ወና ልብ
ከልቧ ሜዳ ላይ፤
ፀሐይ ወጥታ ብታይ፤
ባልታጠረ ግቢ፣ ባላስከበረችው፤
ቅጥር በሌለው ደጅ፣ ወና በተወችው፤
ውሃ እንዲያነሳላት፣ ቢከረክር ወዳ፤
ስንዴዋን አስጥታ፣ ወደ መንደር ሄዳ፤
ቤቷ ላይጨስበት፣ ላትጐልት ጉልቻ፤
ንፍሮም ላትቀቅል፣ ላትጋግር እንጐቻ፤
"እሽ..." ባልተባሉ፣ ዶሮዎች ተለቅሞ፤
አጋች በሌላቸው፣ እሪያዎች ተቅሞ፤
‘ባፋሽ ባጐንባሹ‘፣ እንዳልነበር ወድሞ፤
በጠበቃት ስጡ፣ ሰርክ ስትገናኝ፤
ከመጅ ከማሰሮ፣ በወግ ሳትሰናኝ፤
በዛለ ጉልበቷ፣ ብቻዋን አራግፋ፤
ከነግሳንግሱ፣ ዳውጃዋን አጥፋ፤
ቀኗ ሊመሽ ሲድህ፣ ስትገባ መጀቷ፤
ቆፈኑ ተሰማው የተራበ አንጀቷ፡፡
/ትዕግስት ዓለምነህ/
ጥቅምት 3 ቀን 2005 ዓ.ም.
Bravo TG !!
ምላሽ ይስጡሰርዝ