እሑድ 21 ፌብሩዋሪ 2016

"ሶስት ኪሎ ሙዝ በስስ ፌስታል…"

(ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ)

መገናኛ ድልድዩ ስር ሙዝ በቅርጫ ሞልተው የሚሸጡ ነጋዴዎች፣ "ሶስት ኪሎ ሙዝ አስር አስር ብር!" እያሉ ነበር።

ሙዙ ያስጎመዣል። ፞ጠ፞ቃ፞ጠ፞፞፞ቆ፞ የሚባለው አይነት ነው። አላስቻለኝም። ሶስት ኪሎ አስመዘንኩ። በነጭ ስስ ፌስታል አንጠልጥዬ ወደ ታክሲ ተራ አመራሁ።

ታክሲ ውስጥ እንደገባሁ ማምሻ ግሮሰሪ የማውቀውና በአንድ ወቅት ፈንጂ አምካኝ እንደነበረ የነገረኝን ጎልማሳ አገኘሁት። ከጎኑ ተቀመጥኩ። ሰላም ተባብለን ስናበቃ ወሬው ወደሙዝ ተቀየረና ስለጥቅሙ ያትትልኝ ጀመር።

"አሁን ወቅቱ የሙዝ ነው። ሙዝ አፕሬቲቭ ውስጥ የሚገባው ለሀንጎቨር እንደሆነ ታውቃለህ? ይገርምሃል፣ ሙዝን ለመጀመሪያ ጊዜ ለመብልነት ያዋሉት… "

ይህን ሁሉ ማብራሪያ እየሰማሁ ዝም ማለት ስላላስቻለኝ ሁለት ሙዝ አውጥቼ አንድ ሰጠሁት።  ወዲያው አቀለጣጥፎ ከበላ በኋላ ድገመኝ አይነት አስተያየት ሲመለከተኝ ጊዜ ሁለተኛውን ሰጠሁት።

"ይገርምሃል፣ ይህኛው አይነት ሙዝ ኦርጋኒክ አይደለም። ትክክለኛው ሙዝ ከነልጣጩ ነው የሚበላው…"

ይህ ሰው የሚቀደደው ሲጠጣ ብቻ ይመስለኝ ነበር። (ለነገሩ አሁንም ጠጥቶ ሊሆን ይችላል)
በዚህ መሃል ሂሳብ እየሰበሰበ ያለው የታክሲው ረዳት "እንብላ ባህል እኮ ነው" አለ። አንድ ሙዝ አውጥቼ ሰጠሁት። ሙዙን ተቀብሎ ዞር አላለም። ሂሳብ እንድንከፍል እየጠበቀ ነበር። አስር ብር አውጥቼ ሰጠሁት።

"የት ናችሁ? የሁለት ሰው ነው?" ረዳቱ ጠየቀኝ። ምንም ምርጫ የለኝም። እንኳን አብሮ ለጠጣ አብሮ ለበላም ይከፈላል።

ከታክሲው ስወርድ እንደ ተራ አስከባሪ ከታክሲ ተራ የማይጠፋው መኮንን ተቀበለኝ። የሰፈራችን ደላላ ነው።

"እሸት እና ቆንጆ አይታለፍም" እያለ ሙዙ ላይ አፈጠጠ። ላስቲኩን ከፈትኩለትና ሁለት አወጣ። (ማነበር ያ… "ሙዝ የፋብሪካ ውጤት መሆኑን ሳስበው ሁሌም ዲይንቅ ይለኛል" ያለው? )

ሙዙ እጄ ላይ እየቀለለ ነው። እኮ አሁንስ ተስፋዬ ማነው?! ጥቁር ላስቲክ አይደለምን?! ቀጥታ ወደሱቅ አመራሁ። ጥቁር ላስቲክ ልገዛ። የጀበና ቡና ደንበኛዬ ሱቁ ደጅ ላይ ቆማ አየኋት።

ፈገግታዋ ልዩ ነው። እኔንና በፌስታል የየሰዝኩትን ሙዝ አፈራርቃ እያየች…

ኦዉው…!!

ቅዳሜ 20 ፌብሩዋሪ 2016

ዝሆን ለምን…!?

(ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ)

"የተረገመ ዝሆን!!" አለ በሃዘን ልቡ ተነክቶ። "በቃ፣ ለመቅበሪያ ጉድጓድ ለመቆፈር ተጨማሪ ቀን እዚህ ላድር ነው" ሲል አሰበ።
*
*
*
*
*
("በድሮ በድሮ" ጃሉድ ስታይል) ስንቀይረው
*
*

"የተረገመ ዝሆን!!" ሲል በብስጭት አጉተመተመ ጉንዳኑ። "በቃ፣ አፈር ከሚበላው ተሸክሜ ብወስደውና ብንበላው ይሻላል" 
*
*
(ሞት አደላድሎ አፈር ካልተጫነኝ፣ 
ቃሌን አላጥፈውም ካንተ ጋ ኗሪ ነኝ።) 
*
*
ጉንዳኑ ሐዘን ልቡን አደማው።

እናም እውነታውን እያሰበ እንዲህ አለ…
"የተረገመ ዝሆን!! በፍቅር ላሳለፍኩት አንድ ሌሊት ስል እድሜዬን ሙሉ መቃብሩን ልቆፍር ነው ማለት ነው" 
*
*
*
በመቀጠልም ዝሆኑ ሃውልት ላይ የሚያሰፍረው አጭር ግጥም አዘጋጀ፦

"ለምን ሞተ ቢሉ 
ንገሩ ለሁሉ ሳትደብቁ ከቶ
ከዘመን ተኳርፎ፣ ዘመን ተጣልቶ"

ዓርብ 19 ፌብሩዋሪ 2016

ተራማጅ እሳቤ ፵፯

( ኄኖክ ሥጦታው ናኁሰናይ )

ውሃ…
*
ከፍታን መርጦ ሲጣበቅ፣ በረዶ ሆኖ ሲደድር
ውሃም ይወጣል ዳገት፣ ይወርዳል ሙቀቱ ሲንር።
*
በረዶ አቅላጩ ሙቀት፣ በድን አካል ካፈረሰ
ነዲድ ያገኘው አለት፣ ቀልጦ ቁልቁል ከፈሰሰ
መጠጠርስ እንደውሃ ፣
መቅለጥ …
መትነን…፣
 ሽቅብ መውጣት… ቁልቁል መውረድ…
(ቅዝቃዜ ፅሞና ነው። ርጋታን ለአፍታ ልውደድ)
ራስ…
ለራስ…
ከራስ…  ጋ
ጠምቶኛል ዘልቆ መዋኻድ
ከመትነን ከፍታ በታች፦
እንደበረዶ ጠጥሮ፣ ደግሞ እንደ ዥረት ለመውረድ።
*
ውሃ…
ወንዙ መንገድ ቀይሯል፣ የድርቅ ዱካውን ትቶ
ወዴት ወርዶ አለቀ? ከምድር ሰርጎ ገብቶ?
በሰማይ መንገዱ ተጓዘ? በትነት ሽቅብ ወጥቶ?
*
ራሴን ተጠማሁ…

በደረቀው መንገድ ላይ፣ ቆሜ ነበር ሃሳብ ጠምቶኝ
አሁን አቅጣጫው ሲገባኝ፣ የወንዙን መንገድ መረጥኩኝ
ወደሄደበት ብሄድ ነው፤ ጥቂት ውሃ የማገኝ።

ጠምቶኛል…

ረቡዕ 17 ፌብሩዋሪ 2016

"እሾህን በሾህ"

✧(ኄኖክ ስጦታው)
(የአጭር አጭር አጭር ልቦለድ)

ለእራት የሚሆን ነገር ለመግዛት ወደ ሱቅ አመራ። እንደ ሁልጊዜውም፣ ጎረቤቱ የአይጥ መርዝ እየገዛ ነበር። ከጎረቤቱ ቤት መርዝ በልተው እሱ ቤት ኮርኒስ ውስጥ የሚሞቱ አይጦች ሽታ ረፍት ነስቶታል።
"ለምን በወጥመድ አታጠምዳቸውም?" አለና መፍትሄ ይሆናል ያለውን ሃሳብ አቀረበለት። ለጎረቤቱ።
"ሞክሬ ነበር። ወጥመድ ማለት የአይጥ ገበታ ነው። አይጦቹ ወጥመዱ ላይ ያለውን ምግብ በልተው ይሄዳሉ። ጠዋት ስነሳ ወጥመዱ የሚይዘው እኔኑ ነው።"
ዝም አለ።
አስቦ ፣ አስቦ… አንድ መፍትሄ አገኘ። እናም ጎረቤቱ ዞር እስኪል ጠብቆ፦
"የአይጥ መድሃኒት አለ?" ሲል ጠየቀ። ለባለሱቁ።
"የለም። መርዝ ነው ያለው"
"እሱንም ቢሆን ስጠኝ"

ሐሙስ 8 ጃንዋሪ 2015

‘ከዕለታት አንድ ቀን’ (ኄኖክ ስጦታው)




ያው እንደ ልማዴ፣ በፅሞና ሳለሁ፣
ዝምታን ለብቻው ፣ ርጋታን ለብቻው፣ እያዳመጥኩ ሳለሁ—
የመቃብሩ በር ሲንኳኳ እሰማለሁ።

አንዳንዴ ስመሰጥ ፣
ትዝታችን እንዳይሞት፣ የቀበርኩት እለት
የአንድ ቀን ድምር፣ የአሃዝን ግዝፈት
ገንኖ ይታየኛል፣ ገና ሳልል ሁለት።

አንድ!
‘ከዕለታት አንድ ቀን’ ሲደመር ‘ከዕለታት’
አንዳለኝ እያልኩኝ፣ ዝም ብሎ ማስላት።

አንድ!
‘ከዕለታት አንድ ቀን’ ፣ የተዋወቅንበት።
‘ከዕለታት አንድ ቀን’ ፣ የተጣላንበት።
‘ከዕለታት አንድ ቀን’ ፣ ተሳስመን ነበር።
ምራቅሽን ቀምሼ፣ ምራቄን ቀምሰሽው፣ "አቤት መጣፈጡ" ማለታችን ሳይቀር፣
‘ከዕለታት አንድ ቀን’ ፣ ካንዱ ጋር ሲደመር፣
ደግሞም በሌላ ቀን፣ ተጋጭተን በነገር
ማሩ ምራቅሽን፣ ተፍተሽብኝ ነበር።

አንድ!


‘ከዕለታት አንድ ቀን’ ፣ እንዲህ ለብቻዬ፣
አንድን አሰላለሁ፤ አንድ አለችኝ ብዬ።
አንድ ዝምታ ነው። አንዱ ነው ርጋታ
አንዱ ካለአንዱ፤ አይቆምም ለአፍታ ።
          እና።
         ርጋታን ሳዳምጥ፤ ዝምታን ሳናግር ፣
         ከመቃብሩ ቤት፣ ይሰማኛል ጩኸት፣
‘ክፈት! ክፈት! ’ የሚል…
‘ክፈት ይህን በር!’
ያንቺ ድምፅ ነበር።
ድምፅሽን ስሰማ  ፤ "ክፈት" ስትይ "ክፈት"
                           ያስታወሰወኩት ነገር
ካቅሜ በላይ ሆነሽ፣ "ችግሬ" ያልኩሽ እለት
‘ከዕለታት አንድ ቀን’፤ ላንቺ መቀበሪያ
                           ጉድጓዱን ማስኩበት።

ምክንያቱም፦
አንቺን ከዝንጅብል፣ ያቆራኘ ምስጢር
አፈር ነው ህይወትሽ ፣ አትሞችም በቀብር።

አንቺ የኔ ችግር!
ባክሽ ፣ባክሽ ግቢ፤ "ምሳጤ" ና ውጣ
ሁሉም ይዘነጋል፣ ችግሬ ስትመጣ።
______
ኄኖክ ስጦታው

ዓርብ 2 ጃንዋሪ 2015

ይመሻል ፤ ይነጋል...(ኄኖክ ስጦታው)



ጊዜ ለውጥ አልባ ፤ የአሁን ጉዞ ቅጣይ
የቆመ ዑደት ነው ፤ ምንም ሲጓዝ ቢታይ ።
አዲስ ነገር ብርቁ ፤ ሰው ዘመን ይዋጃል
እንኳን አዲስ ዘመን
ወለሃንቲ የለም ፤ አዲስ ቀን የሚባል ።

ለምሳሌ ፦

የዕድሜ ግስጋሴ ፣ በመኖር ይለካል
በመሞት ይዘጋል ።

ይመሻል ፤ ይነጋል...

መሽቶ እንደነጋው ፤ ያው ነግቶም መምሸቱ
የቆመ ሀቅ ነው ። የታለ ዑደቱ?

ለምሳሌ ፦
ዛሬ
ልክ እንደ በፊቱ ፣
ይነጋል ፤ ይመሻል
ከምናውቀው ውጪ ፤ አዲስ ዑደት የታል?
በርግጥ ያንተ ለውጥ ፣ ጊዜን ይለውጣል?

መምሸትና መንጋት ፣ መንጋትና መምሸት ፣ የቆመ ሂደት ነው
መጥቶም እንደመሄድ ፤ ሄዶም እንደመምጣት ፣ የማልቀበለው ።

በቀጠለው ነገ ፣ አዲስ ቀን ጠብቆ
በቀጠለው ነገ ፣ አዲስ ተስፋ ናፍቆ
በቀጠለው ነገ ፣ ብርታትን ሰንቆ
የዛሬውን ሌሊት ፣ የሚተኛ ሞልቷል...
ጊዜ ግን ባለበት ፤ ጉዞው ይቀጥላል...

ለምሳሌ ፦
አሁን!

ቸጨ∴የኄኖክ diary

እሑድ 9 ኖቬምበር 2014

ዱባና ልጅነት

(ኄኖክ ስጦታው)

#ዱባ
ልጅ ሆኜ የሰማሁት ዘፈን አለ። ስለዱባ እንዲህ ብሎ ነበር፦

"ሳይበላ ሳይጠጣ ይወፍራል ዱባ
ልቤ ተንከባሎ አንቺ መንደር ገባ "

ግጥሙን አድጌ ስረዳው ልብ እና የሚንከባለል ዱባ  ያገናኛቸው ቤት መምቻቸው "ባ" እንደሆነ ገባኝ። ዱባ ወጥ አልወድም።  የዘፈኑ ተፅእኖ ነው መሰል፣ ቤታችን ዱባ ወጥ ሲሰራ ገንዘብ የወጣበት አይመስለኝም ነበር ። ተንከባሎ ቤታችን የገባ ነበር የሚመስለኝ።

በልጅነት ዘመን የማልረሳው አንድ ገጠመኝ አለ። የእርሻ አስተማሪያችን ስለ አዝእርት ሲያስተምሩ እንዲህ ብለው ጠይቀው ነበረ፦

"ከጥራጥሬ ውስጥ የሚመደቡት ምን ምን ናቸው?"

ምድረ ተሜ ተራ በተራ እየተነሱ "ጓያ፣ ሽንብራ፣ ባቄላ…" እያሉ መለሱ። መምህሩ ወደኔ እያዩ፣ "ኄኖክ ፣ የምትጨምረው አለ?" ሲሉኝ ፣ ከመቀመጫዬ ተነስቼ "ዱባ" አልኩና ተቀመጥኩ። የተማሪው ሳቅ እና ያስተማሪው ድንጋጤ ተደምሮ፣ በስክሪብቶ ጫፍ ቂጡን እንደተወጋ ተማሪ አስፈንጥሮ አቆመኝ። (ድሮ ተንኮለኛ ተማሪ አጠገቡ የሚቀመጥ ተሜን ብድግ ሲል ያለቀ ስክሮብቶ አሹሎ እስኪቀመጥ ይጠብቅ ነበር። ያሁኑን ባላውቅም።)

መምህሩ በግርምት አፍጥጠው ፣ አፍጥጠው፣ አፍጥጠው… አይተውኝ ሲያበቁ፣ ባፍንጫቸው የንፋስ ሳቅ ("ህምፍ" አይነት) አሰምተው ዱባ ያልኩበትን ምክንያት ጠየቁኝ። ክፍሉ ረጭ አለ ። እንዲህ ረጭ ያለ ዝምታ ለመጨረሻ ጊዜ ያስተዋልኩት ያኔ ነበር።

ዱባ የጥራጥሬ ዝርያ ለመሆኑ የሰጠሁት አጭር ማብራሪያ፦

"የዱባ ፍሬዎች ፀሐይ ላይ ተሰጥተው ሲደርቁ፣ ተቆልተው ይበላሉ። ልክ እንደ ሽምብራና ባቄላ ማለት ነው።" ከማለቴ ክፍሉ በሳቅ ተናወጠ።

ምን  የሚሳቅ ነገር አግኝተው እንደሆነ ለማወቅ አይኖቼን በክፍል ጓደኞቼ ዙሪያ አንከራተትኩ። ሳያቸው ነው መሰል ይበልጥ መሳቅ ቀጠሉ። ከሁሉ ከሁሉ የገረመኝ፣ የመምህሩም አብሮ መሳቅ ነበር። መቆም እንዲህ ያስቃል?

መቀመጥ ሳይሻል አይቀርም።
ተቀመጥኩ።