ማክሰኞ 14 ማርች 2017

የካህኑ የመጨረሻ ቃል

አንድ ካህን በጠና ታሞ ከተኛበት ሆስፒታል ውስጥ እንዳለ በነፍስ ተይዞ እያጣጣረ፣ አንድ ፖሊስ እና  አንድ ፖለቲከኛ እንዲጠራለት ዶክተሩን አጥብቆ ለመነ።

ከደቂቃዎች በኋላ እንዲጠሩለት የጠየቃቸው ሰዎች ከሆስፒታሉ ተገኝተው ከአልጋው ግራ እና ቀኝ ቆመው ነበር። 

ካህኑ የሁለቱንም እጅ የቀረውን እንጥፍጣፊ አቅም አሟጥጦ ያዘ። ፖለቲከኛው ሰው ግን እጅግ ተጨንቆ ጠየቀው፦

“እኛን ለምን ብለህ እንዳስጠራኸን አልገባኝም። ግን ለምንድን ይሆን?”

ካህኑ ትንፋሹን ሰብስቦ እንዲህ አለ፦

“እኔም ልክ እንደ ኢየሱስ በተመሳሳይ መንገድ በሁለት ወንበዶች መካከል መሞት እፈልጋለሁ ...”

እናም ሞተ !!!!

አባይ ጠባብ መንገድ

(ኄኖክ ስጦታው)

የወንዝ አገሩ መነሻው፤ የወንዝ አገሩ መድረሻው
ወንዝ የሌለበት አገር ነው፣ መውጫ መግቢያው የጠፋው¡
*
የወንዞች ህብር ውጤት፤ የውኆች ስብስብ ጥምር
አባይ ፀሎቴን ስማ፣ ልንገርህ አንዳች ምስጢር።

ወደሄድክበት ውሰደኝ፤ እኔም አፈር ነኝና፣
ከአገሬ አንዴ ከወጣሁ፣ ሌላ ወንዝ አላጣምና።
*
አባይ ፀሎቴን ስማ፣ ከነአፈሬ አብሬህ ልውጣ
ሺህ ቢጎድል ተገድቦ፣ ሺህ ቢሞላ የሚቆጣ
ወንዝ ብቻ እንደሆነ፣ አውቃለሁኝ፤ ታውቀዋለህ!
አብረን ታስረን፣ ነፃ እንውጣ።

ሰኞ 9 ጃንዋሪ 2017

በእንክርዳድ ማሳ ላይ (ስኬች)

(ኄኖክ ስጦታው)

*1*
ስንዴ እና ገብስ እንክርዳድ ተነቅሎ ከተዘጋጀው የማሳ ላይ ተዘሩ።

“ሞተን እየተቀበርን መሆን አለበት ” አለ ገብስ።

“አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” የተባለው ቃል እየተፈፀመ ነው። ሲል ስንዴ መለሰ።

*2*

ጥቂት ዘሮች በወፎች ተበሉ። ብዙዎችም መበስበስ ጀመሩ። መበስበሳቸው የህይወታቸው ፍፃሜ አልነበረም። የሌላኛው ሕይወት ጅማሬ እንጂ።

*3*
የማቆጥቆጥ ዘመን

“እነሆ የመጨረሻው ዘመን ፍሬዎች እንሆን ዘንድ ለፍርድ ተነስተናል።” ሲል አንዱ ስንዴ አጠገቡ ላለው ሌላ ስንዴ ተናገረ።

“አይደለም። ፀድቀን ነው። ዙሪያህን ተመልከት! እኛ ብቻ አይደለንም የፀደቅነው። ከመካከላችን ጥቂት ወንድሞቻችን ፀድቀዋል።”

ገብስ ተናገረ “እኔ ከመሰሎቼ ነጥሎ ከናንተ መካከል እንድበቅል ያደረገው ፈጣሪ ተቆጥቶ ቢሆን ነው።” አለ ዙሪያውን ለከበቡትን ስንዴዎች።

እንክርዳድ ግን ከመካከላቸው ሆኖ“ወዶኛልና አዳነኝ” እያለ ጮክ ብሎ ይዘምር ነበረ።

ሐሙስ 5 ጃንዋሪ 2017

“ጠጣህብኝ”!

አንድ እጅግ ያዘነ ሰው ባር ውስጥ ተቀመጦ ፊት ለፊቱ ያለውን መጠጥ ላይ እንዳተኮረ ሰላሳ ደቂቃ በላይ ቆየ። በዚህ መሐል አንድ ጠጪ ወደርሱ ቀርቦ ጠረጴዛው ላይ ያለውን መጠጥ አንስቶ ሻት አደረገው።

ምስኪኑ ሰው ስቅስቅ ብሎ ማልቀስ ጀመረ። “ተረጋጋ ወንድሜ፣ ለጨዋታ ነው  የጣሁብህ። ሌላ መጠጥ አዝልሃለሁ” ሲል ሊያረጋጋው ሞከረ።

“ነገሩ አልገባህም፣ ዛሬ ለእኔ ሲበዛ በመከራ የተሞላ ቀን ነው። ጠዋት መስሪያ ቤት ስብሰባ ላይ ጥቂት ደቂቃ አርፍጄ ብገኝ አለቃዬ ከስራዬ አሰናበተኝ። ወደ ቤት ለመመለስ መኪናዬን ወዳቆምኩባት ቦታ አመራሁ። በቦታው ግን አልነበረችም። መኪናዬ ተሰርቃ ነበር።  ለፖሊስ አመለከትኩ። እነሱ ግን ምንም ሊረዱኝ እንደማይችሉ ገልፀው አሰናበቱኝ። በጣም እያዘብኩ በኮንትራት ታክሲ ወደቤት ስመለስ ሞባይሌና የእጅ ቦርሳዬን ረስቼው ወረድኩ። ከዚህ ሁሉ መከራ ልታፅናናኝ የምትችለው ባለቤቴ ብቻ ነበረች። እሷም ቤት ስገባ ከአትክልተኛችን ጋር አልጋ ላይ ተኝተው ደረስኩ። ነገሮች ሁሉ ከአቅሜ በላይ ሆኑ። በመጨረሻ ወደዚህ ባር የመጣሁት ራሴን ላጠፋ ነበር። አንተ ግን መርዜን ጠጣህብኝ።”

“የፅኑነት ሥሪት”

(ኄኖክ ስጦታው) 

(ሲያጣሙት ሚጣመም… ሲያቀኑት ሚቀና)
የቆመ ቢመስልም — ፍፃሜው ግን ገና።

ግትር ነው የሚባል — ላመነበት ፀንቶ
ፍፃሜው ላይ ቆሟል — መልመጥመጡን ረቶ።

የ"ፅኑነት'' ትርጉም― ለዚህ ዘመን ድርሻ
ለሟችም ለኗሪም…
አለመታመን ነው — መታመን እያሻ።

አምናለሁ

(ኄኖክ ስጦታው)

አምናለሁ፣
     አምናለሁ፣
              አምናለሁ፣  
                         አምናለሁ
(አምኜ እጥራለሁ)
ጥሬ፣ ጥሬ፣ ጥሬ ፦ እምነት እገነባለሁ።
ስጠረጥር ጊዜ፣ (ሁለት) እንዳለሁ!
ታጥሮ በእምነቴ፣ ንጄው የሚሰፋ
“አንዱ” ራሱ እምነት፣ ሌላኛው ነው “ተስፋ”።
ተስፋ እገነባለሁ፦ እምነት አንፃለሁ፦ ጥላቻን ጠልቼ
(ጥርጣሬን ንጄ፣ እምነትንም ንጄ፣ ሌላነትን ሽቼ)
ማፍረስም መስራት ነው፣ መስራትም ነው ማፍረስ፣ አምናለሁ ተግቼ።

ረቡዕ 4 ጃንዋሪ 2017

“በፍቅር ሥም” ለንባብ በቃ

የደራሲና ሃያሲ ዓለማየሁ ገላጋይ አሥረኛ መጽሐፍ እና አምስተኛው ልቦለድ “በፍቅር ሥም” ለንባብ በቃ