ሰኞ 4 ኦገስት 2014

"መንጭቆ ከማስነሳት" ማዶ… ኄኖክ ስጦታው


አሮጌ መኪና ለማሽከርከር አሪፍ ሹፌር መሆን አይጠበቅብህም፤ ልበ–ደንዳና መሆን ግን የግድ ነው። ደንዳና ልብ ከሞተር ቀጥሎ የመኪናው አንቀሳቃሽ ሃይል ነውና።

በምስኪኗ ቮልሴ ካስተናገድኳቸው ቅስም ሰባሪ ተረቦች የመጀመሪያው ዛሬ ሳስታውሰው ያስቀኛል። "አዲስ" የገዛኋትን መኪናዬ ለጓደኛዬ ላሳየው ያለበት ቦታ ድረስ እያሽከረከርኩ ሄድኩ። አንገቱን በሃዘኔታ እየናነቀ፦ "ይህቺ ቮልስ የተመረተችበት ፋብሪካ፣ አሁን ዲዲቲ ማምረቻ እንደሆነ ታውቃለህ?!" አለ። በጊዜው ተቆጫበርኩ። ተቀየምኩት መሰል። "ከዚህም የባሰ እንዳለ" የገባኝ ግን ወዲያው ነበር።

ባለመኪና ለመባል ቮልስ የሚገዛ ተሸውዷል። ምክንያቱም ማንም ባለመኪና አይለውም። እንበልና መኪናዋ የቆመችው መንገድ ዘግታ ቢሆንና ሹፌሩ ባይኖር "ማነው የዚህ መኪና ባለቤት" አይባልም። ባይሆን፣ "ይቺ ቮልስ የማናት" ይባል ይሆናል።
 

የሆነ ሰሞን፣ «አሮጌ መኪኖች ከመንገድ ይወጣሉ» የሚል ስር የለሽ ወሬ ሰምተን ሰጋን። የቮልስ መካኒካችን ስናማክረው ወሬውን እንዲህ ብሎ አጣጣለው። " አሮጌ መኪና ይገባል እንጂ መቼም አይወጣም። መንግስት እራሱ አሮጌዎቹን የሚተካበት አዲስ መኪና መች አለውና?"

(እውነቱን ነው፤ ሌሌሎች አርጅቶ የተጣለ ለእኛ ግን የክት ነው። ያገለገለ እቃ ዋጋውን የሚያጣበት የገበያ ደንብ በተናደባት አገር እንኳን ያገለገለ መኪና ቀርቶ የተለበሰ የውስጥ ሱሪም ዋጋ አለው።)


ሹፌሮች ቀበቶ ሳያደርጉ ማሽከርከር በትራፊክ ደንብ መተላለፍ እንደሚያስቀጣ ደንብ ወጣ። ታዲያ ያኔ፣ በቮልስ ባሉካዎች ዘንድ ታላቅ ድንጋጤ ተፈጠረ!

ቀበቶ ባልታሰበበት ዘመን የተመረቱ መኪናዎችን ባለቀበቶ ለማድረግ ሩጫ ተጀመረ። የደህንነት ቀበቶ ግን ዋጋው ጣሪያ ደርሶ ነበር። አንድ ወዳጃችን ግን ሁነኛ ዘዴ ፈለሰፈ። የሻንጣ ማንገቻን ቆርጦ እንደቤልት የመጠቀም መላ። የፈጠራ ባለመብት እንደሆነ የቮልስ ቺፍ መካኒኩ አረጋገጠለት።

"ዳሩ ምንያደርጋል" መሀል አደባባይ ላይ በትራፊክ ፖሊሶች ተያዘ። ትራፊኮቹ የፌክ ቀበቶውን ከመኪናው አስፈትተው አላገጡበት። "የደህንነት ቀበቶ ከሌለህ ማንገቻ ያለው ሱሪ ብታደርግ ይሻል ነበር¡" እንዳሉት ነገረን ። ሳቅን።

"ስንት ብር ተቀጣህ?" ሲል ከመሃከላችን አንዱ ጠየቀ።
"አልቀጡኝም። 'ብንቀጣህ ከሌላው ሹፌር እኩል ትሆናለህ፤ ብትቀጣ የምትከፍለውን ብር አሁኑኑ የደህንነት ቀበቶ ግዛበት'— ብለው ለቀቁኝ።"
 

«የአሮጌ መኪናህን መካኒክ ጓደኛህ አድርገው።» የቮልስ ፍቅር ማደሪያ ልቡ ያለው ያው ጋራጅ ነውና።

አንድ ሰሞን ቮልሴን ለማስጠገን ጋራጅ እመላለስ ነበር። ጋራጅ የሚያስኬደኝ የመኪናዋ መበላሸት ብቻም አልነበር ። ጤነኛ ስትሆንም ያሳስበኛል።【ሳትበላሽ ከሰነበተች በቀላሉ የማይጠገን ከባድ ብልሽት እንደሚጠብቀኝ እርግጥ ነው】።

ሌላው ጋራጅ ሳልሳለም እንዳልውል ያደረገኝ ምክንያት፣ ከቮልስ ባሉካዎችና መካኒኮች ጋር መወዳጀቴ ነበር። 

አያሌ ፍተላዎች ከጋራጅ ይወለዳሉ። ተረቦች ነፍ ናቸው። ከመካኒኮች ጋር መዋል ያስደስታል። ጨዋታቸው፣ ትርርቡ፣ ልግጡ፣ … አይጠገብም።

ሞተራቸው በቁልፍ የማይነሳና በግፊ ተመንጭቀው ከሚነሱ ቮልሶች የተቀዳ አንድ አባባል አለ። «መንጭቀው ይነሳል!»  የሚል። አንድ ቀን እዛው ጋራጅ ውስጥ በሃይል አስነጠስኩ። ማንም «ይማርህ» አላለኝም። በምትኩ ግን «መንጭቀው ይነሳል!» የሚል ድምፅ ተሰማኝ።

ይሄ ድምፅ እስከዛሬም ድረስ፤ የቆምኩ ሲመስላቸው እንድነሳ ከሚገፉኝ አነቃቂ ሰዎች አንደበት ይሰማኛል።

"መንጭቀው ይነሳል!!"

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ