ረቡዕ 8 ሜይ 2013

ለኔዋ እጩ ሚስት - ኄኖክ ስጦታው



----------
ከፈላጊሽ ለመቃጠር፣ ፍቃድሽ ሆኖ ሳለ
ልቤ እንዴት ይመንሽ፤ “እመነኝ” ስለተባለ?!
ሰበብ የግልሽ እንደሆን . . . ርዕቱእነትም የግልሽ
ባልሽው ብረታም እንኳ፤ ያመንኩሽ ግን እንዳይመስልሽ፡፡
በተጫራች ማዕድ ግብዣ፣ ይጨናነቅ ሆድሽ ይሙላ
በልተሸ ስትጨርሽ ግን እንዳትመጪ በኋላ!
----------
ኄኖክ ስጦታው

ዓርብ 3 ሜይ 2013

ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት /ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን/

ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት 
/ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን/
------------
አዬ፣ ምነው እመ ብርሃን? ኢትዮጵያን ጨከንሽባት?
ምነው ቀኝሽን ረሳሻት?
እስከመቼ ድረስ እንዲህ፣ መቀነትሽን ታጠብቂባት?
ልቦናሽን ታዞሪባት?
ፈተናዋን፣ ሰቀቀኗን፣ ጣሯን ይበቃል ሳትያት?
አላንቺእኮ ማንም የላት….
አውሮጳ እንዲሁ ትናጋዋን፣ በፋሽስታዊ ነቀርሳ
ታርሳ፣ ተምሳ፣ በስብሳ
ሂትለራዊ እባጭ ጫንቃዋን፣ እንደኮረብታ ተጭኗት
ቀና ብላ እውነት እንዳታይ፣ አንገቷን ቁልቁል ጠምዝዟት
ነፍሷን ድጦ ያስበረከካት
ሥልጡን፣ ብኩን፣ መፃጉዕ ናት፤ ….
እና ፈርቼ እንዳልባክን፣ ሲርቀኝ የኃይልሽ ውጋገን
አንቺ ካጠገቤ አትራቂ፣ በርታ በይኝ እመ ብርሃን
ቃል ኪዳኔን እንዳልረሳት፣ እንዳልዘነጋት ኢትዮጵያን፡፡
አዎን፣ ብቻዬን ነኝ ፈራሁ
እሸሸግበት ጥግ አጣሁ
እምፀናበት ልብ አጣሁ
እማማ ኢትዮጵያን መንፈሴ፣ ተፈትቶ እንዳይከዳት ሠጋሁ …
አዋጅ፣ የምሥራች ብዬ፣ የትብት ምግቤን ገድፌ
ከእናቴ ማኅፀን አርፌ
ከአፈርዋ አጥንቴን ቀፍፌ
ደሜን ከደሟ አጠንፍፌ
ከወዟ ወዜን ቀፍፌ
በሕፃ እግሬ ድሄባት፣ በህልም አክናፌ ከንፌ
እረኝነቴን በሰብሏ፣ በምድሯ ላብ አሳልፌ
ከጫጩት እና ከጥጃ፣ ከግልገል ጋር ተቃቅፌ፤
በጋው የእረኛ አደባባይ፣ ክረምት እንደወንዙ ፍሳሽ
በገጠር የደመና ዳስ፣ በገደል ሸለቆ አዳራሽ
ከቆቅ እና ከሚዳቋ፣ ከዥግራ ጠረን ስተሸሽ
በወንዝ አፋፍ ሐረግ ዝላይ፣ መወርወር መንጠልጠል ጢሎሽ
ከፍልፈል ጋር ሩጫ ስገጥም፣ ከቀበሮ ድብብቆሽ
ከናዳ ጫፍ ሣር አጨዳ፣ ለግት ላሜ ትንሽ ግጦሽ
ለጥጃዬ የሌት ግርዶሽ 
ለጥማድ በሬዎች ራት፣ ለማታቸው ትንሽ ድርቆሽ
ለግልገሌ ካውሬ ከለል
እማሳው ሥር ጎጆ መትከል
ለፀሐይ የሾላ ጠለል፣ ለዝናብ የገሳ ጠለል
ውሎ የንብ ቀፎ ማሰስ፣ ያበባ እምቡጥ ሲፈነዳ
የግጦሽ ሣር ሲለመልም፣ ሲሰማሩ ሰደድ ሜዳ
አዝመራው ጣል ከንበል ሲል፣ ከብቱ ለሆራ ሲነዳ
ፈረስ ግልቢያ ስሸመጥጥ፣ ከወፎች ዜማ ስቀዳ
ልቤ በንፋስ ተንሳፎ፣ በዋሽንት ዋይታ ሲከዳ …..
ያቺን ነው ኢትዮጵያ የምላት
እመ ብርሃን እረሳሻት?

ቅዳሜ 6 ኤፕሪል 2013

*በራስ ምስል ዛቢያ- ኄኖክ ስጦታው


*በራስ ምስል ዛቢያ

ልጅ ሆኜ ነበረ ያደረብኝ ፍቅሩ
ዝናብ እና ምሽት-
ካፊያና ነጎድጓድ በአንድ ሲጣመሩ
በእንቅልፌ ሰመመን  እያየሁ ሲዳሩ
ያሸለብኩት ሌሊት-
ቅዠቴ ጣፋጭ ነው ጥዑም ነው አዳሩ፡፡
ለአቅመ-አዳም በቅቼ ከጎኔም ሰው ኖሮ
ዝናባማ ምሽት ማፍቀሬ ጨምሮ
ጨለማ ሲያረብብ ደመናው ተቋጥሮ
እናፍቅ ነበረ ማየት ሰማይ ጠቁሮ፡፡
 ጮርቃነቴ የታል? የታል ልጅነቴ?
    ጓደኞቼም የሉ ሰው የለም ከቤቴ
    መታሰሬን ባዩ በብቸኝነቴ፡፡
ህመሜን ባዩልኝ
ጭንቀቴን ባዩልኝ
ናፍቆቴን ባዩልኝ-!
    መሽቶ ዝናብ ሲጥል
    ከራሴ ስጣላ በስቃዬ ስዝል
ምን እንደምመስል፡፡
,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,
ኄኖክ ስጦታው
1998ዓ.ም

ቅዳሜ 30 ማርች 2013

"አዳር" (የአጭር ልቦለድ ንድፍ) ኄኖክ ስጦታው


አዳር
(የአጭር ልቦለድ ንድፍ)
ኄኖክ ስጦታው
----------------------------
ከምሽቱ 130ሰዓት

አባትህ ጋር ዛሬም አትሄድም?” አሳዳጊው ነበረች ጠያቂዋ፡፡ ታማሚ አባቱ ሆስፒታል ከተኙ ሰንበትበት ቢልም   ሄዶ አለመጠየቁ ውስጥ ውስጧን እየበላው፡፡
                                “ብዙ ሰዎች ስለሚኖሩ የኔ መሄድ ጥቅም የለውም . . . ” ብሎ ወደ መኝታ ክፍሉ ገባ፡፡

*     *     *

230 ምሽት

ቴሌቪዥን ሊያይ ወደሳሎን ሲገባ፣ አክስቱ፡-
አባትህን ጠየከው ተክሉ?”
ዝም አለ፡፡ ያውቃሉ፡፡ እንዳልጠየቀው፡፡ ለነገር መምዘዣ ብቻ ነው ጥያቄያቸው፡፡ አፍ አፉን ሲያዩ ቆይተው መልስ ሲያጡ፡-
አረመኔነት ነው! አወቅን፣ ተማርን ስትሉ ልባችሁ ይደድራል፡፡ ቆይ፣ ለምን አልጠየከውም?”
ቃላቱን እየረገጠእኔን ሲያይ የሚድን ቢሆን ኖሮ ለምን ሆስፒታል መውሰድ አስፈለገ? ” አለ፡፡ በእጁ ምንም ሳይደገፍ ከመቀመጫው ተነሳ፡፡ ክፍሉን ለቆ ወጣ፡፡ እዚህ አላሳይም ቢሉኝም ጎረቤትም ቤቴ ነው፡፡ 

*     *     *

                የጎረቤት ጓደኛ እናት ገና እንዳዩት በጥያቄ አጣደፉት፡፡
                “ተክሉ፣ አባትህ በጎ ናቸው?”
                “ምንም አይልም፡፡
                “የደም ግፊቱ መጠን ቀንሶላቸው ይሆን?”
                “መሰለኝ፤ እስካሁን ይቀንሳል፡፡
                “ጦስኝ ጠጡ ብያቸው ነበር፤ ጠጥተው ይሆን?”
                “--ይ፣ የጠጣ አይመስለኝም፡፡
                “ከነጋ ሄደህ ነበር?”
                “እኔ እንኳን አልሄድኩም፤ እነ እታባ ሄደው ስለነበር ነው፡፡ዝምታ፡፡ የምሽቱን የቴሌቪዥን ዜና በግማሽ ልብ ተከታትሎ ወጣ፡፡

*     *     *

ንጋት ላይ

                የበሩ መንኳኳት ከጣፋጭ ህልሙ አናጠበው፡፡ እየተነጫነጨማነው?” አለ፡፡
                “ለባብሰህ እንሂድ ተክሉ፤ ጋሼ በጎ ማደራቸውን ዓይተው እንመለሳለን፡፡ ፈጠን በል፡፡አሳዳጊው እታባ ነበረች፡፡
                ዐይኑን ጨፈነ፡፡ ድጋሚ ተኝቶ ህልሙን ሊቀጥል ሞክሮ ሳይሳካለት ቀረ፡፡ አንሶላና ብርድ ልብሱን እያተራመሰ ከአልጋው ወረደ፡፡
               
*     *     *

ጠዋት

አባቱ ከተኙበት የግል ክሊኒክ ደረሰ፡፡ ክፍሉ ሁለት የሕሙማን አልጋ ይዟል፡፡ ሰፋ ያለ ክፍል . . . ሁለት አልጋ፣ በአልጋዎቹ መሐከል የአቡጀዲ መክፈያ፡፡
                ዐይኑ የሁለተኛው አልጋ ታማሚን የምታስታምም ቆንጆ ሴት ላይ አረፈ፡፡ በጎን እያየችው ነበር፡፡ ዐይናቸው ተጋጠመ፡፡ እሷ አቀረቀረች፡፡ እሱ አባቱ ላይ አተኮረ፡፡ አላስችልህ አለው፡፡ ዐይኑን መልሶ ወደ ልጅቱ ወረወረ፡፡ እንዳቀረቀረች ነው፡፡ እዚሁ እንዳደረች ያወቀው በተመሰቃቀለው ፀጉሯ እና በአለባበሷ ነው፡፡ ብትኳኳል ምን ያህል ታምር ይሆን? እግዚኦ!
                ወደታማሚው ተጠግታ ስትናገር አዳመጠ፡፡ “. . . ብዘገይም እመጣለሁ፡፡
                ምን ማለቷ ይሆን? ታድር ይሆን? ጉድ ይታያል፡፡
                ለእሱ የልጅቱ ቤተሰቦች እንደሆኑ የተሰሙት ሶስት ሰዎች ወደክፍሉ ገቡ፡፡ከቆይታ በኋላ፣እየሩስ፣ አንቺ ሄደሽ አረፍ በይ . . .”የሚል ድምፅ ሰማ፡፡ እየሩስ ላይ ዐይኑን ሲጥል ድንገት በሚመስል ሁኔታ ዐይኗን ስትወረውር በድጋሚ ተጋጩ፡፡ ቦርሳዋን ካስቀመጠችበት አንስታ ዕቃ እንደዘነጋ ሰው እያንገራገረች አልፋው ሄደች፡፡ ሊከተላት ፈልጎ ነበር፡፡ ምንነቱ ያልታወቀ የስሜት ገመድ አስሮ አቀረው፡፡
                “ዛሬ እኔ ነኝ የማድረው!” አለ፡፡ የተናገረው ለአባቱ ቢሆንም ድምፁ ግን ለሌሎቹም ይሰማ ነበርና ንግግሩ ግርምትን ፈጠረ፡፡
                “አሁንስ ልብ እየገዛ ነውአሉ አክስቱ፤ተመስገን፡፡
                “ገብርኤል ጸሎቴን ሰምቶታልአለች አሳዳጊው እታባ፡፡

*     *     *


አብረው ሲያድሩ ምን እንደሚያወራት ሲያስብ ዋለ፡፡ አስተያየቷ ናፍቆታል፡፡ ቆንጆ እያዩ ማንጋት ጥሩ እንቅልፍ ተኝቶ ከመነሳት የበለጠ እንደሚሆን ገመተ፡፡
                ትተኛ ይሆን? ከክፍሉ ማዕዘን ላይ አነስተኛ የስፖንጅ ፍራሽ አይቷል፡፡ አተኛኘቷ እንዴት ይሆን? አብሯት የሚያድር ሰው መቼስ አይኖርም፡፡ ምን አይነት ሞኝ ነኝ? እስከዛሬ ለምን አልሄድኩም ኖሯል? የመቆጨት ስሜት ዳበሰው፡፡

*     *     *

200 ሰዓት ከምሽቱ

                ለማሸነፍ ወይም ለመሸነፍ ነበር ተዘጋጅቶ የሄደው፡፡ እታባ እሱ እስኪመጣ ስትጠብቀው አገኛት፡፡ ውስጡ ጭር ብሏል፡፡ እየሩስ የለችም፡፡ የምታስታምማቸውም ሕመምተኛ የሉም፡፡ አሳዳጊው ተሰናብታው ልትወጣ ስትል ያዝ አድርጎ፤ለሽንት ወጥተው ነው?” አለና ጠየቀ፣ ልቡ እየመታ፡፡
                “ለቀዋል፤ የግል ክሊኒክ ክፍያ አማሯቸው ዛሬ ከሰአት ለቀቁ፡፡ እስካሁን የገባበት የለም፡፡ በል ደህና እደር፡፡

 ተፈጸመ