ሙሉውን ለማንበብ |
አደፍርስ - የብዕር ጠብታ
(ከባለፈው የቀጠለ)
ቅንጣቢ ዳሰሳ
፡-ሄኖክ ስጦታው
******
****** ****** *****
አደፍርስ የብዕር ጠብታ ነው፡፡ የጥበብ መታያ - የእውነት መገለጫ ነው፡፡ ድብቅ
ሰብእና የለውም፡፡ የገፀ-ባህሪው ውስጠ ምስል ግልፅነት የተከተለ ነው፡፡ የአገራችን ደራሲያን ለዋና ገፀባህሪይ ነፃነት ለመስጠት
የሚጠቀሙበት ተመሳሳይ የአሳሳል ስልት በአደፍርስ ላይ መስተወሉን ልብ ይለዋል፡፡
“ቀልድ ጨዋታ የማላዘወትር፣ የተሰማኝን ሃሳብ ያስቀይማል አያስቀይምም ብዬ ሳላስብ
ቀጥታ መግለፅ የምወድ…” ገፅ129 እያለ እራሱን የገልጸዋል፡፡ ከደራሲው አንፃር ስለ አደፍርስ ግልፅ ባህርይ የነገረናል፤ “የማይቦዝን ፣ ስለውጤቱም እምብዛም የማያስብ፣ እንደልቡ የሚናገር፤
ተቃዋሚዎቹም ከራስ ፀጉሩ የበዙ ናቸው…”
ዳኛቸው ወርቁ ለአደፍርስ እንደልቡ የመናገር ነፃነትን በመስጠት፣ የራሱን ነፃነት
እንዳወጀ እናስተውላለን፡፡ እውነታውም ይህ ነበር፡፡ የወቅቱን ስርአት፣ ስርአቱ ለዘመናት የፈጠረውን ተፅዕኖ፣ ጭቆና እና ብዝበዛ
ብሎም አጉል ልማዶችን በአደፍርስ አማከኝነት አውግዟል፡፡ በደራሲው ውስጥ አደፍርስ አለ፤ በአደፍርስ ውስጠም ደራሲው ፡፡
መጽሐፉ፣ በተማረው እና ባልተማረው ማህበረሰብ መሀል ለውን ለውጥ ያሳያል፡፡ ስለመሀይምነት
መጥፋት ያትታል፡፡ አደፍርስ ለኢትዮጵያ ያለውን ብሩህ ተስፋ ትምህርትን
አስታኮ ይናገራል፡፡ መዕራፍ 26 ለዚህ ዋቢ የሚሆን ነው፡፡ የምዕራፉ ውይይት አደፍርስ በመጨረሻዎቹ ምዕራፍ ለያዘው ሥራ መጠቆሚያም
ጭምር ሆኗል፡፡
“ሀዲስ” እና “አደፍርስ”
አደፍርስ በዓሉ ግርማ የደረሰው “ሀዲስ” ረጅም ልብ ወለድ ዋና ገፀ ባህርይ ሀዲስ ላይም የባህርይ
ተፅዕኖ ያሳደረ
ይመስላል፡፡ የሀዲስ እና አደፍርስ እንቅስቃሴ የወቅቱ
መንፈስ ታትሞባቸዋል፡፡ ሀዲስ መስቀል መሳለም ይሸሻል፤ አባቱ ግን ቄስ ናቸው፡፡ አደፍርስ ፀበል ይሸሻል፤ የወጣበት ማህበረሰብ ግን የፀበልን ፈዋሽነት አጥብቀው ያምናሉ፡፡ /ደራሲው የአደፍርስ ጤንነት
ተደራሲው እንዲጠራጠር ፣ ሽፋን የመስጠት ዘንባሌን ለመፍጠር የሞከረበት ብልሃት ነው/ ፡፡ ሀዲስ እምነቱ “ሕይወት” እንደሆነ ይናገራል፡፡ የሚያምንበት ሀይማኖት እንደሌለ አስረግጦ፡፡
ለአደፍርስ እምነት ማለት “እውነት” ነው፡፡ አሁንም ሀዲስ “ኢትዮጵያ ታበጽሕ ኢደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር” የሚለውን ጥቅስ አይቀበለውም፡፡
አደፍርስም በገፅ 101 ላይ “ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” የሚለውን ጥቅስ አጥብቆ ሲቃወም እናያለን፡፡
ሀዲስ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆች የከብት ጭራ እየተከተሉ ሲቀሩ ዝም ማለትን አይሻም፡፡ በአንፃሩ ትምህርት ቤት ለማሠራት ደፋ ቀና
ይላል፡፡ አደፍርስም በገፅ 165 ላይ በእረኝነት ሕይወት የከብት
ጭራ ተከትሎ ትውልድ እንዳይቀር መስኖጌ /የከብት ማቆሚያ/ መሠራት እንዳለበትና እረኛው እንዲማር የሚደረግበትን ብልሃት ያሰላስላል፡፡ የበዓሉ ግርማ “ሀዲስ” እና የዳኛቸው ወርቁ “አደፍርስ” አንድ የሚያደርጋቸው
አብይ አላማ አለ፡፡ እሱም ለውጥ! ነው፡፡
የሁለት ባህርያት አንድነት፣ የሁለት መጻሕፍት የጭብጥ ተመሳሳይነት እንዳለ ሆኖ
ቅርጽ ላይ ግን ከፍተኛ ልዩነት ፈጥረዋል፡፡ በዓሉ ግርማ “የህሊና ደውል”/1966ዓ.ም/ በሚል ስያሜ ያስነበበንን መጽሐፍ፣ የይዘት እና ቅርፅ
እድሳት ተደርጎለት በ1975ዓ.ም “ሀዲስ” ተብሎ መታተሙ ይታወቃል፡፡
በሀዲስ እና አደፍርስ ውስጥ ያሉ የአላማ ተመሳሳይነትን እንመልከት፡፡
ሀዲስ “የድንቁርና ዛፍ” የሚለው የአምልኮ ዛፍ በሀዲስ ረጅም ልብ ወለድ መጽሐፍ ውስጥ ገዝፎ ይታያል፡፡ ለውጥ ፈላጊው ሀዲስ “ይህ ዛፍ መፈንዳት አለበት!”
ብሎ ሲወስን ዛፉ የበቀለበት ቦታ የእውቀት ቤት እንዳይሠራ እንቅፋት ሆኖበት ነው፡፡ ዛፉ ተምሳሌት ነው፡፡ ታሪክ ሆኖ የቀረው ጥንታዊ
እውቀታችን ላይ የበቀለ ዛፍ፡፡ ለዘመናት ሥሩን ሰዶ የዘለቀ ዛፍ፡፡ የሚፈራ፣ የሚመለክ ዛፍ፡፡ ዘሩን ከሰለሞናዊ የዘር ግንድ የሳበው ዛፍ ከንጉሣዊ አገዛዝ ሥርአት ጋር ያለውን
ተዘዋዋሪ መልእክት ያስተውሏል፡፡ ይህ ዛፍ ካልወደቀ እውቀት አይኖርም፡፡
የወቅቱ ስርአት ፣ ወግ፣ ባህል እና አስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልጋቸዋል ብለው በአንድነት
እንደቆሙ ታናሽ እና ታላቅ ወንድማማቾች ይመሰላሉ፡፡ አደፍርስ እና ሀዲስ፡፡
የ“እጅ መንሻ” ስነስርአት አደፍርስ በፍፁም አያምንም፡፡ የመረረ ተቃውሞውንም አሰምቷል፡፡ “ልማድ ልተውህ
ቢሉት የት ይተዋል…?”
ከሚሉት ወ/ሮ አሠጋሽ ጋር ይጋጫል፡፡ በአስተሳሰብ፡፡ ወ/ሮ አሸጋሽ እግራቸውን የሚስምላቸው ሰው ከሌለ ሕይወት መጓዟን እንዳቆመች
የሚደመድሙ ናቸው፡፡ አደፍርስ መቅረት አለበት የሚለውን “ወግ” ከቁብም አይቆጥሩ፡፡ ይበልጥ ግን ያጠናክሩታል፤ በተለይ ስለራሳቸው
ክብር የእግር መሳም ጠቀሜታ ሲናገሩ፡-
“… እንደ እህል እና ውሃ አስፈላጊ ነው፡፡ ያለእሱ ለመኖር አይችል
ህዝቡ…” ገፅ 208
ለክብሩ ከፍተኛ ቦታ ይሰጥ የነበረው ክፍል በወ/ሮ አሠጋሽ በኩል
ይታያል፡፡
መጽሐፉ ጥሉቅ ምጡቅ መልእክትን አጭቆ ይዟል፡፡ ምዕራፋት በተቆጠሩ
ቁጥር ይበልጥ ውበት ይረጭበታል፡፡ ጠጣር ቋንቋዎቹ፣ የገፀ ባህርይ
አሳሳሉና የመቼት አገላለፁ መለያዎቹ
ናቸው፡፡ ለአላማው ስኬት ፣ ለአላማው ፅናት እንባ የማይሸረሽረው አደፍርስ ለቆመለት አላማ ውልፍች አይልም፡፡ እናም አደፍርስ ብዙ
ነው፡ ግን አንድ፡፡ አደፍርስ አንድ ነው፤ ግን ብዙ - የብዕር ጠብታ፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ