደብዝዘሽ
መልኳን በመልክሽ አክስለሽ
ቡቃያዋን በዕድሜሽ ውጠሽ
በስም ብቻ እሷን ሆነሽ
ማነሽ? እውነት አንቺ ማነሽ
እኮ ንገሪኝ እሷ ነሽ?

እሑድ 27 ጃንዋሪ 2013

የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ - ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን





የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ

ተስፋ ባጣ ምድረ በዳ
ያንድ እውነት ይሆናል ዕዳ፡፡
እና ትንፋሼ አልሆነሽም፥ ሆኜብሽ መራር መካሪ
“ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ፣”
እውነት ላንቺ መች ተስፋ ናት፥ ጉስቁል ልሳንሽን ነክሳሽ
ክንድሽን ካዘለ ቅርስሽ፥ መጠላለፍ ሲሆን እጣሽ
ከእንግሊዝ የሞት አማልክት፥ መተናነቅ ሲሆን ድርሻሽ
መልመጥመጡ፥ መሽቆጥቆጡ፥ መስሎሽ ድንገት የሚያዋጣሽ
የኔ እውነት ሆነብሽ ዕዳሽ ፡፡  …..
ወራሪም ፈጣሪን ላያቅ
የጣለውን በስሏል እንጂ፥ ወድቋል ብሎ ግፉ ላያልቅ
መች ትተርፊያለሽ ኢትዮጵያ፥ ሕዋስሽ አብሮኝ ካልሠራ
አንገትሽ ብቻ መቅደላ፥ አፋፍ ወጥታ ብታበራ
የቀረው ሠራ-አከላትሽ፥ በየጥሻው ተዘርሮ
ከአባት በወረሽው ንፍገት፥ ነብዞ ደንዝዞ ተቀብሮ
ባጉል ወጌሻ ታጅሎ
እጅና እግርሽ ታሽቶ ዝሎ
እኔን ለጥንብ አንሳ ጥሎ፤
ከደቀቀ ከደከመ፥ ክንድሽ አልነሣ ካለ
ሞት እንጂ ለኔስ ምን አለ?.....
ሆኖም ጐስቋላ አልምሰልሽ፥ የሚያዝንልኝ አልፈልግም
ጠላትሽን በክንድሽ እንጂ፥ በእንባሽ ወዝ ባላሸንፍም
የልቤን ፍቅር በሰተቀር፥ እማወርስሽም ውል የለኝ
የኮሶ ሻጭ ልጅ ደሃ ነኝ፡፡ …..

ሰኞ 21 ጃንዋሪ 2013

ጌታው ባለህበት - ማረፍ በቀለ













ጌታው ባለህበት

አጋድመህ መዘንጠል ከለመድክበቱ
የሚታረድ ጠቦት ከምታስስበት
እዛው ካክራሞትህ ከበረት ከጋጡ
በሩን ተሸሽገህ በጥጋት ቀዳዳ
በሽንቁሩ አልፈው የሚጉረጠረጡ
እነዛ አይኖችህ ጨለማ ይሁኑ!
አልልህም እኔ
ድብስብስ ለሊትን የጭርታን ጊዜ
የዝለትን ሰበብ የቀንን ድንጋዜ
ብርታቱ አድርጎ የሚጣራ ድምፅህ
ዜማ እያምታታ
የእረኛውን ዋሽንት አምስሎ እየመታ
የሚያፏጭ ልሳንህ
ዘላለም ይደፈን ጎሮሮህ ይዘጋ!
አልልህም እኔ
ድንቃፍ ላይመልሱ ላያስጥሉ ከውርጭ
ጨብጠው ላይመሩ ረብ ላይሰጡ ቅንጣት
እቅፍ የዘረጉ - ምርኩዝ ቢያድርጓቸው ሰልትው የተዋጉ
ነፍስ ድረስ ዘልቀው ነፍስ ያስመረቀዙ
እነዚያ እጆችህ አመል የለመዱ
ሰይፍ ይረፍባቸው በጦር ይቀደዱ
አልልህም እኔ