ዋ! አድዋ!
“Many died…[and] no one knows their names…but their names are written in Heaven, in the book of life…for they became martyrs…” The Mannawe Manuscript
“ብዙዎች ሞቱ ... [እና] አንዳችም ስማቸውን የሚያውቅ ሰው የለም ... ነገር ግን ስማቸው በመንግሥተ ሰማያት፣ በህይወት መዝገብ ላይ ተጽፏል ... ሰማዕታት ስለሆኑ ...”
*
አንድ ወቅት ላይ የኢጣሊያ መንግስት ስልጡን ለሆነው ህዝቡ አንድ እቅድ አቀረበ። የእቅዱ ስያሜ “የኢጣሊያ ክቡር ተልዕኮ” ይሰኛል። “ክቡር ተልእኮ” ምንድነው?!
ኢጣሊያ፣ የውስጥና የውጭ ችግሮቿን ለመፍታት ከነደፈቻቸው እቅዶች አንዱ በአፍሪካ ውስጥ ያላትን የቅኝ ግዛት ማስፋፋት ነበር። በ1860ዎቹ(እኤአ) ውስጥ በኢኮኖሚ መዋዠቅ ውስጥ ለተዘፈቀችው ኢጣልያ “ክቡር ተልእኮ” ታቀደ። የገጠር ነዋሪዎች እና በድህነት ውስጥ ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢጣልያውያን የተሻለ ሕይወት ለመፈለግ ሀገራቸው መሰደዳቸውን ለማስቀረት የኢጣሊያ ንጉሥ የሆኑት ንጉሥ ኡንቤርቶ በአፍሪካ የሚካሄደው ቅኝ አገዛዝን ይበልጥ ማስፋፋት ሁነኛ መፍትሄ ይሆን ዘንድ ተለሙ፤ እቅዳቸውም ከአገር ከመሰደድ ይልቅ ለአገር መሰደድ ላይ ያተኮረ ነበር። ስያሜውንም “የኢጣሊያ ክቡር ተልዕኮ” በሚል ገለፁት። ድህነት፣ ሥራ አጥነትና የውጪ አገራት ጣልቃ ገብነት ጫናን ለማስወገድ መፍትሄ ለመስጠት የቅኝ ተገዥ አገራትን በአፍሪካ ማስፋፋት እንደ ታላቅ መሳሪያ ተደርጎም የወረራው አቅጣጫ ኢትዮጵያ ላይ አተኮረ።” (A Plebano, Storia dela Fianza Italiana III, Turin, 1902)
የጦርነቱ መንስኤ
ሚያዚያ 1881 ዓ.ም. ንጉሥ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ውጫሌ በሚባለው ቦታ ሳሉ የኢጣልያ ልኡክ የሆነው አንቶኔሊ፣ ንጉሥ ምኒልክን ለማግኘት ውጫሌ ድረስ በማምራት በኢጣሊያኖች የተረቀቀውን ውል አቀረበ። የውጫሌ ውል ሃያ አንቀጽ ያለውን ሲሆን በኢጣሊያ በኩል በንጉሥ ኡምቤርቶ ተወካይነት አንቶኔሊ ሲፈርም፣ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ በዳግማዊ ምኒልክ ተፈረመ። ስያሜውም “የውጫሌ ውል” ተባለ።
ከዚህ ውል ውስጥ 17ኛው አንቀጽ በአማርኛው፣ “የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከአውሮጳ ነገሥታት ለሚፈልጉት ጉዳይ ሁሉ በኢጣሊያ መንግሥት አጋዥነት መላላክ ይቻላቸዋል” ሲል፣ በኢጣሊያኛው ደግሞ “የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከአውሮጳ መንግሥታት ለሚፈልጉት ግንኙነት በኢጣሊያ መንግሥት አማካኝነት ማድረግ ይገባቸዋል” ይላል። ይህ አንቀጽ ውሎ አድሮ በሁለቱ ሀገሮች መካካል የአድዋ ጦርነት ተብሎ ለሚታወቀው ጦርነት መነሻ ምክንያት ሆኗል።
ውሉም እንደ ጸደቀ፣ “ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ሥር ናት” የሚል ጽሑፍ በየጋዜጦቹ ላይ ታትሞ ወጣ። ይህንኑ መልዕክት የኢጣሊ ጠቅላይ ሚንስትር ክሪስፒ ጥቅምት አንድ ቀን 1882 ዓ.ም. ለአሜሪካና ለ12 አውሮጳ መንግሥታት አስታወቀ። በዚህ ሂደት ውስጥ ነበር ዳግማዊ ምኒልክ ሥርዓተ ንግሣቸውን ለማሳወቅ ደብዳቤ የጻፉላቸው መንግስታት፣ እንግሊዝና ጀርመን፣ ለአፄ ምኒልክ በጻፉት መልስ ላይ፣ በውጫሌ ውል መሠረት ግንኙነታችን በቀጥታ ሳይሆን በኢጣሊያን በኩል ብቻ ነው በሚል ያሳወቁት። ይህ ደግሞ አፄ ምኒልክን ይበልጥ አስቆጣ። የጣልያን አካሄድ የተለሳለሰ ቢመስልም ችግር ማስከተሉን የተመለከቱት አፄ ምኒልክ ጥር 19 ቀን 1882 ዓ.ም. ለኢጣልያው ንጉስ ኡምቤርቶ “ለአገሬ ውርደት እንደሆነ ደርሼበታለሁ…” የሚል መልእክት መላካቸውን “አፄ ምኒልክ እና የአድዋ ድል” የተሰኘው መፅሃፍ ይናገራል።
*
አፄ ምኒልክ የውጫሌውን ውል በተዋዋሉ በአራተኛው ዓመት፣ ለአውሮጳ ኃያላን መንግሥታት የውጫሌን ውል ማፍረሳቸውን የካቲት 4 ቀን 1885 ዓ.ም. በደብዳቤ አስታወቁ።
በህዳር 1886 ዓ.ም. የኢጣልያ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆነው ክሪስፒ፣ አንቶኔሊን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጸሐፊ፣ ጄኔራል ባራቲየሪን ደግሞ አዲሱ የኤርትራ ገዢ አድርጎ ሾማቸው። ጄኔራል ባራቲየሪ በ1886 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ ጦሩን እየመራ የኢትዮጵያን ግዛት ዘልቆ በመግባት የሰሜኑን ክፍል በኃይል መያዝ ጀመረ።
ጄኔራል ባራቲየሪ በ1887 ዓ.ም. ለዕረፍት ወደ ሮም ሲመለስ በጣሊያን ፓርላማ ተገኝቶ ንግግር ከማድረጉ በፊት፣ አባላቱ ከመቀመጫቸው ተነሥተው የደመቀ ጭብጨባ በመስጠት ተቀብለውታል። ንጉሡ ኡምቤርቶም ድል አድራጊው ጄኔራል ባራቲየሪን በማድነቅ የጣልያን ኃይልን “የሠለጠኑ የበላይነት ኋላ–ቀር በሆኑ ላይ” በማለት አወድሰውታል። ጄኔራል ባራቲየሪም “በጥቅምት ወር ጦርነት ይኖራል። የእኛ የሠለጠነው አሥር ሺህ ጦር ከሃያ ሺህ እስከ ሰላሳ ሺህ የሚደርሰውን ያልሠለጠነ የኢትዮጵያ ጦር በቀላሉ ያሸንፈዋል፤ የኢትዮጵያውን ንጉሥ በቀፎ አድርጎ ሮም ያመጣዋል” ሲል በኩራት ተናገረ። በቅኝ ግዛት መስፋፋት ምኞት ሕልም የሰከረው ፓርላማም ንግግሩን ከሰማ በኋላ የጄኔራሉ ዓላማ እንዲሳካለት ለአንድ ሺህ ተጨማሪ ወታደሮች መቅጠሪያ በጀት አፀደቀለት። ጄኔራል ባራቲየሪ በመስከረም 15 ቀን 1888 ዓ.ም. ተመልሶ ምፅዋ ገባ። በዘመኑ ከጣልያን የወገኑ ቅጥር ወታደሮችን ከአፍሪካ የመለመላቸው ሲሆን በቀን አንድ ሊሬ ከሽልንግ ይከፈላቸው እንደነበር “The Battle of Adwa: African Victory in the Age of Empire” የተሰኘው መጽሐፍ ይነግረናል።
ንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒልክም የውጫሌውን ውል ሲያፈርሱ፣ ከኢጣሊያኖች ጋር ጦርነት የማይቀር መሆኑን አውቀውት ስለነበር፣ ወታደሮቻቸውን ማዘጋጀትና ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን ከራሺያና ከፈረንሳይ በጅቡቲ በኩል ማስመጣት ቀጠሉ። በ1895 ዓ.ም. በአጠቃላይ ለዚህ ጦርነትዝግጅት አፄ ምኒልክ ከ70 -100 ሺህ የሚደርስ ዘመናዊ ጠብመንጃ እና 5 ሚሊዮን ጥይት መግዛት ችለው ነበር።
የክተት ዐዋጅ
የጦርነት አይቀሬነት ርግጥ ሲሆን ኢትዮጵያም ለፍልሚያ ተዘጋጀች። ዝነኛው የአፄ ምኒልክ የክተት አዋጅም ነጋሪት እየተጎሰመ ተለፈፈ።
“እግዚአብሄር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ ከእንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለእኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡ አሁንም አገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖትን የሚለውጥ፣ በፊት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል፡፡ እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ፤ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሃዘንህ እርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፡፡ አልምርህም፡፡ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም…”
(“አፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት” በተክለ ጻዲቅ መኩሪያ ገጽ 226)
የጦርነት ውሎ
ዘመቻው ጣይቱ ብጡል ከምኒልክ በላይ ግልተው የታዩበት ነበር። ጣይቱ ያስከተሉትን ጦር ይመሩ የነበሩት ባልቻ ከጦር መሪነታቸውም በተጨማሪ የምኒልክ ግምጃ ቤት ኃላፊ እና የዘውድ ጠባቂም ጭምር ነበሩ። ጣይቱ በሺህ የሚቆጠሩ ወታደሮች ብቻ ሳይሆን የሙዚቀኞች ቡድን ያቀፈ ስብስብ አካተው በሽለላና በፉከራ የታጀበ ቡድን ጭምር እንደነበር ታሪክ ይናገራል።
ጦርነቱ የካቲት 23ቀን 1888 ዓ.ም. ማለዳ ተጀመረ። በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ “የተተከለው ድንኳን ሲታይ ከብዛቱ የተነሣ አፍሪቃ አውሮጳን ለመጠራረግ የተነሣች ይመስላል፡፡ የጦርነቱ ዕለት ኢትዮጵያውያኑ ደማቅ ቀለም ያለው ካባ ለብሰው፣ የነብርና ያንበሳ ቆዳ ለብሰው አዝማሪዎቹ እየዘፈኑ፣ ቄሶች፣ ልጆች፣ ሴቶች ሳይቀሩ ፀሐይዋ ፈንጠቅ ስትል በተራራው ላይ በታዩ ጊዜ የኢጣሊያን ጦር አሸበሩት፡፡” ሲል ታሪክ ጸሃፊው በርክለይ ይገልፀዋል።
በጦርነቱ ላይ ከተሳተፉት የታሪክ ምስክሮች መካከል ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለማሪያም አንዱ ሲሆኑ “ኦቶባዮግራፊ” በተሰኘው ማስታወሻቸው ላይ የጦርነቱን ውሎ እንዲህ ሲሉ ይተርኩልናል፦
“ጠመንጃ ሲንጣጣ ሰማን፤ መድፍ ወዲያው ያጓራ ጀመር። ተኩሱ እያደር እየባሰበት ተቃረብን። ዐረሮቹ ማፏጨት ጀመሩ። የቆሰሉ ሰዎች ተቀምጠው አገኘን።… ጦራችን ተደበላልቋል። ሰውና ሰው አይተዋወቅም።… ሴቶች በገንቦ ውሃ እያዘሉ፣ በበቅሎቻቸው እንደተቀመጡ፣ ለቁስለኞች ውሃ ያቀርባሉ። ሲነጋገሩ ሰማኋቸው። “ኧረ በጣይቱ ሞት” ይላሉ።… ነጋሪቱ ከግንባርም፣ ከጀርባም፣ ከቀኝም፣ ከግራኝ ይጎሸማል። የተማረኩ ጣልያኖች አየሁ። ወዲያው ምርኮኞቹ በዙ። አንዳንዶቹ ወታደሮች ሦስት ይበልጥም ጣልያኖች እየነዱ መጡ። በኋላ የምርኮኞች ብዛት ለዓይን የሚያሰለች ሆነ። ድል ማድረጋችንን አወቅሁት። ጣልያኖች መዋጋታቸውን ትተው ማርኩን እያሉ ይለምናሉ።”
አክለውም፣ ጦርነቱ አልቆ እንኳን ወደግንባር የሚሄደው የሰው ብዛት እንደ ውሃ ሙላት እንደነበር ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ይገልፁታል።
“The Battle of Adwa: African Victory in the Age of Empire” መጽሐፍ ስለጦርነቱ ሲገልፅ፦
“የጣልያን ሠራዊት በመገስገስ ላይ የነበሩትን የኦሮሞ ፈረሰኞች በተመለከተበት ወቅት የሚገባበት ጠፋው፡፡ ቀድሞ በሠራዊቱ ውስጥ ስለኦሮሞ ፈረሰኞች የተነገራቸው ኋላ ቀር እና ተራ ተዋጊዎች እንደሆኑ ነበር፡፡ በጦር ሜዳ ላይ የተመለከቱት ግን ፈረሰኞች እጅግ ፈጣን እና የተካኑ መሆናቸውን ነበር፡፡
“የጀ/ል አርሞንዲ የበታች ከኾኑት መካከል ጂዩቫኒ ቴዶኔ ለሠራዊታቸው መሸነፍ ቁልፉን ሚና የተጫወቱት የኦሮሞ ፈረሰኞች መሆናቸውን መስክሯል፡፡ የወቅቱን አስፈሪ ሁኔታ ሲገልፅም “ፈረሰኞቹ ወደ ሽለቆሁ ሲወርዱ በድንገት የገነፈለ ጥቁር ባህር ይመስሉ ነበር” ብሏል፡፡ በወቅቱ ሌ/ኮ አጎስቲኖ ቺጉ ፣ ሌ/ኮ ሎኔንዞ ከምፕያኖ ፣ ሌ/ኮ ጊሊዮ እንዲሁም በመጨረሻ ራሱ ጀነራል አሪሞንዲ አንድ በአንድ መግደላቸውን ጠቅሷል፡፡
“በርካታ የጦር መሪዎች ራሳቸውን አጥፍተዋል፡፡ ል/ኮ ጋሪባልዲ ቬናዞ እና ሌ/ኮ ማዞሌኒ የኦሮሞ ፈረሰኞችን ጦርና ጎራዴ በመፍራት በራሳቸው ሽጉጥ ራሳቸውን አጥፍተዋል፡፡ ቴዶኔ ሁኔታውን ሲገልፅ በተለይ ኮ/ል ፔናዚ መጀመሪያ የተኮሰው ጥይት ስላልገደለው ለኹለተኛ ጊዜ ደረቱን በራሱ ጥይት መምታቱን ገልጿል፡፡ ራሱ ታዶኔ ቆስሎ የተማረከ ሲሆን ጦርነቱም በዚያው ተጠናቋል፡፡”
*
የአድዋ ጦርነት ድል አሸናፊ ይሆናል ተብሎ በተደመደመለት ኃያል መንግስት ተቃራኒ ሆነ። ድሉም በአሸናፊዎቹ ዘንድ ወራሪን መክቶ መመለስ ቢመስልም ውጤቱ ግን በሃያላን ሃገራት አስገድዶ ቅኝ የመግዛት ስርዓት እና ደካማ ሃገራትን ለመቀራመት በጉልበት የመግዛት ሂደት ውስጥ ለቅኝ ገዢዎችም ሆነ በቅኝ ተገዢነት ላሉት ሁሉ የማይታመንና አስደንጋጭ የዓለማችን ክስተት ለመሆን በቃ። “ጥቁር ሕዝቦች የባርነት ቀንበር ለመሸከምና ተገዢ ለመሆን የተፈጠሩ እንደሆኑ” ያምኑ የነበሩትንም ጭምር ቆም ብለው እንዲያስቡ ከማድረግም አልፎ ሽንፈታቸውን በግድ እየመረራቸው ለመመስከር አስገደደ። ይብስ ብሎም መጽሔቶች የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ሚኒሊክ የኢጣሊያን ንጉስ በጦር ሲወጉ የሚያሳይ የካርቱን ምስል አስደግፎ በመዘገብ አንድ ሃያል አገር “ኋላ ቀር “ እንደሆነ በሚታመን “ጥቁር ሕዝብ” መሸነፉን አወጀ። ይህኔ ነበር በግልጽ ለኢጣልያ ወግኖ የሚፅፈው የጆርጅ በርክሌይ ምስክርነት እንዲህ የቀል፦
“ከሰፊው የፖለቲካና የታሪክ ትንታኔ አኳያ የዐድዋ ጦርነት በአፍሪቃ ምድር አዲስ ኃይል መነሣቱን የሚያበስር ይመስላል። የዚህች አህጉር ተወላጆች፣ የማይናቅ ወታደራዊ ኃይል ሊሆኑ እንደሚችሉ ልናሰላስል ተገደናል።… ነገሩ አስቂኝ ቢመስልም፣ ይህ ሁኔታ (ማለትም ዐድዋ) ጨለማይቱ አህጉር በላይዋ ላይ ሥልጣኗን ባንሰራፋችው በአውሮጳ ላይ የምታደርገው አመፅ የመጀመሪያው ምእራፍ ነው…”
*
የታሪክ ተመራማሪው ባሕሩ ዘውዴ “የኢትዮጵያ ታሪክ” በተሰኘው ምርምራቸው ሥራቸው ላይ በገፅ 89 እንደገለፁት “ዐድዋ ልዩ ትኩረት ያሰጠው ጥቁሮች በነጮች ላይ የተጎናጸፉት የመጀመሪያው ዐቢይ ወታደራዊ ድል በመሆኑ ነው…።”
*