አለቃ ለማ ትዝታቸውን ለልጃቸው ለመንግስቱ ለማ(ለአብዬ መንግስቱ) ያጫወቱት ነው ፤ በመምህሩ አፍልሆ ስለተደረገለትና በቅኔ ተወዳዳሪ ስለሌለው አንድ ተማሪ ነው ጨዋታው። መምህሩ አለቃ ተጠምቆ ይሰኛሉ። የተማሪው ስም ሠረገላ ብርሃን የተሰኘ በኋላም የታወቀ የቅኔ አስተማሪ የሆነ ሰው ነው። አለቃ ለማ በጣፈጭ አንደበታቸው ለልጃቸው እየተረኩለት ነው።
“ተማሪያቸው ነው አፍልሆ አርገውለታል ይመስለኛል ተጠምቆ፥ መዳኒት ጸሎት በውሃ እሚደግም - ለቅኔ ብቻ አይደለ፤ ለዜማም ለመጣፍም እንዲያው ለሚጠናው ሁሉ ነው። በውሃ ስለተደገመ ነው አፍልሆ የተባለው. . . እገሌ ሰው ያህለዋል አይባልም ቅኔ በማሳመር - ቅኔው ሌላ ነዋ ባያሌው። ሲመራ! ወዲያው መምራት ነው። አራት ተማሪ አቅርቦ ይመራል የሚባለው እሱ ነው። መምህር ሆኖ፤ . . . እሱን እንዲህ ያደረገው አለቃ ተጠምቆ ናቸውና እኔም እንደሱ እሆናለሁ ብዬ ተነስቼ ሄድኩ ኸሳቸው። . . .” (መፅሐፈ ትዝታ ዘዓለቃ ለማ፤ ገፅ 79)
ስለ አብሾ (አፍልሆ) በቃል የተናገሩት ሊቀ ጉባኤ ፈቃደ ስላሴ ተፈራ ናቸው። አያሌ ጥያቄዎችን የሚመልስና ብዙ ጥያቄዎችን የሚያጭር መረጃ ሆኖ ለዚህ ዕሑፍ የጀርባ አጥንት ሆኖኛል። “በአገራችን የቤተክርስቲያን ምሁራን ዘንድ ትምህርት ይገልፃል፥ አእምሮ ይስላል እየተባለ በልዩ ልዩ ሁኔታዎች ተቀነባብሮ በተለያየ የእድሜ ደረጃ ላሉ ተማሪዎች የሚሰጥ መድሃኒት ሲሆን በተጨማሪ “ዘኢያገድፍ” እንዲይዝ የማይጥል፣ “መክሰተ ጥበብ” እና “መፍትሄ ሀብት” እየተባለ ይጠራል. . .” ሲሉም አክለውም ስለ አብሾ ምንነት ያብረራሉ።
ይህ ገለፃቸውን ለሚመረምር ሰው የአብሾን ጥቅም ከዕውቀት ገላጭ ከመሆኑ ጋር ብቻ እንዳልሆነ ይረዳል። የመጀመሪያው ደረጃ መድሀኒት “ዘኢያገድፍ” ተብሎ የተገለፀው በቤተክህነት ትምህርት ፊደለም ሆነ ቅኔ ለሚገድፉት የሚሰጥ ሲሆን የሚማሩትን በቃላቸው ቶሎ እንዲይዙ (እንዳይጥሉ) የማድረግ አቅም ያለው መድሃኒት እንደሆነ ግልፅ ነው። ሌላኛው “መክሰተ ጥበብ” የሚሰኘውም የቃላቱ ትርጓሜ እንደሚነግረን ጥበብ ገላጭ እንደሆነ ያመላክታል። ይህም ከዕውቀት አንድ ደረጃ ከፍታውን ወደ ጥበብ የሚያሳድግ መድሃኒት ነው። ሶስተኛው “መፍትሄ ሀብት” ነው። ለነዋይ ማካበቻ ይረዳል ተብሎ የሚሰጥ መድሃኒት እንደሆነ ተረድቻለሁ።
[በተለይም የአብሾ አፍልሆ ለቅኔ ዘረፋ እድሜ ልክ የሚያነቃቃ አብነት ነው። እየተባለ ይጠጣል። በቃልም፥
ጠላ ያለጌሾ
ቅኔ ያለአብሾ . . . እየተባለ ይተረታል። አብሾ ሶስት አይነት ዝርያ ሲኖረው ጥቁር፥ ቀይና ነጭ ናቸው። ጥቁሩ በአገራችን በየትኛውም ቦታ በቅሎ የሚገኝ ሲሆን አስተናግር ተብሎ የሚታወቀውም ጥቁሩ ነው። (አብሾ የተሰጠው ተማሪ) . . . የሚነገረው ትምህርት የማይጠፋውና የሰማውን ነገር የማይረሳ ከሆነ ሆሳዕናው (መድሃኒቱ) ሰመረለት ይባላል። ካልሰመረለት የርኃወተ ሰማይ ቀን ጠብቆ እንደገና ይደረግለታል እየተባለ ይነገራል። (ርኃወተ ሰማይ የሰማይ መከፈት ነው) ይኸውም የሚሆነው በአመት አራት ጊዜ ሲሆን ጳጉሜ 3፥ ታህሳስ 13። የካቲት 4 እና ግንቦት ስምንት ቀን ነው። ]
ጥንታዊው የቤተክህነት መፅሐፍት መካከል፣ “ፅፀ ደብዳቤ” አንዱ ነው። በጥንታዊ አባቶቻችን በመድኃኒቶች ላይ የነበራቸውን ጥበብ በአውደ ነገሥት ላይ ሰፍረው ይገኛሉ። ከእነዚህም መድኃኒቶች ተራ ቁትር 56ኛው አብሾ (አብሶ) በሚል ስም ተጠርቷል። ስለሆሳእናው (መድሓኒቱ) ምንነት እና አድራጎት፣ በባህላዊና መንፈሳዊ ህክምና ጥበብ አማካኝነት ትምህርት ለማይዘልቀው ልጅ ሁነኛ መድሃኒት እንደሆነ እንዲህ ሲል ይገልፀዋል፦
[፶፮፤ አብሶ (ዕፀ ፋርስ አስተናግር) በበርኻ የበቀለ ነጩ ፍሬውን ደቍሶ በነጭ ሽንኵርት ብቻ በተደለዘ በርበሬ ሽሮ በነጭ ጤፍ እንጀራ እየፈተፈቱ መልክአ ኢየሱስን እየደገሙ ፯ ቀን ለክተው ለሕፃናት ቢያበሏቸው ትምህርት ከመ ቅጽበት ይገባቸዋል ፍቱን ነው። እንዲሁም ከመ ዘኢያገድፍም ፫ ቀን ጠዋት ጠዋት ማዋጥ ነው።]
ሊቀ ጉባኤ ፈቃደ ስላሴ ተፈራ ስለ መድሃኒቱ አዘገጃጀት ሰፋ ያለ ትንታኔን ሰጥተዋል።[“. . .የሚዘጋጀውም ከልዩ ልዩ እፅዋት ቅጠል፥ አበባ፥ ስርና ተቀፅላ በመሆኑ በማር ወይም ንፁህ ማር ወፍ ባልቀመሰው ውሃ (በጠዋት በተቀዳ ውሀ) በሞላ ብርሌ (በጥቁር ብርሌ) ውስጥ እስከ አንገቱ ውሃ ተሞልቶ ከተበጠበጠ በኋላ ለማፍሊያ የተዘጋጀ ፀሎት እየተፀለየበት አንድ ሱባኤ ይቆያል። እስከ ሰባት ቀን ይሰነብታል። ሱባኤው ሲያልቅ በሰባተኛው ቀን ተጠቃሚው ልጅ ወይም ደቀመዝሙር በባዶ ሆዱ ይጠጣዋል። ወዲያው እንደ ጠጣ ከሰው ተለይቶ ለሶስት ቀናት ብቻውን በአንድ ክፍል ውስጥ ይታቀባል/ ይቀመጣል። ከዚያም ለአንድ ሱባኤ ወይም ለሰባት ቀናት አልያም ለሰባት ሱባኤ ወይም ለአርባዘጠኝ ቀናት የተወሰኑ ምግቦችን እየበላ ማለትም የገብስ ቆሎ ፥ የገብስና የጤፍ እንጀራ በኑግ ጭማቂ በማጥቀስ እየበላና የኑግ ጭማቂ ብቻ እየጠጣ የሚያጠናውን ንግግር በማሰላሰል እንዲቆይ ምክር ይሰጠዋል። አደራረጉ የተለያየ ከመሆኑም በላይ የሚቀመሙትም እፅዋት እንደየመምህራኑ ጥናትና እንደየገቢሩ የተለያዩ ናቸው ይባላል. . .”]
መዛግብት ይህንን ቃል በምን መልኩ አንደፈቱት ተመልክቼ ነበር። አብሾ የመድሃኒት ስያሜ ሲሆን የተለያዩ አይነት አእምሮን አነቃቂ እፆች አማካኝነት ተቀምሞ ለመፍትሄነት ሲያገለግል የኖረ ጥንታዊ መድሐኒት እንደሆነ ይናገራሉ። ከኢትዮጵያ ውጪ የጥንት ስልጣኔ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ በሆኑት ሩቅ ምስራቅ አገራትም ውስጥ ተመሳሳይ መድሀኒቶች እንዳሉ ይታወቃል። በቻይና፣ በሕንድ እና በጃፓን እውቀት ገላጭ፣ አእምሮን አብሪ የሆኑ ባህላዊና መንፈሳዊነትን ያጣመሩ ተመሳሳይ መድሃኒቶች እንዳሉ ጥናቶች ያረጋግጣሉ።
በቤተክርስቲያን ውስጥ ተወስኖ ስላለውና እንብዛም ጥናት ባልተደረገበት “አብሾ” ዙሪያ በቃልና በፅሁፍ ያገኘኋቸውን መረጃዎች ተቀነጣጥበውም ቢሆን ሰፍረው ይገኛሉ፤ ከነዚህም ውስጥ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ በመዕሀፈ ሰዋሰው አስተናግር ወይም ዕፀ ፋርስ አናግር አስለፍልፍ ስለሚሰኘው ዕፅ ምንነት ሲያብራሩ፥ ‘የቀመሰው ሰው ወደ ፊት የሚሆነውንና የሚያገኘውን ስለሚያናግር አስተናግር’ እንደሆነ ይጠቁሙናል።
ደስታ ተክለወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት በተሰኘው መፅሐፋቸው ስለ ዕፁ
[ዕጠ፡ ፋርስ] ተመሳሳይ ሐሳብ አስፍረው አንብቤያለሁ። [የፍሬው ልብስ እሾህ ያለበት ተክልነት የሌለው የዱር እንጨት፤ ቅጠሉን በጎች ቢበሉት ራሳቸውን ያዞራል፤ ሰውም ቢቀምሰው ያሳብዳል። ባላገሮችም ዐጤ ፋሪስ ይሉታል። ይህ ሁለት አይነት እንጨት ባገዳ በቅጠል በፍሬ ልዩ ሲሆን ልብን በመንሳት ስለተባበረ ባንድ ስም ተጠራ። በካህናት ዘንድ ግን ሁለተኛው ከአንደኛው ተለይቶ አስተናግር ይባላል። ]
በቤተክህነት አካባቢ ያሉ አንድ አባት ስለ አብሾ ምንነት እንዲነግሩኝ ጠይቄ ነበር። “ፍሬውን የቀመሱ ሁሉ ባለብሩህ አእምሮ ይሆናሉ። ትምህርት ገላጭ ነው። ትንቢትም ያናግራል። በጥንቃቄ ካልተደረገ ለእብደትና ለሞት የሚያበቃ ስካር ውስጥ ይጥላል” ሲሉ ሃሳቡን አጠናክረውታል።
በተለምዶ አብሾ (አብሶ) ተብሎ የሚጠራው አንዱና ዋንኛው አድራጎታዊ መገለጫው ሲሆን አስተናግር ከተሰኘ ዕፅ ይቀመማል። አድራጎት አፍልሆ ተብሎ ይጠራል። በአንድ ቀን የሚፈላ አፍልሆ አለ ይባላል። የዚህም ቅመማ ከላይ እንደተገለፀው ሆኖ በተጨማሪም ዛጎል ተደቁሶ ይጨመርበታል። ዛጎል ፀሎት የሚደረግበትን መድሃኒት ቶሎ የማፍላት ሃይል ስላለው እለቱን እንዲፈላና እንዲገነፍል ያደርገዋል። እንደ ፈቃደ ስላሴ ተፈራ አባባል ከሆነ የዚህ አይነቱ አፍልሆ (ዛጎል የገባበት) ጥሩ እንዳልሆነ ሲነገር ሰምተዋል። ተማሪዎች ቅጠሉን አፍልተውና ከጤፍ እንጀራ ጋራ ፈትፍተው በቀመሱት ጊዜ አእምሯቸውን ለውጦ ማደሪያቸውን ያናጋል፤ ማርከሻውም የኑግ ልጥልጥ ወይም በሶ እንደሆነም ያምናሉ።
ቀዩ በቆላማ ቦታዎች አካባቢ በሚፈስ ወንዝና ወንዝ መጋጠሚያ ላይ ይገኛል። ነጩ አብሾ ከጎንደር በበሸሉና አባይ መጋጠሚያ በጎጃም በዚገም ወንዝና በአባይ መጋጠሚያ፥ በሸዋ በሙገርና በአባይ ወንዝ መጋጠሚያ ይበቅላል ሲሉ ፈቃደ ስላሴ ተፈራ ስለፍሬዎቹ አይነትና ጥቅም፣ ብሎም ጉዳት ጠቁመዋል። ከፍሬዎቹም ዓይነቶች ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉት ቀዩ እና ነጩ ብቻ እንደሆኑ ይነገራል። አጠቃቀሙም የተለያየ ነው። አንዳንድ መምህራን ስለአብሾ መድሀኒት ሲናገሩ አብሾ ጠጥቶ ወይንም በልቶ እስከ አርባው ቀን አልክሆል መጠጥ መቅመስ ሰካራም ያደርጋል ይላሉ። ነገር ግን አርባው ቀን ካለፈ በኋላ አልኮል ቢጠጣም ምንም ጉዳት እንደማያስከትል ይናገራሉ። በተለይ አደራረጉን የማያውቁ መምህራንም ሆኑ ተማሪዎች ወይም ግለሰቦች አብሾ ጠጥተው ወይም አጠጥተው ወዲያው አልኮል ስለሚጋቱ ሰካራሞችና አልፈው ተርፈውም እብዶች ይሆናሉ።
“የአብሾ ነገር ሲነሳ አንድ ትዝ የሚለኝ ነገር አለ” ባሉት የሕይወት ገጠመኝ በሳቸው አንደበት እንዲህ ይተረካል፦
[በ1953 ዓ.ም በነሀሴ ወር በጎጃም ክፍለሀገር በደጋ ዳሞት አውራጃ ዋሸራ የቅኔ ትምህርት ቤት በነበርኩበት ጊዜ 3 ሰዎች አብሾ ሲጠጡ ጠብቀን ብለው እኔንና ጓደኛዬን ዛሬ የቅኔ መምህር ማሞ ሀብተ ማርያምን ከዋሸራ በግምት 15 ኪሎሜትር ርቆ በሚገ/ነው በአካባቢው ሰው በሌለበት በዮሀንስ ገዳም ወስደውን በአንድ ሰፊ ደጀ ሰላም ውስጥ ገብተን ሳለ ቀኑ መሸት ሲል አብሾውን በስንዴ ዳቦ ጋግረው ሶስቱም ከበሉ በኋላ በሩን በጥብቅ ዘግተን ፀሎት ጀመሩ። ከዚያ ፀሎቱን እየፀለዩ ለሁለት ሰአት ያህል እንደቆዩ አንዱ እሪ፥ እንሽሽ ያለንበት ቤት ተቃጥሏል አለና ውሸቱን አስተጋባ። ወዲያው ለመሸሽ ከግድግዳ ጋራ እየተላተመ ስለአስቸገረ እኛ እና ሁለቱ ያልሰከሩ ጓደኞቹ ከአንድ ወጋግራ ላይ በገመድ አሰርነው። ወዲያው ሁለተኛው ተማሪ አንዳንድ ትንቢት ብጤ ሲናገር ቆይቶ “ሸማ ስራዬን አላሰራ አላችሁኝ፥ ቁቲቴን ስጡኝ” እያለ ስላስቸገረን እንደፊተኛው ከአንድ ወጋግራ ላይ ሸብ አደረግነው። ወዲያው የቅዳሴ ዜማ እንደጀመረ አንቀላፋ። ሶስተኛወ ግን ስካር እንደጀመረው “ተው ና ውረድ ቡሬ” እያለ የአራሽ መሰል ንግግሩን ጀመረ። ከዚያም ቀጥሎ
የበሬው ውለታ ይገለፃል ማታ
እብቁ በግርግብ ውሃው በገበታ።
እያለ ሲያዜም ቆይቶ እንቅልፍ ወሰደው። ከዚያ በኋላ መጀመሪያ የሰከረው ሰው የቅኔ ዘረፋውን ቀጥሎ ዶሮ እስኪጮህ የጀመረ እስኪነጋ ድረስ እጅግ በጣም ብዙ ቅኔ ድርሰቶችን ሲደርስ አድሯል።
ከዚያ በኋላ ሶስቱ እንቅልፍ ወስዷቸው ቀኑን ከዋሉ በኋላ ሌሊቱን አድረው በሶስተኛው ቀን ሙሉ አእምሯቸው ተመልሶላቸዋል፥ አንዳንድ ጊዜ ሲገላበጡ እየጠራን እህል ውሃ እነዲቀምሱ ስንጠይቃቸው በጣም ይበሳጩ ነበር። የታሰሩትን ፈትተን ልብሳቸውን ሲጥሉ እያለበስን አስተኝተን ተራ በተራ ያለምንም ድንጋጤ ስንጠብቅ ሰንብተናል። ከዚህ ውስጥ አስገራሚው ሁኔታ ሰካራሞቹ እኛን ለመደብደብ አልሞከሩም። ስንቆጣቸው ቶሎ ደንግጠው ትእዛዛችንን ይቀበሉ ነበር።]