2012 ኦክቶበር 17, ረቡዕ

የሼህ ሁሴን ጅብሪል ትንቢታዊ ግጥሞች


ሼህ ሁሴን ጅብሪል

በሙሉ ግጥሙን ለመመልከት [PDF]
ሼህ ሁሴን ጅብሪል በወሎ አካባቢ በአፈታሪክ በስፋት የሚታወቁ ሼህ ናቸዉ። የተወለዱት በወሎ ክፍለ ሀገር በወረሄመኖ አውራጃ፣ በባዙራ ምክትል፣ በባሆች ቀበሌ፣ ልዩ ስሙ እምበለ ሴዳ ተብሎ በሚጠራ ቦታ በ1811 ዓ.ም ገደማ እንደነበርና 1908 ዓ.ም በተወለዱ በ97 ዓመታቸው ማረፋቸዉ ይነገራል።

ሼህ ሁሴን ጅብሪል መፍረድ የጀመሩት ገና በሰባት ዓመታቸው እንደነበርና የሚናገሩትም መሬት ጠብ የማይል እንደነበር ይነገርላቸዋል። አሐዱ ወይም ቢስሚላሂ ብለው ፍርድ የጀመሩት ደግሞ በአጼ ዮሐንስና መምሬ ግርማ በተባሉ ቄስ ነበር ይባላል። የሗላ ሗላ ግን ወደፊት የሚሆነውንና የሚመጣውን ከነመፍትሔው ጭምር በግጥም ይተነብዩ እንደነበርና በዚህም ምክንያት ነገሥታቱም፣ መሳፍንቱም፣ ትንሹም ትልቁም እሳቸውን መጀን ማለት እንደጀመሩ ይነገራል። ምንም እንኳን በዚህ ፅሁፍ ዉስጥ ያካተትኳቸዉ ግጥሞች የሼህ ሁሴን ጅብሪል የራሳቸው ትንቢቶች ይሁኑ አይሁኑ የራሱ የሆነ ጥናትና ምርምር የሚያስፈልገዉ ጉዳይ ቢሆንም፣ ሼህ ሁሴን ጅብሪል ግን በትንቢታዊ ግጥሞቻቸዉ ከአጼ ዮሐንስ አራተኛ ጀምሮ እስከ ወታደራዊ ደርግ አገዛዝ መጨረሻ፥ ምናልባትም አሁን እስካለንበት ኢሕአዴግ ዘመን ድረስ ያለውን የኢትዮጵያ ታሪክ ቀድመዉ እንደተነበዩና በግጥም እንዳስቀመጡ በአፈታሪከ ይነገርላቸዋል።

ከአጼ ቴዎድሮስ፣ አጼ ዮሐንስ፥ አጼ ምኒልክ፥ እቴጌ ጣይቱ፥ ልጅ ኢያሱ፥ ንግሥት ዘውዲቱ፥ ተፈሪ፣ አጼ ኃይለ ሥላሴ፣ ደርግ፣ ወዘተ ጋር የተያያዙ ብዙ በርካታ ጉዳዮችም በስፋት በግጥሞቻቸዉ ዉስጥ ተነሰተዋል። ሼህ ሁሴን ጅብሪል አፄ ሚኒሊክ አድዋ ላይ ከጣሊያን ጋር እንደሚዋጉና በጦርነቱም ድል እንደሚቀናቸዉ ቀድመዉ ተንብየዋል፡ ከአድዋ ጦርነትም በሁዋላ ጣሊያን ተመልሶ ኢትዮጵያን እንደሚወርና ከአምስታመት ቆይታ በሁዋላ ተመልሶ ከሀገር እንደሚባረር፣ ሆኖም በነዚህ የአምስት አመታት የቆይታ ጊዜ ዉስጥ ብዙ ሰዉ በግፍ እንደሚገደል ጭምር ተንብዬዉ እንደነበር ይነገራል። ለምሳሌ ያክልም፣ የጽሑፍ ጥናት ገና ያልተጠናቀቀ ቢሆንም፣ የሼህ ሁሴንን ትንቢታዊ ግጥሞች ለማጥናትና ለማነጻጸር፣ ለሚፈልጉ ምሁራንና ተማሪዎች ይረዳል ብለዉ በማሰብ ዶ /ር ጌቴ ገላዬ 1996 ዓ.ም በእጅ ተጽፎ ፎቶ ኮፒ ከተደረገ አንድ አነስተኛ ደብተር አግኝተዉ ካጠናቀሩትና በኢንተርኔት እንዲሰራጭ ካደረጉት ብዛት ያላቸዉን የሼህ ሁሴን ጅብሪል ትንቢታዊ ግጥሞችን ካተተ መጣጥፋቸዉ ዉስጥ ከዚህ የሚከተሉት ሁለት ግጥሞች መዉሰድ ይቻላል።
ሥራቸው ባለጌ አህያ የሚበሉ
ባሕር ወዲያ ማዶ ክፉ ሰዎች አሉ፣
ሐበሻን ለመውረር ሐሳብ ያስባሉ
የኋላ የኋላ መምጣት ይመጣሉ
አምስት ዓመት ገዝተው ወዲያው ይሄዳሉ።
ድንጋይ ዱቄት አርገው መንገድ የሚያበጁ
ገመድን ዘርግተው መብራት የሚያበጁ
አህያ የሚያርዱ አሞራ የሚፈጁ
መጡ እየተማሩ ሐበሻን ሊያበጁ
ማማሩን አማረች ግን ብዙ ሰው ፈጁ።
ስለ ወታደራዊ አገዛዝ የደርግ መንግስትና በጊዜዉ ስለ ነበረዉ የመሬትና ሹመት ጣጣ አስመልከተዉ ሼህ ሁሴን ጅብሪል በትንቢታዊ ግጥማቸዉ እንዲህ ብለዉ አስጠንቅቀዉ እንደነበርም ይነገራል።
በሰማይ ቀበሌ መላኢሞች ሲያወጉ
በአጼ መባል ቀርቶ ይባላል በደርጉ
ያን ጊዜ በዱአ እንዳትዘነጉ
መሬትና ሹመት እንዳትፈልጉ።
እንዲሁም ከነገሥታትና፣ መሳፍንት በተጨማሪ ስለ ሌሎች በርካታ ቀላልና ከባድ ጉዳዮችም ሼህ ሁሴን ጅብሪል በትንቢታዊ ግጥሞቻቸዉ አዉስተዋል። ለምሳሌ አንድ የእርሳቸዉን ነብይነት የሚጠራጠር ሰዉ ነበር አሉ። እናም ትክክለኛ አዋቂ መሆን አለመሆናቸዉን ለመፈተሽ በማሰብ፣ በልብሱ ዉስጥ ትርጎ ደብቆ በመያዝ ሆዱ ያበጠ /የተነፋ/ በማስመሰል ሼህ ሁሴን ጂብሪልን ጋ ይደርሳል። ከዚያም እያቃሰተ በፅኑ እንደታመመና በሽታዉም ሆዱን ጭምር እንደነፋዉ በመግለፅ መፍትሄ እንዲነግሩት ይጠይቃቸዋል። ሼህ ሁሴን ጂብሪልም ጉዳዩን ካዳመጡ በሗላ፣ ሆዱ ያበጠዉ በደበቀዉ ትርጎ ምክንያት እንጂ ታሞ እንዳልሆነ ፍጥነት ባለዉ ሁኔታ በግጥም በመመለስ ታላቅ ነብይነታቸዉን አስመስክረዋል። እንዲህ በማለት ነበር በግጥም የመለሱለት፤
በራስህ ገብቼ በሆድህ ብወጣ
ከትርንጎ በቀር ሌላ ምንም ታጣ
ይኸ ያልሆነ እንደሁ እኔ በጉድ ልውጣ
ሆድህን የሚገልጥ ሽማግሌ ይምጣ
ይኸንን ጉድ ሳላይ ከቤትም አልወጣ።
አብዛኛዎቹ በግጥሞቻቸዉ ውስጥ የተነሱት ጉዳዬች የተፈፀሙና በታሪካ ማህደር ተመዝገበዉ ያለፉ ጉዳዮች በመሆናችዉ በዚህ ዘመን ለሚኖር ሰዉ ለመረዳት ቀላል ናቸዉ። ምናልባትም በዚህ ረገድ ትልቅ ስራ ሊሆን የሚችለዉ እያንዳንዱ ግጥም ታሪኩ ከመፈፀሙ በፊት በትክክል መገጠሙንና ግጥሞቹ የራሳቸዉ የሼህ ሁሴን ጂብሪል መሆን አለመሆናቸዉን ማረጋገጡ ላይ ነዉ)። ሆኖም አንዳንድ ግጥሞቻቸዉን በምን ምክንያት ወይም ደግሞ ምንን በማስመልከት እንደገጠሟቸዉ ለመረዳት አስቸጋሪ ሆነዉ አግቻቸዋለሁ። ምናልባትም ግጥሞቹ ለብዙ ዘምን በቃል ከትዉልድ ወደ ትዉልድ እየተላለፉ በመምጣታቸዉ መጀመሪያ የነበራቸዉን ይዘትና ቅርፅ አጥተዉ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ በግጥሞቹ ዉስጥ የተነገሩት ትንቢቶች ገና ያልተፈፀሙ በመሆናቸዉ ለመረዳት አስቸገረዉንም ሊሆን ይችላል። ከነዚህ ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች ዉጭ ሊነሳ የሚችለዉ ሌላዉ ቁምነገር ደግሞ ምናልባትም ግጥሞቹ እራሳቸዉ የተሳሳተ ትንቢት የያዙም በመሆናቸዉም ሊሆን እንደሚችል መገመት መቻል ነዉ። ነገር ግን እነዚህን ብዠታዎች ለማጥራትና አንድ ወጥ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ፣ የራሱ የሆነ ጥናትና ምርምር የሚያስፈልገዉ ትልቅ ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን ከስነ ፅሁፍ ባለሙያዎችና የታሪክ ተመራማሪዎች ብዙ ስራ እንደሚጠበቅ አመላካች ነዉ። /የአማርኛ ውክፔዲያ/

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ