እሑድ 9 ኖቬምበር 2014

ዱባና ልጅነት

(ኄኖክ ስጦታው)

#ዱባ
ልጅ ሆኜ የሰማሁት ዘፈን አለ። ስለዱባ እንዲህ ብሎ ነበር፦

"ሳይበላ ሳይጠጣ ይወፍራል ዱባ
ልቤ ተንከባሎ አንቺ መንደር ገባ "

ግጥሙን አድጌ ስረዳው ልብ እና የሚንከባለል ዱባ  ያገናኛቸው ቤት መምቻቸው "ባ" እንደሆነ ገባኝ። ዱባ ወጥ አልወድም።  የዘፈኑ ተፅእኖ ነው መሰል፣ ቤታችን ዱባ ወጥ ሲሰራ ገንዘብ የወጣበት አይመስለኝም ነበር ። ተንከባሎ ቤታችን የገባ ነበር የሚመስለኝ።

በልጅነት ዘመን የማልረሳው አንድ ገጠመኝ አለ። የእርሻ አስተማሪያችን ስለ አዝእርት ሲያስተምሩ እንዲህ ብለው ጠይቀው ነበረ፦

"ከጥራጥሬ ውስጥ የሚመደቡት ምን ምን ናቸው?"

ምድረ ተሜ ተራ በተራ እየተነሱ "ጓያ፣ ሽንብራ፣ ባቄላ…" እያሉ መለሱ። መምህሩ ወደኔ እያዩ፣ "ኄኖክ ፣ የምትጨምረው አለ?" ሲሉኝ ፣ ከመቀመጫዬ ተነስቼ "ዱባ" አልኩና ተቀመጥኩ። የተማሪው ሳቅ እና ያስተማሪው ድንጋጤ ተደምሮ፣ በስክሪብቶ ጫፍ ቂጡን እንደተወጋ ተማሪ አስፈንጥሮ አቆመኝ። (ድሮ ተንኮለኛ ተማሪ አጠገቡ የሚቀመጥ ተሜን ብድግ ሲል ያለቀ ስክሮብቶ አሹሎ እስኪቀመጥ ይጠብቅ ነበር። ያሁኑን ባላውቅም።)

መምህሩ በግርምት አፍጥጠው ፣ አፍጥጠው፣ አፍጥጠው… አይተውኝ ሲያበቁ፣ ባፍንጫቸው የንፋስ ሳቅ ("ህምፍ" አይነት) አሰምተው ዱባ ያልኩበትን ምክንያት ጠየቁኝ። ክፍሉ ረጭ አለ ። እንዲህ ረጭ ያለ ዝምታ ለመጨረሻ ጊዜ ያስተዋልኩት ያኔ ነበር።

ዱባ የጥራጥሬ ዝርያ ለመሆኑ የሰጠሁት አጭር ማብራሪያ፦

"የዱባ ፍሬዎች ፀሐይ ላይ ተሰጥተው ሲደርቁ፣ ተቆልተው ይበላሉ። ልክ እንደ ሽምብራና ባቄላ ማለት ነው።" ከማለቴ ክፍሉ በሳቅ ተናወጠ።

ምን  የሚሳቅ ነገር አግኝተው እንደሆነ ለማወቅ አይኖቼን በክፍል ጓደኞቼ ዙሪያ አንከራተትኩ። ሳያቸው ነው መሰል ይበልጥ መሳቅ ቀጠሉ። ከሁሉ ከሁሉ የገረመኝ፣ የመምህሩም አብሮ መሳቅ ነበር። መቆም እንዲህ ያስቃል?

መቀመጥ ሳይሻል አይቀርም።
ተቀመጥኩ።

ዓርብ 15 ኦገስት 2014

የጆገረረ ጆሮና ምናምን… (ኄኖክ ስጦታው)

ልጅቱ ቆንጆ ናት መሰለኝ። እንጃ…

ለሥራ የምመላለስበት ቢሮ ውስጥ ተቀምጫለሁ። ስልኬን አውጥቼ ማስታወሻውን ከፈትኩ። (ይህ ማስታወሻ ወሳኝ ግብዓቴ ነው። የዳየሪዬ ዋናው አካል ከዚህ ይጨለፋል። እና ከዚህ ቢሮ እስክወጣ ድረስ ለምን አልቆዝምበትም?

ጸሐፊዋ፤
ጉዳዬ እስኪፈፀምልኝ ድረስ ሰረቅ እያደረኩ ተመለከትኳት። ከንፈሯን ደማቅ ቀይ ቀለም ቀብታዋለች። 【የሊፒስቲክ ጥቅም ከንፈር ከማለስለስና ከማስዋብ አገልግሎት ባሻገር ምንም ጉዳት አያስከትልም?!】የከንፈር ቀለም የውሽማ ሸሚዝ ላይ ከታተመ በቶሎ ታጥቦ የማይለቀው ቀለሙ ብቻ አይደለም። የሚያስከትለው መዘዝም እንጂ። (ለብዙ ቤተሰብ መበጥበጥ ምክንያት ሲሆን ያላሳየ የኢቲቪ ድራማ ይኖር ይሆን?!)

በድንገት ቀና ብላ "ተጫወት" አለችና ወደትየባዋ ተመለሰች። በዚህ ቅፅበት ምን ልጫወት? እቃቃ ልጫወት? ከማይገቡኝ ጨዋታዎች አንዱ ይህ ነው። "ተጫወት" ።

  (አንዷ ናት አሉ፤ ፈረንጅ ተጃልሳ ነው። የቋንቋ ነገር አላግባባ ሲላቸው ሁለቱም ዝምታን መርጠው ይቀመጣሉ። ዝምታው እንዴት ይሰበር?! በመጨረሻ እርሷ እንዲህ አለች አሉ፦ "Play" ) ተጫወት፤ ተጫወቺ፤ እንጫወት፤ ፕሌይ …

የጸሐፊዋ ዓይን ያምራል። ፀጉሯ ያምራል። ፊቷ የኦቫል ቅርፅ አለው። ለብቻዬ ፈገግ አልኩ።  የፊቷ ቅርፅ ከትላልቅ አይኖቿ ጋር ተዳምሮ ጥንታዊ የብራና ላይ ስእል አስመስሏታል።  【ያሰብኩትን ከፊቴ ላይ አንብባ ይሆን?!】ሰረቅ አድርጌ አየኋት። እሷ'ቴ፤ አንዳቀረቀረች ነው።

በምን ፍጥነት ከትየባ ወደ ጥፍር ሙረዳ አንደተሸጋገረች አላውቅም። ጣቷ ያምራል። ውበቱን ግን የጥፍሯ ርዝማኔ ያደበዘዘው ይመስላል።

"ተጫወት" እስክትለኝል ድረስ አፈጠጥኩባት። ይገርማል። ጥፍሯ ላይ ተመስጣለች።
ጥፍር! 
የጥፍር እድገት ፍጥነትና፣ የወንድ ልጅ ጡት ሁሌም ይገርሙኛል። ጥፍርስ ይደግ፣ ይመንደግ። ቢያንስ ለሴቶች የውበት ሳሎን ባለሙያዎች የገቢ ምንጭ መሆኑን እያየን ነው። (ኧረ የማይገባኝ ነገር ፤ "እጅና እግር እንሠራለን" የሚሉ ፀጉር ቤቶች  ከጥፍር የዘለለ አንዳች ጥበብ ላይ ደርሰው ይሆን?!) ። ከደረሱ ድንቅ ነው። ካልደረሱም እሰየሁ። እኔም ያልደረስኩበትን በነፃነት እንድናገር በር ከፍተዋል። ውሻ በቀደደው ጅብ እንደሚገባ ፈሪ አበዎች ከገለጹ ዘንዳ እነሆኝ በረከት ለክፉ… የወንድ ልጅ ጡት ጥቅም ምንድነው?! አጥብቶ ሊያሳድግበት… ወይስ ራሱ ጠብቶ ሊመነደግበት?!

ጸሐፊዋ፣
በዚህ ዓመት በሀቀኝነት ያየሁዋት ባትኖርም፣ ሰርቄ ካየኋቸው ሴቶች ውስጥ ግን  "የአንበሳውን ድርሻ" ትወስዳለች። አሁን ከጥፍር ሙረዳ ወደ ወደትየባዋ ተመልሳለች። ጸሐፊዋ።

ጆሮዋን!
ኧረ ጆሮ! በአንድ ጆሮዋ ላይ ብቻ ስንት የጉትቻ ማንጠልጠያ ብስ እንዳለ ልቆጥር ሞክሬ አቅም አጣሁ። እውነት ለመናገር ያልተበሳው የጆሮዋ አካል ቢኖር እርሱም ተበሥቷል።

የጆሮ ጥቅም አናሳ እንደሆነ የገባኝም ዛሬ ነው። (አንድ ግጥም ትዝ አለኝ። ያኔ የጋዜጠኝነት ትምህርት ስንማር የቃላት ፈጠራን አስመልክቶ አንዱ መምህር "ልጂቱ ፣ የዘመነቺቱ " የሚለውን የደበበ ሰይፉን ግጥም በምሳሌነት አጣቀሰና የራሳችሁን ግጥም በፈጠራ ቃል ተጠቅማችሁ ጻፉ ሲል አዘዘን። ጫማዋን ጨምታ፣ ሱሪዋን ሶርታ፣ ቦርሳዋን ቦርሳ፣… ቲሽ!  ሁሉንም አዲስ ቃላት ደበበ ሰይፉ አደብይቶታል። አንዷ ክላስ ሜታችን ግን ለምሳሌነት ያልቀረበ ምርጥ የቃላት ፈጠራ ይዛ ቀረበች፦

"ጆሮዬም ይጆርር፣ እጅ እግሬ ይጀግረር
ጆሬዬም ይደንቋ፣ ከደነቋ አይቀር…"

አለችና ተሜን በፈጠራዋ አስደምማ እርፍ!!"

መምህራችን ግን አልተዋጠለትም። ወይ ደበበ ፣ ደበበ ሸትቶት አልዋጥ ብሎት ይሆናል እንጃ፤ የተገጀረረውን የቃል ፈጠራ ገርጅጆት አለፈው። ቺኳ ገጣሚት ተቆጫበረች። እናም አለፈ። እንኳን አለፈ።

ዛሬ ያየሁት ጆሮ የተበሳ እንዳልሆነ ሳስበው ታወሰችኝ። በርግጥም ጆሮ ይደነቋል! ! እጅ እግርም ይጀገረራል!!

የቢሮዋ "ጸሐፊ" ተጫወት የምትለኝ መስሎኝ ቀና ብዬ አየዃት። ኤጭ። "ተጀግርራለች፣ አልያም ደንቁታለች…

ሰኞ 4 ኦገስት 2014

"መንጭቆ ከማስነሳት" ማዶ… ኄኖክ ስጦታው


አሮጌ መኪና ለማሽከርከር አሪፍ ሹፌር መሆን አይጠበቅብህም፤ ልበ–ደንዳና መሆን ግን የግድ ነው። ደንዳና ልብ ከሞተር ቀጥሎ የመኪናው አንቀሳቃሽ ሃይል ነውና።

በምስኪኗ ቮልሴ ካስተናገድኳቸው ቅስም ሰባሪ ተረቦች የመጀመሪያው ዛሬ ሳስታውሰው ያስቀኛል። "አዲስ" የገዛኋትን መኪናዬ ለጓደኛዬ ላሳየው ያለበት ቦታ ድረስ እያሽከረከርኩ ሄድኩ። አንገቱን በሃዘኔታ እየናነቀ፦ "ይህቺ ቮልስ የተመረተችበት ፋብሪካ፣ አሁን ዲዲቲ ማምረቻ እንደሆነ ታውቃለህ?!" አለ። በጊዜው ተቆጫበርኩ። ተቀየምኩት መሰል። "ከዚህም የባሰ እንዳለ" የገባኝ ግን ወዲያው ነበር።

ባለመኪና ለመባል ቮልስ የሚገዛ ተሸውዷል። ምክንያቱም ማንም ባለመኪና አይለውም። እንበልና መኪናዋ የቆመችው መንገድ ዘግታ ቢሆንና ሹፌሩ ባይኖር "ማነው የዚህ መኪና ባለቤት" አይባልም። ባይሆን፣ "ይቺ ቮልስ የማናት" ይባል ይሆናል።
 

የሆነ ሰሞን፣ «አሮጌ መኪኖች ከመንገድ ይወጣሉ» የሚል ስር የለሽ ወሬ ሰምተን ሰጋን። የቮልስ መካኒካችን ስናማክረው ወሬውን እንዲህ ብሎ አጣጣለው። " አሮጌ መኪና ይገባል እንጂ መቼም አይወጣም። መንግስት እራሱ አሮጌዎቹን የሚተካበት አዲስ መኪና መች አለውና?"

(እውነቱን ነው፤ ሌሌሎች አርጅቶ የተጣለ ለእኛ ግን የክት ነው። ያገለገለ እቃ ዋጋውን የሚያጣበት የገበያ ደንብ በተናደባት አገር እንኳን ያገለገለ መኪና ቀርቶ የተለበሰ የውስጥ ሱሪም ዋጋ አለው።)


ሹፌሮች ቀበቶ ሳያደርጉ ማሽከርከር በትራፊክ ደንብ መተላለፍ እንደሚያስቀጣ ደንብ ወጣ። ታዲያ ያኔ፣ በቮልስ ባሉካዎች ዘንድ ታላቅ ድንጋጤ ተፈጠረ!

ቀበቶ ባልታሰበበት ዘመን የተመረቱ መኪናዎችን ባለቀበቶ ለማድረግ ሩጫ ተጀመረ። የደህንነት ቀበቶ ግን ዋጋው ጣሪያ ደርሶ ነበር። አንድ ወዳጃችን ግን ሁነኛ ዘዴ ፈለሰፈ። የሻንጣ ማንገቻን ቆርጦ እንደቤልት የመጠቀም መላ። የፈጠራ ባለመብት እንደሆነ የቮልስ ቺፍ መካኒኩ አረጋገጠለት።

"ዳሩ ምንያደርጋል" መሀል አደባባይ ላይ በትራፊክ ፖሊሶች ተያዘ። ትራፊኮቹ የፌክ ቀበቶውን ከመኪናው አስፈትተው አላገጡበት። "የደህንነት ቀበቶ ከሌለህ ማንገቻ ያለው ሱሪ ብታደርግ ይሻል ነበር¡" እንዳሉት ነገረን ። ሳቅን።

"ስንት ብር ተቀጣህ?" ሲል ከመሃከላችን አንዱ ጠየቀ።
"አልቀጡኝም። 'ብንቀጣህ ከሌላው ሹፌር እኩል ትሆናለህ፤ ብትቀጣ የምትከፍለውን ብር አሁኑኑ የደህንነት ቀበቶ ግዛበት'— ብለው ለቀቁኝ።"
 

«የአሮጌ መኪናህን መካኒክ ጓደኛህ አድርገው።» የቮልስ ፍቅር ማደሪያ ልቡ ያለው ያው ጋራጅ ነውና።

አንድ ሰሞን ቮልሴን ለማስጠገን ጋራጅ እመላለስ ነበር። ጋራጅ የሚያስኬደኝ የመኪናዋ መበላሸት ብቻም አልነበር ። ጤነኛ ስትሆንም ያሳስበኛል።【ሳትበላሽ ከሰነበተች በቀላሉ የማይጠገን ከባድ ብልሽት እንደሚጠብቀኝ እርግጥ ነው】።

ሌላው ጋራጅ ሳልሳለም እንዳልውል ያደረገኝ ምክንያት፣ ከቮልስ ባሉካዎችና መካኒኮች ጋር መወዳጀቴ ነበር። 

አያሌ ፍተላዎች ከጋራጅ ይወለዳሉ። ተረቦች ነፍ ናቸው። ከመካኒኮች ጋር መዋል ያስደስታል። ጨዋታቸው፣ ትርርቡ፣ ልግጡ፣ … አይጠገብም።

ሞተራቸው በቁልፍ የማይነሳና በግፊ ተመንጭቀው ከሚነሱ ቮልሶች የተቀዳ አንድ አባባል አለ። «መንጭቀው ይነሳል!»  የሚል። አንድ ቀን እዛው ጋራጅ ውስጥ በሃይል አስነጠስኩ። ማንም «ይማርህ» አላለኝም። በምትኩ ግን «መንጭቀው ይነሳል!» የሚል ድምፅ ተሰማኝ።

ይሄ ድምፅ እስከዛሬም ድረስ፤ የቆምኩ ሲመስላቸው እንድነሳ ከሚገፉኝ አነቃቂ ሰዎች አንደበት ይሰማኛል።

"መንጭቀው ይነሳል!!"

ሰኞ 7 ጁላይ 2014

"የሃብታም ልጅ " ፍለጋ

በኄኖክ ስጦታው

አብሮ አደጌ ነበር። አብረን ብናድግም ቅሉ፣ አብረን ግን አንድም ቀን ቁም ነገር ተጫውተን አናውቅም። እንደው ርግጫ ወደጨዋታ ከተጠጋጋም፣ ከተጫወትነው ትዝ የሚለኝ "ሹሌ" ብቻ ነው።

ዛሬ ይህ ሰው ያደኩበት መንደር "እግረኛ ትራፊክ" ሆኗል።

በየመንደሩ አያሌ እግረኛ ትራፊኮች አሉ። እንኴን አብሮ አደጋቸውን በመልክ የሚያውቁትን በፈለጣ የሚቀጡ።

ርግጥ ነው፤ የፈለጣ ቴክኒኮች "በስማ በለው" ከአንዱ ፈላጭ ወአሌላው ይተለፋሉ። ( እንደ ስነቃል በፅሑፍ አልሰፈሩም።)

የትውልድ መንደሬ አስቁሞ ፈላጭ ከየት መጣ ሳይባል ከች አለ። (መንገድ ዘጋብኝ ማለት ይቀላል መሰል!)

ፈገግታው ልዩ ነበር። (በናፍቆት የጦዘ ፈገግታ :D ) ፊቱ ላይ ያለው ፈገግታ… "ይሸጣል!" የሚል ማስታወቂያ ቢለጠፍበት የሸማቹን አጀብ አስቤ "አማተብኩ"።

ሰላምታ ተለዋውጠን፣ የፈገግታው ወላፈን በርዶ፣ እጅ ለእጅ መወዛወዛችን ጋብ ብሎ… ከዚህ ሁሉ በዋላ መንገድ ጀምረን ለጨዋታው አዝማች ፣ "ኑሮ እንዴት ነው?" ስለው… ፊቱ በመቅፅፈት ተፈጠፈጠ። (እደዚህ ዓይነት ተለዋዋጭ ፊት ማግኘት መታደል ነው¡)

"ምነው?" ብዬ ጠየቅኩት።

"ምን እዚህ አገር ላይ እየኖርክ ለብቻህ ለውጥ አታጣውም።…" አለና ለመጀመሪያ ጊዜ የምር የሚመስል ጨዋታ ያመጣ መሰለኝ። ቀጠለ:– "መቼስ ላንተ አልነግርህም፤ ዘመኑን ታውቀዋለህ፤ ካለው ተወለድ፤ ወይም ካለው ተጠጋ። ካልሆነ ግን በእንጀራ አባት እንደኔ ስትሰቃይ ትኖራለህ… " አለኝ።

(የሰበቡ ድምዳሜ ፈለጣ ነውና ዘለልኩት) ከሃብታም ቤተሰብ ተወልዶ ድህነቱን የሚያምን እርሱ ሃብታም እንደሆነ አምናለሁ።

የሃብት መለኪያው ባለን እና ፣ እንዳይኖረን ባረግነው እንጂ፣ በኖረን እና በእንዳይኖር ባረግነው ግብአት አይሰፈርም።

በመሰረቱ ሃብት ያከቸው ሃብታም ቢባል ቅሬታ የለኝም። "የሃብታም ልጅ" መባል ግን ከአድናቆትነቱ ይበልጥ ስድብነቱ ያመዝንብኛል። ያልሆነ፤ ግን ሆነዋል ከተባሉት የተወለደ በመወለድ ብቻ ያለው መመቻመች "የወራሽነት" መብት ነውና "እጩ ወራሽ" ቢባል ይመጥነዋል…


አብሯደጌ ቅፈላውን ገፋበት። "… አየህ፣ ሥራ የለም። ብራሞችም እኛ ችስታዎችን አያስጠጉንም።…"

የገንዘብ የማጣት ችግርን ማስታገሻ ስሞች የኅብረተሰብ ውስጣዊ ማንነት መገለጫ ከመሆን አይድኑም። አንድ ብር ዋጋ እንደዛሬ በአንድ ሳንቲም ሳይተካ በፊት እነ "ሺ ብሬ" ተወልደዋል። የብሩ ዋጋ እየወረደ ሲመጣ ደግሞ እነ "ሚሊዮን" ተወለዱ። አሞሌ ጨው ብር በነበረበት ዘመን የኖሩ ሰዎችን መጠሪያ ስም ብናጣራ "አሞሌ" እና "አሞሊት" ተብለው የሚጠሩ አይታጡም።
★ ★
አንድ የመጨረሻው የድህነት ወለል በታች ተነስቶ ወደ ታላቅ "ቅንጦት" የተሸጋገረ አባት፣ በ14 ዓመት ልጁ ይህን ጥያቄ ተጠየቀ:— "ድህነት ምንድነው?"

አባት መልሱን ወዲያው አልተናገረም
ድህነትን ሳያውቅ ለኖረው ልጁ በተግባር ሊያስተምረው አሰበ። እናም በጉብኝት ሰበብ ገጠር ወደሚኖሩት ዘመዶቹ ዘንድ ላከው። ልጁ ከሳምንት በኋላ ሲመለስ :—

"እንዴት ነበር ጉብኝት?" ሲል ጠየቀው።

"በጣም ደስ የሚል ጊዜ ነበር " አለ ልጁ።

"እና ምን ተገነዘብክ? " አባት ሌላ ጥያቄ አስከተለ።

"የላከኝ አገር የሚኖሩት ሰዎች እኛ ከምንኖረው የተለየ አኗኗር አላቸው። እኛ በግንብ በታጠረ ጠባብ ግቢ ውስጥ በብዙ ዘበኛ አገልጋዮች ተከበን እንኖራለን፤ እነርሱ ግን በነፃነትና ባልታጠረ ሰፊ ቦታ ላይ ይኖራሉ። አንዱ የሌላው ጠባቂ እንጂ፣ እንደኛ ዘበኛ አይቀጥሩም።

"እኛ ሁለት ውሾች አሉን፤ እነርሱ ግን ብዙ አላቸው። እኛ ሚጢጢ የዋና ገንዳ ስንቦራጨቅ፤ እነርሱ ግን ትልቅ ወንዝ ውስጥ ይዋኛሉ። እኛ ከገበያ የምንገዛቸውን አትክልቶች ፤ እነርሱ ግን ከጓሮ ይቀጥፋሉ። …"

"እና ድህነት ምን እንደሆነ አሁን ተመለሰልህ? " አለ አባት።

"በሚገባ ተመልሶልኛል። እኛ ምን ያህል ድሆች እንደሆንን አውቄያለሁ" አለ ልጁ።

★ ★

አብሮ አደጌ በቀላሉ እንደማይፋታኝ ገብቶኛል። የጀመረውን ሃሳብ ሳይጨርስ ወደሌላው የሚሻገርበት ፍጥነት ይደንቃል።

"… የምሬን ነው፤ አንዷን ልጥጥ ካልተጃለስኩ ከዚህ ሲዖል አልወጣም!" አለ።

"ወንድሜ፤ ገንዘብ አይቶ ከመጃለስ፣ ቁልቋል ታቅፎ ማደር ይቀላል።"
★ ★

አቋራጭ መንገድ ፍለጋ ረጅምና አስቸጋሪውን መንገድ መጓዝ መርጧል። ጥገኝነት የሕይወት መንገዱ ነው። ከሰዎች የሚፈልገው ብዙ ነው። ለሰዎች የሚሰጠው ግን ምንም።

እጅግ ሀብት ካላቸው ቤተሰብ የተወለደ አንድ ወዳጅ አለኝ። —‘የሃብታም ልጅ‘ ሲሉት ይቆጣል። "የሚያኮራው ሃብታም መሆን ነው።" ይላል። ዋናው ጥያቄ ይህ ነው:— ጥገኛ ሃብታም፣ ወይስ ጥገኛ ድሃ?

ሕይወት ሙሉ ናት። የጥገኝነት ተፅእኖ ግን የሌሎችን እንጂ የራሳችንን እንዳናይ ጋርዶናል። ጥገኛ ምሑር፣ ጥገኛ ነጋዴ፣ ጥገኛ ባል፣ ጥገኛ ሚስት፣ ጥገኛ ተማሪ፣ ጥገኛ ተከራይ፣ የጥገኛ ጥገኛ ተጠጊ · · ·

ጥገኝነትን የሙጥኝ ያሉ ግንዛቤዎች በንሮ ዘዬያችን ውስጥ ሰልጥነውብናል። የስብሰባ አዳራሾች "የኔም ሃሳብ እከሌ እንዳለው ነው—" በሚሉ ተሰብሳቢዎች ይጨናነቃሉ። የሊቃውንት ስም ካልጠሩ ከእውቀት መዝገብ የሚፋቁና የሚጎድሉ የሚመስላቸው "ምሁራን" ከስራቸው አያሌዎችን "ይቀርፃሉ"። መሪ ቢቃዥም ባይቃዥም፣ ለራሳቸው ያልገባቸውን ለማስፈፀም የሚታትሩ ትጉህ ሸምዳጅ "አስፈፃሚ" ጥገኞችም "ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው¡"።

አዎ ጥገኞች ነን። ስንጠላ የጥላቻ፣ ስንወድም የውዴታ ጥገኛ ነን። ስንወለድ የወላጅ፣ ስናረጅም የልጆች ጥገኛ ነን። የተቃራኒ ዓለም ሰዎችም ነን። ቅሪት የቋጠረ እየፈራ፣ ቅሪት አልባው የሚጀግንበት። ለውጥ አልባ ጥገኞችም ነን። ስንወጣ የመውረድ፣ ስንወረደድ የመውጣት ውትብትብ ለመቀበል ያልበቃን ጥገኛ ድሆች።

ድሃው ማነው? ሃብታሙስ?

ድህነት የገንዘብ ከሆነ በሰለጠኑት አገራት ተሰደው ያሉ ወገኖች የመጨረሻውን ድሃ የማይሰራውን ስራ ሰርተው ሲመጡ ሃብታም የምንላቸው ለምንድነው? ሃብታም ስለነበሩ? ሃብታም ስለሆኑ? ወይስ እኛ ከእነርሱ በታች ድሃ ስለሆንን?

በፍፁም፤ ድህነት ስታስቲክ እንጂ እውነታ አይደለም። ሃብታምም ሆነ ድሃ ለቁጥር አይመቹም። "ከሃብታም" ጋር የተመሳሰሉ ድሆች "ከበርቴ" ይሰኛሉ። "ከድሃ" ጋር የተማሰሉም "ከበርቴዎች" እንዲሁ "ምንዱባን" ይባላሉ። የቱ ነው ትክክል? ቆጣሪው ወይስ ተቆጣሪው?

በእድሜ ዘመኑ ከፍሎ በማይጨርሰው ብድር ተዘፍቆ ሃብታም ከተሰኘው አባት ለተወለደ ልጅ ሃብት ምንድነው? እድሜ ዘመኑን ድህነቱን አምኖ በጠኔ ከሚጠበስ ቤተሰብ ለተወለደ ልጅስ ድህነት ምኑ ነው?

ረቡዕ 11 ጁን 2014

አክስት አዛሉ - (ኄኖክ ስጦታው)

አክስት አዛሉ


እውነተኛ ስሟአዛለችይሰኛል፡፡ እኛ ቤተሰቦቿአንቺየሚለውን ድምፀት ከአንደበታችን ለማጥፋትአዛሉብለን በመጥራት አንቺን ከአንቱ አስታርቀነዋል፡፡

አዛሉ ሞባይል የያዘች ሰሞን ጥቂት ተቸግራ ታስቸግረን እንደነበር አይረሳኝም፡፡ በተለይየቴሌዋ ሴትዮብላ ከምትጠራት ጋር ያነበራት ጠብ እጅግ የከረረ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡

አዛሉ፣ በሞባይል ስልኳ ስትደውል (የቴሌዋ ሴትዮ) ... “የደወሉላቸውን ደንበኛ አሁን ማግኘት አይችሉም...” ስትላት ነው መሰል እንዲህ ስትል ሰምቻታለሁ፡-

ምነው እቴ! አሁን ብታገናኚኝ ክብርሽ አይቀንስ...”

አዛሉ ሚሴጅ ሲደርሳትምየቴሌዋ ሴትዮትብጠለጠላለች፡፡እንግሊዝ ያስተማረችኝ አይመስልም አሁን?! ጉድ እኮ ነው! አበስክ ገበርኩ..... እስቲ ይህች ሴትዮ ምን እንደምትል አንብብልኝ...” ብላ ስልኳን ትሰጠኛለች፡፡ በቁጥር ስህተት ካልሆነ፣ አልያም የቴሌዋ ሴትዮ ካልተላከላት በቀር፣ ከማንም መልዕክት ደርሷት አያውቅም፡፡

እናም መልዕክቱን አነብላታለሁ፡-

“Dial *808*3# and call up to 6o minutes for only Br 4.99 or *808*4# for unlimited calls with only Br 9.99 from 11:00PM -6 :00AM (NIGHT TIME).”

ደግሞ አሁን፣ ምን አድርጉ ነው የምትለው?” ትላለች አፏን በሽርደዳ መልክ እያሞጠሞጠች፡፡ እንምንም ላስረዳት እጥራለሁ፡፡ እስኪገባት ድረስ ግን ታግሳ አትሰማኝም፡፡ ተቋርጠኝና፤

መልሰህ ላክላት! ʿእንኳን ዘንቦብሽ እንዲሁም ጤዛ ነሽʾ ብለህ ላክላት!” ትላለች እየተንጨረጨረች፡፡ ከንዴት ጋር ያላት ቅርበት፣ ለማወቅ ካላት ትዕግስት አልባነቷም ያይላል፡፡

አክስት አዛሉ፣የቴሌዋ ሴትዮከምትላት ባላንጣዋ ጋር ሳትነታረክ ውላ አታውቅም፡፡ አንዳንዴ፣ያለዎት ቀሪ ሂሳብ አነስተኛ ነው... እባክዎን ተጨማሪ ሂሳብ...”  የሚለውን ንግግር ትሰማና መልስ ትሰጣለች፡፡

እሺ፣ እሞላለሁ፡፡ እኮ ምን አለብሽ?! እኔ በሞላሁት ካርድ የምታወሪው አንቺው....”

አንድ ጊዜየቴሌዋን ሴትዮድምፅ መስማት -- ብሏት እንዲህ በማለት የጠየቀችኝ አይረሳኝም፡-

እንደው ይህቺን ሴትዮ የሚተካ አንድ ደህና ወንድ በአገሩ ጠፍቶ ነው እንዲህ ቀን ተሌት ቦርቂባቸው ብለው የለቀቁብን?! ”

አክስቴ፣ምን ወንድ አለ ብለሽ ነው....” እላታለሁ ነገሯ እንዲራዘም ስለምፈልግ፡፡


እውነት ብለሃል! ይህ መንግስት ሴቱን የሚያደራጀው ለምን ሆነና?! ወንዱንማ ደርግ ጨርሶታል....”

ረቡዕ 14 ሜይ 2014

የበርሃ አንበጣ - አማራጩ የምግብ ግብዓት


በኄኖክ ስጦታው

ዛሬ የሰፈራችን ሕፃናት ሰማዩን ከወረሩት አንበጣዎች በላይም መነጋገሪያ ለመሆን በቅተዋል፡፡ (“አንበጣ ናቡና ጠጣ . . . ” እያሉ ለመጀመሪያ ጊዜበአማርኛሲዘምሩ ተሰምተዋል፡፡ ከዚህም በላይ፣ አንገብጋቢው የስኳር እጥረት ችግርን አስመልክተው እሪታቸውን አሰምተዋል፡፡) በነገራችን ላይ፣ ከዚህ መዝሙር ውስጥ አንድ ስንኝ ይገርመኛል፡፡ስኳር የለኝም እንዳትቆጣ...” ጥንትም የስኳር ችግር ነበር፤ ዛሬም እንዲሁ፡፡ (ማን ያውቃል¡ ግንባታ ላይ ያሉት - በለስ፣ ተንዳሆ፣ ኩራዝ፣ ወልቃይት. . . ስኳር ፋብሪካዎች ሥራ ሲጀምሩ መዝሙሩ ይለወጥ ይሆናል፡፡)

አንበጣ

የሰው ልጆች፣ አማራጭ ነፍሳትን በመመገብ የምግብ ግብዓቶቻቸውን አስፍተዋል፡፡ እነ ጉንዳን በቆሎ እና በቋንጣ መልክ እጅ የሚያስቆረጥም መብል መሆናቸውንም እየሰማን ነው፡፡ የተባበት መንግስታት ድርጅት እንዳው ከሆነ፣ እንቁራሪትም ሆነ ትላትሎችን መመገብ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አማራጭ የሌላቸው መፍትሔዎች መሆናቸውን አሳስቧል፡፡

መጥምቁ ዮሐንስ እንኳን በዘመኑ የበርሃ አንበጣዎችን በመብላት ሰብላችንን የሚበሉትን እንበላቸው ዘንድ ምሳሌ ሆኖ አልፏል፡፡ አንበጣ ከገብስም በላይ ለሰውነት ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች አሉት፡፡

በጥንት ጊዜ አንበጣ በአሦራውያንና በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተወዳጅ ምግብ እንደነበረ ታሪክ ዘግቦታል፡፡ አንዳንድ የአረብ ዘላኖችና የመናውያን አይሁዶች አንበጣ ይበላሉ ነበር፡፡ በእስራኤላውያን ዘንድ አንበጣ የድሆች ምግብ ተደርጎ ይታይ ነበር።

አንድ ስለአንበጣ የወጣ ማስረጃ እንደሚለው፤አንበጦች 75 በመቶ የሚያህል ፕሮቲን ስላላቸው አንድ ሰው አንበጦችን ከዱር ማር ጋር ቢበላ የተመጣጠነ ምግብ ያገኛል።በነገራችን ላይ አንበጣ ለመብልነት ለማዋል ቀላል ነው፡፡ ታዲያ ዛሬ ለምን አንበላውም?! አሰራሩን ለማታውቁ እነሆ በረከት፡-

በመጀመሪያ የአንበጣው ራስ፣ እግሩና ሆዱ ከተወገዱ በኋላ ቀሪው ክፍል ይኸውም ደረቱ ጥሬውን አሊያም ተቆልቶ ወይም በፀሐይ ደርቆ ሊበላ ይችላል፡፡ አንበጣ፣ በጨው ታሽቶ አሊያም በኮምጣጤ ተዘፍዝፎ ወይም በማር ተለውሶ ለመብልነት ሊውል ይችላል፡፡ (ይህ የሚሆነው ግን ለዲዘርት ነው፡፡ ለራበው ሰው ጥሬውን ቢበላ ይመረጣል፡፡)

መልካም ገበታ!

*Share . *Comment .*Invite Your Friends to Like This Page
[የኄኖክ diary ] https://www.facebook.com/henokspad

ቅዳሜ 10 ሜይ 2014

ወጣትነት አቁሮ የማቆየት ግፊት - በ ኄኖክ ስጦታው

ወጣትነት አቁሮ የማቆየት ግፊት

ሰው እድሜውን የሚደብቀው ለሁለት ምክንያት ይመስለኝ ነበር፡፡ በግዳጅ ጦር ሜዳ ከመዝመት እና ጡረታን ፍራቻ ፡፡ አሁን ግን ብዙ ምክንያቶች ይታዩኛል፡፡ ከጥቃቅን ሰበባ አስባቦች በላይ ወጣትነትን ባለበት አቁሮ የማስቀረት ግፊት ማየል ሰፊ ሃተታ ቢወጣውም በስሱ ቃኘሁት፡፡
***
ትልቅ ለመሆን የተመኘንበት የልጅነት ሲዝናችን በዕድሜ ዑደት ተሽሮ ለጉርምስና ቦታውን ይለቃል፡፡ ጉርምስና እሳት ነው፡፡ ነዶ ለማለቅ ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ አመዱን ትቶ ቦታውን ለወጣትነት ይለቃል፡፡ የሚግለበለበውን የእድሜ እሳት ለማርገብ የውሸት ውሃ መቸለስ የሚጀመርበት ሲዝን፡፡
ዕድሜ ግን አሪፍ አርቲስት ነው፡፡ ሌሎችን ለማሳመን የዋሸነውን ስዕል ሙሉ በሙሉ ሰርዞ የራሱን እውነተኛ ምስል እኛው ላይ የሚጠበብ ድንቅ አርቲስት! ዕድሜ፣ ተፈጥሯዊ ማስተባበያውን አካላችን ላይ በመሳል ጉዞውን ይቀጥላል፡፡ እኛም ስዕሉን በሌላ ስዕል (ሜካፕ) ለማጥፋት እንጥራለን፡፡ ነጩን ስናጠቁር፣ ጥቁሩን ስናቀላ፣ የተጨማደደውን ስናቃና፣ የወደቀውን ስናነሳ፣ የረገበውን ስንወጥር፣ የበለዘውን ስናነጣ፣ . . .
***
ልደቷብለን ቅፅል ስም ያወጣንላት ጓደኛች አለችን፡፡ ቆንጆ ናት፡፡ ጭሰት የማይታክታት ቆንጆ፡፡ ፍቅረኛ አይበረክትላትም፡፡ አቤት! ከአንዱ ወደሌላው ለመሸጋገር ያላት ፍጥነት! “ፍቅረኛዬ ነውብላ ያስተዋወቀችን ወንዶች ተመሳሳይ የሚያደርጋቸው አንድ ነገር አለ፡፡ ልደቷን በፌሽታ ያከብሩላታል፡፡ አድሜዋንም ሆነ የተወለደችበት ቀን ግን ከራሷ በቀር በትክክል የሚያውቅ የለም፡፡ልደቷን በአመት ውስጥ አራት አምስቴ ልታከብር ትችላለች፡፡ (ቁጥሩ የሚወሰነው በአመት ውስጥ በተጃለሷት ወንዶች መጠን ነው)፡፡ ዕድሜዋ ግን ጨምሮ አያውቅም፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ እንደ ሰዓት ወደኋላ አድርጋ የሞላችው ይመስለኛል፡፡
(በአንዱ የልደቷ ፓርቲዋ ላይ በብዙ ጉትጎታ ተገኝቼላት ነበር፡፡ ቦሌ መስመር ካሉ አንድ ክለብ ውስጥ ነበር ድግሱ፡፡ ደጋሹም አዲሱፍቅረኛ፡፡ ሸከከኝ፡፡እጮኛዬን ብሉልኝ እጮኛዬን ጠጡልኝ፤ ፍቅረኛዬን አጫርሱኝ. . .” ብላ የጋበዘችኝ መሰለኝ፡፡ በቃ፤ ማንም ሳያየኝ ሹልክ ብዬ ወጣሁ፡፡ )
በሌላ ቀን ሳገኛት እንዲህ ስል ጠየቅኳት፡- “አዲስ ፍቅረኛ በያዝሽ ቁጥር ለምንድነው ልደትሽን እንዲያከብሩ የምታደርጊያቸው?!”
መልሷ በናቲ ዘፈን አሳወቀችኝ -
በቃ፤ በቃ፤ ዛሬን ኑር በቃ! . . .በቃ!
ለምንድነው የምትጨነቃው...
በቃ . . . . .”
በቃ! ይህ ሁሉ ልደት ለዚሁ ነው በቃ! የሁሉ መዝናናት ለዚሁ ነው በቃ! ይህ ሁሉ መነ....(እንዝለላት በቃ፡፡)
***
ኮመዲያን ልመነህ ታደሰንአዲስ ቪው ሆቴልበረንዳ ላይ ነበር ያገኘሁት፡፡ ጥቁር በጥቁር ለብሷል፡፡ ጥቁር ቦርሳ ... ጥቁር ባርኔጣ ...፡፡ . አድናቆቴን ስነግረው በትህትና አመስግኖ ተቀበለኝ፡፡ በርግጥ መታመሙን በሚደያ ሲነገር ሰምቻለሁ፡፡ ሕመሙ ግን የማገናዘብ ብቃቱና እና ጨርቁን አላስጣለውም፡፡
አንድ ነገር ግን አስተዋልኩ፡፡ ፀጉሩ ላይ ሽበት አይታይም፡፡ በርሱ እድሜ ካሉትም አንፃር ልመነህ አሁንም ወጣት ነው፡፡ ለጨዋታ በር መክፈቻ እንዲሆነኝ ስል ወጣትነቱ ጠብቆ የቆየበት ምስጢር ምን እንደሆነ ጠየቅኩት፡፡
(በመልሱ ተመራመሩበት፡፡)ትኩር ብሎ አይቶኝ ሲያበቃ እንደህ ሲል መለሰልኝ፡-
ቀላል ነው፡፡ ዕድሜህን እያሰብክ አትቁጠረው፡፡ እንዲያውም ፈፅሞ እድሜህ ስንት እንደሆነ እርሳው፡፡

ቅዳሜ 3 ሜይ 2014

የ“ሸኖ ቤት ሃሳቦች” #ኄኖክ_ስጦታው



ሸኖ ቤት ሃሳቦችየማንበብ ሱስ የተጠናወተኝ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ነበር፡፡ በርግጥ ብዙዎቹ ሃሳቦች በጨዋ ቋንቋፀያፍተብለው የሚነገሩ ቢሆንም ብሶትና ምክርን በጨዋ ገለፃ የሚቀርቡ ሃሳቦችም አይታጡም፡፡ ያም ሆኖ ሕዝብ የሚጠቀምባቸው መፀዳጃ ቤቶች ስገባ በግድግዳው ላይ የተጻፉ ጽሑፎችን ማንበብ ያዝናናኛል፡፡

ሸኖ ቤትን ለመውደድ የፎክሎር ተማሪ መሆን አይጠይቅም፡፡ ከማይረቡ መፅሐፍት የተሻለ ምልከታን እና ሂዩመርን በሸኖ ቤት ሃሳቦች መቃረሜ በራሱ ለመፀዳዳት የማባክነውን ጊዜ የሚክስ ቁምነገር አላጣበትምና፡፡

የዘርሲዎች ፍቅርየተሰኘው ልቦለድ መፅሃፍ ላይ አንድ ገፀባሕርይ አስታውሳለሁ፡፡ በተለይ መፀዳጃ ቤት ስገባ ብዙ ጊዜ ትዝ ይለኛል፡፡ (አብሮኝ ይገባል - - ብል ይቀላል፡፡) ይህ ሰው ቁምነገርን የሚቃርመው ከመፀዳጃ ቤት ነው፡፡ ግድግዳ ላይ የሚጻፍ ግራፊቲ አልነበረም የሚያነበው፡፡ ሰዎችካካቸውንየጠረጉበትን ወረቀት ሰብስቦ ኪሱ በመክተት እና በማንበብ ነበር፡፡

እነዚህ የግድግዳ ላይ ጽሁፎች ስለምንስ ይጻፋሉ? ግባቸው ምንድነው? ... ምክንያቱን እርሱት፡፡ ከየት መጡ የሚለው ምርምር አያሳስበኝም፡፡ ባለቤት አልባነታቸው በራሱ በቂ ምክንያት ነው፡፡ ምክንያት ከስም ይጀምራልና፡፡ ማንነቱን ለማወጅ የመፀዳዳት ባህሉን አደባባይ ላይ ከሚፈጣጥም ሰው ምንም አልጠብቅም፡፡ ማንነቱን በመጸዳጃ ቤት ግድግዳ ላይ የሚያሰፍር ማንነቱ ያልታወቀ ሰው ግን ታዳሚ ነኝ፡፡ (እስቲ ዛሬ የተመረጡ ትውስታዎቼን በሹካ ጨልፌ ላካፍላችሁ፡፡)

ለመጀመሪያ ጊዜ ካነበብኳቸው ውስጥ የሚመደብ የመፀዳጃ ቤት ሃሳብ እንዲህ የሚል ነበር፡-

“God is dead!” -Nietzshce
“Nietzshce is dead!” -God

ያኔ ይህን ሳነብ ያልገባኝ ብዙ ነገር ነበር፡፡ በርግጥ ኒቼእግዚአብሔር ሞቷልበሚለው ግንዛቤው ዛሬም ድረስ (ሞቶም) ያወዛግባል፡፡ በሕይወት በነበረበት ጊዜእግዚአብሔር ሞቷል ሰዎችም ነፃ ወጥተዋል...” እያለ መስበኩን የተረዳሁትም ከጥቅሱ በኋላ ነበር፡፡ አመታት አልፈው፡፡ የኒቼን ሞት ጠብቆ እግዚአብሔር እንዲህ ማለቱን ግን መፀዳጃ ቤት እንደ ትንቢት ቀድሞ አሳውቆኛል፡፡ ጥበብ ከጲላጦስ መፅሐፍ ላይ ይህን ጥቅስ ሳነበው አልደነቀኝም፡፡ ጥቅሱን ሲያስታውሰኝ ግን የሆነ ነገር ግን ሸቶኝ ነበር፡፡ ያም ጠረን፣ ይህን አባባል ያነበብኩበት መፀዳጃ ቤት አጉል ጠረን ነበር፡፡

በአንድ ኮሌጅ መጸዳጃ ቤት ውስጥ ደግሞ እንዲህ የሚል መልዕክት ግድግዳው ላይ ተፅፎ አነበብኩ፡- “ምን ግድግዳው ላይ ታፈጣለህ!? አርፈህ አትፀዳዳም!?” ሆሆሆ... ሰዉ ጨምሯል!

በሌላ ዩኒቨርስቲ መፀዳጃ ቤት ውስጥም እንዲህ አይነት ትዕዛዝ አጋጥሞኝ እንደነበር አልረሳውም፡፡ በደቃቅ ጽሑፍ የተጻፈ መልዕክት ከመጸዳጃው በር ላይ ሰፍሮ አየሁና ከቅምጤ በመጠኑ ብድግ ብዬ ላነብ ስሞክር ያገኘሁት መልዕክት አስደንግጦየሚያስቀምጥነበር፡፡ሃሳቡ እንዲህ የሚል ነበር፡- “ሰው ማለት አንተ ነህ፡፡ አሁን ወደነበርክበት ተመልሰህ አርፈህ እራ! ” የሚል ትዕዛዝ ፡፡

የሸኖ ቤት ግድግዳ ላይ ከተፃፉ ሃሳቦች ሌላው የማርከኝ እንዲህ የሚል ነው -

ቺክህን ጥሩ ነገሮች እንዴት እንደምታሳያት በማሰብ አትጨናነቅ፡፡ አሁን እየጣልክ ያለውን እንቁላል ግን ጠብሰህ እንዳታበላት አደራ! ስትጨርስ ውሃ ድፋበትና ከሌሎች እይታ ሰውረው!”

የሸኖ ቤት ግድግዳ ሃሳቦች አንዳንዴም ፍልስፍና ይቃጣቸዋል፡፡ በአንድ የሕዝብ መፀዳጃ ቤት ውስጥ ያነበብኩትሃሳብ ለዚሁ ምስክር ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡-

[“መኖር ማለት፣ በምታባክነው ጊዜ የምታጣው ብኩንነት ነው፡፡ ለመኖር ስትል ከምታባክናቸው ሰዓታት ትልቁን ቦታ የሚይዘው ምን እንደሆነ ታውቃለህ?”

አውቃለሁካልክ ተሳስተሃል! በዚህ ሰዓት ማራት አልነበረብህም!!”]

ትውስታዬን ተደብቄ በተጠቀምኩበት የሴቶች መጸዳጃ ቤት ግድግዳ ላይ ባነበብኩት ልቋጭ፡፡


በወንዶች ከሚነገሩ - ውሸቶች መሃከል የማላምነውሮም በአንድ ቀን አልተገነባችምየሚሉትን ብቻ ነው፡፡


(›››› ሌሎች ጽሑፎችን በፌስቦክ ገጽ ለማንበብ ይህን አድራሻ ይጠቀሙ፡-  https://www.facebook.com/pages/የኄኖክ-diary/736486173038263