ማክሰኞ 9 ኦክቶበር 2012

ለፈጠራት ፀፀት / የትዕግስት ዓለምነህ ግጥም


ለፈጠራት ፀፀት
በሚርመሰመሰው፣ የጥምቀት ታዳሚ፤
የሻሞ እንደሚሏት፣ እንደጣሏት ሎሚ፤
እንደመያዝ ያህል፣ እድል ለሷ ጠባ፣
አይታ ትቀራለች፣ እምነትና ተድላ፤
አለም ግሳንግሷን፣ በእሷው ላይ ቆልላ፡፡
ፍቅሯ እንደ ትልቅ ወንዝ፣ ቢሆንም ፍጥረቷ፤
ገባሮቿ አቅመ ቢስ፣ ሆነው ለህይወቷ፤
መች ሲሻገር አየች፣ ኩራቱ ከመኸር፤
በጋው ሲያብት ጠፋ፣ እንኳን ሊገማሸር፡፡
በአህያ ቆዳ፣ ፍቅሯ በሩን ዘግቶ፤
ከሃዲ ጅብ ሲጮህ፣ ዛሬም አቅሉን ስቶ፤
ልቧን ያዘርፋል፣ ሳይንኳኳ ከፍቶ፡፡
በጨረቃ ‘ሚደርቅ፣ በምራቅ የሚርስ፤
.............................. ሁሉም ስሜተ ስስ፤
መሆኑን እያየች፣ የአርባ ቀን እጣዋ፤
እያለቁ ማማር፣ እየጠፉ መድመቅ፣ ተምራ ከፀሐይዋ፤
ሲጠሏት አፍቅራ፣ ሲከዷት ታምናለች፣ ልቧ በተራዋ፡፡
እሷስ በወደደች.........
ደጋግማ ብትግተው፣ እምነቷን በጥብጣ፤
ከደሟ ቢዋረስ፣ ብትወልደው አምጣ፡፡
ሳይሏት ከጫፍ መጥታ፣
ሳይሰጣት በልታ፣
ሳትመረቅ ወጥታ፣
......................... ሜዳ የቀረችው፤
የአይኖቿን ጓዳ፣
በእምባ ምንጣፍ ጋርዳ፤
እንደ ልቧ ሳታይ፣ ያልሸኘችው ፈቅዳ፣
....................... መቼ አሳዘነችው፡፡
ብቸኝነት ጥዳ፣
ትዝታን ቆስቁሳ፣
...................... ወና ልብ ማማሰል፤
እንደ ገበታ ውሃ፣
ስትል ወዲህ ወዲያ፣
..................... ላታርፈው መዋለል፡፡
ፀፀት ባልተለየው፣ ውልደቷ እምነት ባጣ፤
ውሎዋ በክህደት፣ በፍቅር በተቀጣ፤
ኑሮዋ አጋር አጥቶ፣ ከስቶ በገረጣ............
እድሜ አለሟ በቅቶ፣ እሷ የሞተች ‘ለት፤
የፈጠራት ጌታ፣ ምን ያህል ይፀፀት?
“ኢየአምር አነ ዕለተ ሞትየ”

ምንም አስተያየቶች የሉም: