የመጽሐፍ አዟሪዎች ቅሸባ ይቁም!
-
-
-
መጽሐፍት መደብር ሄደው መግዛት ለማይችሉ አንባቢያን አመቺ የገበያ አማረጮች ናቸው ፤ የመጽሐፍት አዟሪ ነጋዴዎች፡፡ እንደአነሳሳቸው መልካም ነበር፤ ብዙ መጻህፍትንም ገዝቻቸው አውቃለሁ፡፡ “ቅሸባቸው” እንዲህ አፍጥጦ ሳይመጣ በፊት ነው ታዲያ፡፡ የመጽሐፉ መሸጫ ዋጋ እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት የማስመሰል ጥበብ 35 ብር የሚለውን ወደ 85 . . . .10ብር የነበረውን 40ብር፣ ባስ ካለም 100ብር የሚለውን 400 ብር በማድረግ የራሳቸውን የዋጋ ተመን አውጥተው እየተንቀሳቀሱ ያሉ ነጋዴዎች ጥቂት አይባሉም፡፡ በደራሲዎቹና አሳታሚዎቹ በወጣላቸው የዋጋ ተመን በቀላሉ ሊሰራጩ እና ሊነበቡ የሚገባቸው መጻሕፍት በዋጋ መፋረስ ምክንያት ብቻ ተደራሲ ጋር አለመድረሳቸው ትልቁ ችግር እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ዋናው ጥያቄ “መፍትሔው ምንድን ነው?? ምን መደረግ አለበት????”
አንዳንድ መጽሐፍ አዟሪ ነጋዴዎችን
ባገኘሁት አጋጣሚ “ለምን ትክክለኛውን የዋጋ ተመን ተጠቅማችሁ አትሸጡም? ለምን ዋጋ ትጨምራላችሁ??” ብዬ ጠይቄ ነበር፤ መልሳቸው
ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው ፤ “ ሰዉ ስለሚከራከር!” የሚል፤ ኧረ ምን ተሸለ?? ቁርጥ ዋጋ ድርድር አያሻውም፤ በተጻፈው የዋጋ
ተመን መገበያት ካልቻለ ዋጋ ማሻቀብ ወይም መቀሸብ ፋይዳው እስከምን ድረስ ነው???
የመጽሐፍ አዟሪ ነጋዴዎችን መኖር እደግፋለሁ፡፡ ከሚነግዱት መጽሐፍ የሚያገኙት ትርፍ አነስተኛ እንዳልሆነም እረዳለሁ፡፡ አንድ መጽሐፍ አሳታሚ ለመጽሐፉ ማሳተሚያ ብቻ የሚያወጣው ገንዘብ ከመጽሐፉ ዋጋ አንጻር ሲሰላ ከ50% ያላነሰ ወጪ አለው፡፡ ይህ ወጪ መጽሐፉ ለሕትመት ቅድመ ዝግጅት የሚያወጣውን ብር አይጨምርም፡፡ /ቅድመ ዝግጅቱ ከሽፋን ምስል እስከ ጽሑፍ ትየባ ብሎም እስከ አርትኦት ይጓዛል/ ፡፡ ከባዱ ወጪ እና የትርፍ ክፍፍል ሂደት የሚያመራው ወደ መጽሐፍ አከፋፋዩ ሲያመራ ነው፡፡ አከፋፋዩ ከመጽሐፉ ዋጋ ላይ በጥቂቱ 35% ይቆርጣል፡፡ /በቀላል ሂሳብ ሲሰላ . . . የ40ብር መጽሐፍ ላይ አከፋፋዩ 14ብር ይቆርጣል፡፡ 14ብሩንም ከመጽሐፍ አዟሪው ጋር የሚካፈለው ይሆናል/ ፡፡ የአዕምሮ ባለንብረቱ እና አሳታሚው ጥቅማቸው ምን ያህል ነው??? ይህ ጥቅማቸውንስ እንዴት ነው የሚያገኙት?
የእጅ በእጅ ሽያጭ በመጽሐፍ ነጋዴዎች ዘንድ የለም ለማለት እደፍራለሁ፡፡ እና ምንድነው ያለው?????? “ኮንሳይመንት” አንዱ እና ባመዛኙ ገበያው የሚመራበት የቅብብል መንገድ ነው፡፡ ሲሸጥ የሚከፈል እንደማለት ነው/እዚህ ላይ ከተሳሳትኩ አርሙኝ/፡፡ አሁን ባለንበት የገበያ ስርዓት ደግሞ ፣ ደራሲው እንደ አሳታሚም ሆኖ ብቻውን የሚባክንበት ነው፡፡ ከኪሱ አውጥቶ ያሳተመውን መጽሐፍ ሽያጭ ትርፍና ኪሳራውን እንዳይለይ ከሚያደርጉት ትልቅ ችግሮች ዋንኛውም ስርዓት ይሄው “ሲሸጥ የሚከፈልበት” ግብይት ነው፡፡ አሁን ደግሞ እንዳይሸጥ ትልቅ እንቅፋት ተደንቅሮበታል፡፡ ችግሩም ግልጽ ነው፡፡ ከተመን በላይ ዋጋ የሚሸቅቡ ነጋዴዎች፣ ተሸጦ በሚከፈለው መጽሐፍ ላይ የራሳቸውን ዋጋ እየለጠፉም ሆነ እየቀሸቡ ችግሩን አባብሰውታል፡፡ ነገሩ ግልጽ እና የአደባባይ ዝርፊያ ከመሆኑም በላይ ድክድክ ለሚለው የአሳታሚው ዘርፍ እና ተቸግሮ በሚያሳትመው ጸሐፊው ላይ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖበታል፡፡
አዟሪዎቹ ሕጋዊ እንዲሆኑ ወይም ሕገወጥ የዋጋ ቅሸባ እንዲቆም ጉዳዩ ይበልጥ የሚመለከተው
አካል /የኢትዮጵያ ደራሲያን ማሕበር / ምን አይነት እንቅስቃሴ አድርጓል/ … ሌሎች መሰል
ተቋማትስ ምን እየሰሩ ነው?
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ