መሸ ደግሞ አምባ ልውጣ! በ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን


መሸ ደግሞ አምባ ልውጣ!

አምባ ወጥቼ እኩለ-ሌት ስለት ገብቼ በስሟ
ከርሞ ሰይጣን በሷ አስቶኝ፤ ልገላገል ከህመሟ
ጠበሏ አፋፍ በጨረቃ፤ ደጋግሜ፤ ማህሌት ቆሜ
ሆዴ ቃትቶ ባር ባር ብሎ፤እርቃኔን ከሷ ታድሜ
ደጀ ሰላሟን በአራት እግር፤ ተንበርክኬ ተሳልሜ
በስጋዬ እሚነደውን፤ በጸሎት ላቤ አጣጥሜ
እፎይ ብዬ አመስግኜ፤ ውዳሴዋን ደጋግሜ...
ገና ከደጅዋ እልፍ ሳልል፤ ደሞ ይምጣ የቁም ህልሜ?
ሌት በጥምቀቷ የነጣው፤ ነጋ፤ ደፈረሰ ደሜ።
ለሷ እንጂ ለኔ አልያዘልኝ፤ አዬ የስለት አታምጣ!
በውጣ ውረድ በጠበል፤ ባሣር ወዜ ቢገረጣ
ልክፍቷ እንደሁ አልለቀቀኝ፤ መሸ ደሞ አምባ ልውጣ!
ሎሬት ፀጋዬ /መድህን

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ