ረቡዕ 14 ሜይ 2014

የበርሃ አንበጣ - አማራጩ የምግብ ግብዓት


በኄኖክ ስጦታው

ዛሬ የሰፈራችን ሕፃናት ሰማዩን ከወረሩት አንበጣዎች በላይም መነጋገሪያ ለመሆን በቅተዋል፡፡ (“አንበጣ ፤ ናቡና ጠጣ . . . ” እያሉ ለመጀመሪያ ጊዜ “በአማርኛ” ሲዘምሩ ተሰምተዋል፡፡ ከዚህም በላይ፣ አንገብጋቢው የስኳር እጥረት ችግርን አስመልክተው እሪታቸውን አሰምተዋል፡፡) በነገራችን ላይ፣ ከዚህ መዝሙር ውስጥ አንድ ስንኝ ይገርመኛል፡፡ “ስኳር የለኝም ፤ እንዳትቆጣ...” ጥንትም የስኳር ችግር ነበር፤ ዛሬም እንዲሁ፡፡ (ማን ያውቃል¡ ግንባታ ላይ ያሉት ፡- በለስ፣ ተንዳሆ፣ ኩራዝ፣ ወልቃይት. . . ስኳር ፋብሪካዎች ሥራ ሲጀምሩ መዝሙሩ ይለወጥ ይሆናል፡፡)

አንበጣ

የሰው ልጆች፣ አማራጭ ነፍሳትን በመመገብ የምግብ ግብዓቶቻቸውን አስፍተዋል፡፡ እነ ጉንዳን በቆሎ እና በቋንጣ መልክ እጅ የሚያስቆረጥም መብል መሆናቸውንም እየሰማን ነው፡፡ የተባበት መንግስታት ድርጅት እንዳው ከሆነ፣ እንቁራሪትም ሆነ ትላትሎችን መመገብ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አማራጭ የሌላቸው መፍትሔዎች መሆናቸውን አሳስቧል፡፡

መጥምቁ ዮሐንስ እንኳን በዘመኑ የበርሃ አንበጣዎችን በመብላት ሰብላችንን የሚበሉትን እንበላቸው ዘንድ ምሳሌ ሆኖ አልፏል፡፡ አንበጣ ከገብስም በላይ ለሰውነት ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች አሉት፡፡

በጥንት ጊዜ አንበጣ በአሦራውያንና በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተወዳጅ ምግብ እንደነበረ ታሪክ ዘግቦታል፡፡ አንዳንድ የአረብ ዘላኖችና የመናውያን አይሁዶች አንበጣ ይበላሉ ነበር፡፡ በእስራኤላውያን ዘንድ አንበጣ የድሆች ምግብ ተደርጎ ይታይ ነበር።

አንድ ስለአንበጣ የወጣ ማስረጃ እንደሚለው፤ “አንበጦች 75 በመቶ የሚያህል ፕሮቲን ስላላቸው አንድ ሰው አንበጦችን ከዱር ማር ጋር ቢበላ የተመጣጠነ ምግብ ያገኛል።” በነገራችን ላይ አንበጣ ለመብልነት ለማዋል ቀላል ነው፡፡ ታዲያ ዛሬ ለምን አንበላውም?! አሰራሩን ለማታውቁ እነሆ በረከት፡-

በመጀመሪያ የአንበጣው ራስ፣ እግሩና ሆዱ ከተወገዱ በኋላ ቀሪው ክፍል ይኸውም ደረቱ ጥሬውን አሊያም ተቆልቶ ወይም በፀሐይ ደርቆ ሊበላ ይችላል፡፡ አንበጣ፣ በጨው ታሽቶ አሊያም በኮምጣጤ ተዘፍዝፎ ወይም በማር ተለውሶ ለመብልነት ሊውል ይችላል፡፡ (ይህ የሚሆነው ግን ለዲዘርት ነው፡፡ ለራበው ሰው ጥሬውን ቢበላ ይመረጣል፡፡)

መልካም ገበታ!

*Share . *Comment .*Invite Your Friends to Like This Page
[የኄኖክ diary ] https://www.facebook.com/henokspad

ቅዳሜ 10 ሜይ 2014

ወጣትነት አቁሮ የማቆየት ግፊት - በ ኄኖክ ስጦታው

ወጣትነት አቁሮ የማቆየት ግፊት

ሰው እድሜውን የሚደብቀው ለሁለት ምክንያት ይመስለኝ ነበር፡፡ በግዳጅ ጦር ሜዳ ከመዝመት እና ጡረታን ፍራቻ ፡፡ አሁን ግን ብዙ ምክንያቶች ይታዩኛል፡፡ ከጥቃቅን ሰበባ አስባቦች በላይ ፣ ወጣትነትን ባለበት አቁሮ የማስቀረት ግፊት ማየል ሰፊ ሃተታ ቢወጣውም በስሱ ቃኘሁት፡፡
***
ትልቅ ለመሆን የተመኘንበት የልጅነት ሲዝናችን በዕድሜ ዑደት ተሽሮ ለጉርምስና ቦታውን ይለቃል፡፡ ጉርምስና እሳት ነው፡፡ ነዶ ለማለቅ ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ አመዱን ትቶ ቦታውን ለወጣትነት ይለቃል፡፡ የሚግለበለበውን የእድሜ እሳት ለማርገብ የውሸት ውሃ መቸለስ የሚጀመርበት ሲዝን፡፡
ዕድሜ ግን አሪፍ አርቲስት ነው፡፡ ሌሎችን ለማሳመን የዋሸነውን ስዕል ሙሉ በሙሉ ሰርዞ የራሱን እውነተኛ ምስል እኛው ላይ የሚጠበብ ድንቅ አርቲስት! ዕድሜ፣ ተፈጥሯዊ ማስተባበያውን አካላችን ላይ በመሳል ጉዞውን ይቀጥላል፡፡ እኛም ስዕሉን በሌላ ስዕል (ሜካፕ) ለማጥፋት እንጥራለን፡፡ ነጩን ስናጠቁር፣ ጥቁሩን ስናቀላ፣ የተጨማደደውን ስናቃና፣ የወደቀውን ስናነሳ፣ የረገበውን ስንወጥር፣ የበለዘውን ስናነጣ፣ . . .
***
“ልደቷ” ብለን ቅፅል ስም ያወጣንላት ጓደኛች አለችን፡፡ ቆንጆ ናት፡፡ ጭሰት የማይታክታት ቆንጆ፡፡ ፍቅረኛ አይበረክትላትም፡፡ አቤት! ከአንዱ ወደሌላው ለመሸጋገር ያላት ፍጥነት! “ፍቅረኛዬ ነው” ብላ ያስተዋወቀችን ወንዶች ተመሳሳይ የሚያደርጋቸው አንድ ነገር አለ፡፡ ልደቷን በፌሽታ ያከብሩላታል፡፡ አድሜዋንም ሆነ የተወለደችበት ቀን ግን ከራሷ በቀር በትክክል የሚያውቅ የለም፡፡ልደቷን በአመት ውስጥ አራት አምስቴ ልታከብር ትችላለች፡፡ (ቁጥሩ የሚወሰነው በአመት ውስጥ በተጃለሷት ወንዶች መጠን ነው)፡፡ ዕድሜዋ ግን ጨምሮ አያውቅም፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ እንደ ሰዓት ወደኋላ አድርጋ የሞላችው ይመስለኛል፡፡
(በአንዱ የልደቷ ፓርቲዋ ላይ በብዙ ጉትጎታ ተገኝቼላት ነበር፡፡ ቦሌ መስመር ካሉ አንድ ክለብ ውስጥ ነበር ድግሱ፡፡ ደጋሹም አዲሱ “ፍቅረኛ” ፡፡ ሸከከኝ፡፡ “እጮኛዬን ብሉልኝ ፤ እጮኛዬን ጠጡልኝ፤ ፍቅረኛዬን አጫርሱኝ. . .” ብላ የጋበዘችኝ መሰለኝ፡፡ በቃ፤ ማንም ሳያየኝ ሹልክ ብዬ ወጣሁ፡፡ )
በሌላ ቀን ሳገኛት እንዲህ ስል ጠየቅኳት፡- “አዲስ ፍቅረኛ በያዝሽ ቁጥር ለምንድነው ልደትሽን እንዲያከብሩ የምታደርጊያቸው?!”
መልሷ በናቲ ዘፈን አሳወቀችኝ ፡-
“በቃ፤ በቃ፤ ዛሬን ኑር በቃ! . . .በቃ!
ለምንድነው የምትጨነቃው...
በቃ . . . . .”
በቃ! ይህ ሁሉ ልደት ለዚሁ ነው በቃ! የሁሉ መዝናናት ለዚሁ ነው በቃ! ይህ ሁሉ መነ....(እንዝለላት በቃ፡፡)
***
ኮመዲያን ልመነህ ታደሰን “አዲስ ቪው ሆቴል” በረንዳ ላይ ነበር ያገኘሁት፡፡ ጥቁር በጥቁር ለብሷል፡፡ ጥቁር ቦርሳ ... ጥቁር ባርኔጣ ...፡፡ . አድናቆቴን ስነግረው በትህትና አመስግኖ ተቀበለኝ፡፡ በርግጥ መታመሙን በሚደያ ሲነገር ሰምቻለሁ፡፡ ሕመሙ ግን የማገናዘብ ብቃቱና እና ጨርቁን አላስጣለውም፡፡
አንድ ነገር ግን አስተዋልኩ፡፡ ፀጉሩ ላይ ሽበት አይታይም፡፡ በርሱ እድሜ ካሉትም አንፃር ልመነህ አሁንም ወጣት ነው፡፡ ለጨዋታ በር መክፈቻ እንዲሆነኝ ስል ወጣትነቱ ጠብቆ የቆየበት ምስጢር ምን እንደሆነ ጠየቅኩት፡፡
(በመልሱ ተመራመሩበት፡፡)ትኩር ብሎ አይቶኝ ሲያበቃ እንደህ ሲል መለሰልኝ፡-
“ቀላል ነው፡፡ ዕድሜህን እያሰብክ አትቁጠረው፡፡ እንዲያውም ፈፅሞ እድሜህ ስንት እንደሆነ እርሳው፡፡”

ቅዳሜ 3 ሜይ 2014

የ“ሸኖ ቤት ሃሳቦች” #ኄኖክ_ስጦታው



የ“ሸኖ ቤት ሃሳቦች” የማንበብ ሱስ የተጠናወተኝ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ነበር፡፡ በርግጥ ብዙዎቹ ሃሳቦች በጨዋ ቋንቋ “ፀያፍ” ተብለው የሚነገሩ ቢሆንም ብሶትና ምክርን በጨዋ ገለፃ የሚቀርቡ ሃሳቦችም አይታጡም፡፡ ያም ሆኖ ሕዝብ የሚጠቀምባቸው መፀዳጃ ቤቶች ስገባ በግድግዳው ላይ የተጻፉ ጽሑፎችን ማንበብ ያዝናናኛል፡፡

ሸኖ ቤትን ለመውደድ የፎክሎር ተማሪ መሆን አይጠይቅም፡፡ ከማይረቡ መፅሐፍት የተሻለ ምልከታን እና ሂዩመርን በሸኖ ቤት ሃሳቦች መቃረሜ በራሱ ለመፀዳዳት የማባክነውን ጊዜ የሚክስ ቁምነገር አላጣበትምና፡፡

“የዘርሲዎች ፍቅር” የተሰኘው ልቦለድ መፅሃፍ ላይ አንድ ገፀባሕርይ አስታውሳለሁ፡፡ በተለይ መፀዳጃ ቤት ስገባ ብዙ ጊዜ ትዝ ይለኛል፡፡ (አብሮኝ ይገባል - - ብል ይቀላል፡፡) ይህ ሰው ቁምነገርን የሚቃርመው ከመፀዳጃ ቤት ነው፡፡ ግድግዳ ላይ የሚጻፍ ግራፊቲ አልነበረም የሚያነበው፡፡ ሰዎች “ካካቸውን” የጠረጉበትን ወረቀት ሰብስቦ ኪሱ በመክተት እና በማንበብ ነበር፡፡

እነዚህ የግድግዳ ላይ ጽሁፎች ስለምንስ ይጻፋሉ? ግባቸው ምንድነው? ... ምክንያቱን እርሱት፡፡ ከየት መጡ የሚለው ምርምር አያሳስበኝም፡፡ ባለቤት አልባነታቸው በራሱ በቂ ምክንያት ነው፡፡ ምክንያት ከስም ይጀምራልና፡፡ ማንነቱን ለማወጅ የመፀዳዳት ባህሉን አደባባይ ላይ ከሚፈጣጥም ሰው ምንም አልጠብቅም፡፡ ማንነቱን በመጸዳጃ ቤት ግድግዳ ላይ የሚያሰፍር ማንነቱ ያልታወቀ ሰው ግን ታዳሚ ነኝ፡፡ (እስቲ ዛሬ የተመረጡ ትውስታዎቼን በሹካ ጨልፌ ላካፍላችሁ፡፡)

ለመጀመሪያ ጊዜ ካነበብኳቸው ውስጥ የሚመደብ የመፀዳጃ ቤት ሃሳብ እንዲህ የሚል ነበር፡-

“God is dead!” -Nietzshce
“Nietzshce is dead!” -God

ያኔ ይህን ሳነብ ያልገባኝ ብዙ ነገር ነበር፡፡ በርግጥ ኒቼ “እግዚአብሔር ሞቷል” በሚለው ግንዛቤው ዛሬም ድረስ (ሞቶም) ያወዛግባል፡፡ በሕይወት በነበረበት ጊዜ “እግዚአብሔር ሞቷል ፤ ሰዎችም ነፃ ወጥተዋል...” እያለ መስበኩን የተረዳሁትም ከጥቅሱ በኋላ ነበር፡፡ አመታት አልፈው፡፡ የኒቼን ሞት ጠብቆ እግዚአብሔር እንዲህ ማለቱን ግን መፀዳጃ ቤት እንደ ትንቢት ቀድሞ አሳውቆኛል፡፡ ጥበብ ከጲላጦስ መፅሐፍ ላይ ይህን ጥቅስ ሳነበው አልደነቀኝም፡፡ ጥቅሱን ሲያስታውሰኝ ግን የሆነ ነገር ግን ሸቶኝ ነበር፡፡ ያም ጠረን፣ ይህን አባባል ያነበብኩበት መፀዳጃ ቤት አጉል ጠረን ነበር፡፡

በአንድ ኮሌጅ መጸዳጃ ቤት ውስጥ ደግሞ እንዲህ የሚል መልዕክት ግድግዳው ላይ ተፅፎ አነበብኩ፡- “ምን ግድግዳው ላይ ታፈጣለህ!? አርፈህ አትፀዳዳም!?” ሆሆሆ... ሰዉ ጨምሯል!

በሌላ ዩኒቨርስቲ መፀዳጃ ቤት ውስጥም እንዲህ አይነት ትዕዛዝ አጋጥሞኝ እንደነበር አልረሳውም፡፡ በደቃቅ ጽሑፍ የተጻፈ መልዕክት ከመጸዳጃው በር ላይ ሰፍሮ አየሁና ከቅምጤ በመጠኑ ብድግ ብዬ ላነብ ስሞክር ያገኘሁት መልዕክት አስደንግጦ “የሚያስቀምጥ” ነበር፡፡ሃሳቡ እንዲህ የሚል ነበር፡- “ሰው ማለት አንተ ነህ፡፡ አሁን ወደነበርክበት ተመልሰህ አርፈህ እራ! ” የሚል ትዕዛዝ ፡፡

የሸኖ ቤት ግድግዳ ላይ ከተፃፉ ሃሳቦች ሌላው የማርከኝ እንዲህ የሚል ነው ፡-

“ቺክህን ጥሩ ነገሮች እንዴት እንደምታሳያት በማሰብ አትጨናነቅ፡፡ አሁን እየጣልክ ያለውን እንቁላል ግን ጠብሰህ እንዳታበላት አደራ! ስትጨርስ ውሃ ድፋበትና ከሌሎች እይታ ሰውረው!”

የሸኖ ቤት ግድግዳ ሃሳቦች አንዳንዴም ፍልስፍና ይቃጣቸዋል፡፡ በአንድ የሕዝብ መፀዳጃ ቤት ውስጥ ያነበብኩትሃሳብ ለዚሁ ምስክር ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡-

[“መኖር ማለት፣ በምታባክነው ጊዜ የምታጣው ብኩንነት ነው፡፡ ለመኖር ስትል ከምታባክናቸው ሰዓታት ትልቁን ቦታ የሚይዘው ምን እንደሆነ ታውቃለህ?”

“አውቃለሁ” ካልክ ተሳስተሃል! በዚህ ሰዓት ማራት አልነበረብህም!!”]

ትውስታዬን ተደብቄ በተጠቀምኩበት የሴቶች መጸዳጃ ቤት ግድግዳ ላይ ባነበብኩት ልቋጭ፡፡


“በወንዶች ከሚነገሩ ብ-ዙ ውሸቶች መሃከል የማላምነው “ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም” የሚሉትን ብቻ ነው፡፡”


(›››› ሌሎች ጽሑፎችን በፌስቦክ ገጽ ለማንበብ ይህን አድራሻ ይጠቀሙ፡-  https://www.facebook.com/pages/የኄኖክ-diary/736486173038263

ረቡዕ 16 ኤፕሪል 2014

የኄኖክ-diary (በፌስቡክ ተከፈተ፡፡)


ውድ የእልፍኜ ታዳሚያን፤ የኄኖክ-diary በፌስቡክ መንደር የከፈትኩት አዲሱ ገጼ ነው፡፡

የኄኖክ-diary
የኄኖክ-diary
ማነው ዳየሪዬን ማንበብ የሚፈልግ?  የኄኖክ-diary ፡-  https://www.facebook.com/henokspad በዚህ ሊንክ ገብተው ላይክ በማድረግ ይከተለኝ፡፡

ሰኞ 14 ኤፕሪል 2014

የበዓል ሰሞን ፍተላዎች - ኄኖክ ስጦታው



በግ ከመግዛት በግ የገዛንባቸውን ዘመናት በማሰብ መፈተል ይቀላል፡፡ 

ፍተላ 1 (እውነተኛ)

ለአዲስ ዓመት ቅበላ ሸመታ በወጣንበት ባንዱ የሆነ ነው፡፡ ሶስት ሆነን ገበያ ወጣን ፡፡ ሁለታችን ሙክት ስንገዛ ሶስተኛው ጓደኛችን ደግሞ እኛ አንድ ሙክት በገዛንበት ሂሳብ ሁለት ትንንሽ በጎችን ሸመተ፡፡ ሊቀልባቸው ነው ሊቀለባቸው?¡? . . . ለምን ሁለት ትንንሽ በጎች እንደገዛ ጠየቅነው፡፡ በኩራት ነገረን፡፡

እቅዱ እንዲህ ነው፤ አንዱን ለዘመን መለወጫ ይባረካል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ለቅዱስ ዮሐንስ፡፡ 

በቃ! የሸመታ ጥበቡ አሪፍ ቅጽል ስም አሰጠው፡፡ “ቬንገር” ተባለ፡፡

በሌላ ቀን . . .

ባለ ሁለት በጉን ሰው (“ቬንገር”ን) በአካል የማያውቁ የኔ ጓደኞች ሁሉ ስለሆነው ተረኩላቸው፡፡ አብርሃም ጆሮ ደረሰ፡፡ አብርሃም ዛሬ የነገርከውን ቀልድም ይሁን ቁምነገር ሪሚክስ አድርጎ በሌላ ቀን መልሶ ለራስህ ይነግርሃል፡፡ ማን እንደነገረው ቢረሳም የተነገረውን የማይረሳ ጓደኛ ኖሮህ አያውቅም? እንደዚህ አይት ሰው ነው፡፡ 

ለገና በዓል ዋዜማ አብርሽ አብሮኝ ገበያ ወጣ፡፡ “ቬንገርም” ነበር፡፡ የበግ ወሬ ተነሳ፡፡ 

“አንዱ የተባለውን ልንገራችሁ . . . ” ብሎ ወሬ ጀመረ፡፡ አብርሽ፡፡ “አንድ ትልቅ በግ በሚገዛበት ገንዘብ ሁለት ትናንሽ በጎች ገዝቶ ቤቱ ሲገባ ምን እንዳሉት ታውቃላችሁ ??!! . . .”

እኔና “ቬንገር” ተፋጠጥን፡፡ አብርሽ ወሬውን ቀጠለ፡፡ እስኪጨርስ ታግሼ እንዲህ አልኩት፡-

“እሱ ነው “ቬንገር”፡፡ ተዋወቀው፡፡”

አብርሽ ደነገጠ፡፡ ድንጋጤው ደግሞ እኛን አሳቀ፡፡ ከሳቁ በኋላ “ቬንገር” ወደጆሮዬ ተጠግቶ፡-

“በስሜ ካልጠራኸን ጓደኛዬ አይደለህም!” አለ፡፡ እንዳለኝም አደረኩ፡፡ (በተቃራኒው ይህን ወሬ ስጽፍ እውነተኛ ስሙን አልጠራሁም፡፡)

የዛን እለት “ቬንገር” ትልቅ በግ ገዛ! አብርሽ ግን “ቬንገር” ገዝቷቸው ከነበሩ ትናንሽ በጎች ያነሰች በግ ገዛ፡፡

“ቬንገር” በተራው ፡- 

“በግ ገዛሁ እንዳይል ንገረው፡፡ የበግ ለምድ የለበሰች ዶሮ ገዛሁ ይበል፡፡” 

ፍተላ 2 (በእውነት የሆነ)

እንዲሁ በሌላው በዓል . . . ሁለት ሆነን በግ ሸመትን፡፡ ዶሮ ማነቂያ የምናውቀው አንድ ሌላ ወዳጃችን ድክም ያለች በግ እንደ ቦርሳ አንጠልጥሏት መጣና “በፒያሳ የምታልፉ ከሆነ እባካችሁ ሸኙኝ” አለን፡፡ ተባበርነው፡፡ የእርሱ በግ ከሁለት ቀንዳም በግ መሐል የመኪና ኪስ ውስጥ አስገባንና ጉዞ ተጀመረ፡፡ መንገድ ላይ በመኪና ኪሱ ውስጥ የጦፈ የመንጓጓት ድምጽ ተሰማ፡፡ ያው የተለመደ የበጎች መንፈራገጥ እንደሆነ በማሰብ ፒያሳ ደረስንና መኪናው ቆመ፡፡ ኪሱ ተከፈተ፡፡ መጨረሻ የተጫነችው በግ ነስር በነስር ሆናለች፡፡ 

“ጭንቅላቷን ወደሰማይ ቀና አድርገህ ያዝላት!” አልነው፡፡ እንደተባለው አደረገ፡፡ 

የበጓ ባሉካ “ሶፍት ! ሶፍት! እባካችሁን ሶፍት . . .” አለ ብለን አስወራን፡፡ ነገሩ ካለፈ በኋላ፡፡ 

በወቅቱ አቅማችን የፈቀደው የመጀመሪያ ርዳታ ተረብ ነበር፡፡ የህክምና ጉዳይ የማይታሰብ በመሆኑ . . . እንደ ሻንጣ አንጠልጥሎ ወደ ቤቱ ሮጠ፡፡ 

“በረንዳ ላይ ታስራ ለመጮህ ያልታደለችው በግ በበአል ዋዜማ ትባረካለች፡፡” እንዳለው ሼክስፒር /ለአባባሉ ክብደት ልስጠው ብዬ ነው/ እንዲሁም ሆነ፡፡ 

ፍተላ 3፡- (በቢሆን የተፈተለ . . . የበዓል ትርርብ ላይ የተፈጠረ)

ቀጭን ድምፅ ያለው ወዳጃችን ፍየል ገዛ፡፡ ፍየሏ ስትጮህ የሰው ስም የምትጠራ ነው የምትመስለው፡፡ “በቀለ!” የምትል፡፡ ደግሞም እንደዛ ነው የምትለው፡፡ ቤቱ ወስዶ አሰራት፡፡ መጮህ ጀመረች፡፡ በቀጭን ድምጿ፡፡

“በቀለ! በቀለ! በቀለ!”

በሩ ተንኳኳ፡፡ ባለ ፍየል ጓደኛችን በሩን ከፈተ፡፡ ጎረቤቱ አቶ በቀለ ከደጅ ቆመው፡-

“አቤት ! ጠራኸኝ??”

በቀጭን ድምፁ ፤ “ኧረ እኔ አልጠራሁዎትም” አለ፡፡ እንዳልጠራቸው በመኃላ አረጋገጠ፡፡

እንዲህ እያሉ ሄዱ፣ “የማርያም ብቅል እየፈጨሁ ነው!” 

እሱ በተራው አፀፋ ተረብ ሰነዘረ፡፡

ኄኖክ ከጩኸት ይልቅ ፉጨት የሚቀናት ዶሮ ገዛ፡፡ ሊያርዳት ሲል “ቆቆቆቆቆይ . . . “ቆቆቆቆቆይ . . .!” ስትል የሰሙ እናቱ ለዶሮዋ አዝነው አልያም ዶሮዋ እያጣጣረች እንደሆነ ተረድተው፡-

“ምነው ኄኖክ! ቆይ እያለችህ ልታርዳት!?! ”

“እና ምን ላድርጋት??”

“ትንሽ ከታገስክ መሞቷ ስለማይቀር ያኔ ትቀብራታለህ፡፡”