2013 ፌብሩዋሪ 17, እሑድ

የሁለት ግጥሞች ወግ ፤ ብቻዬን እና ብቻውን



ብቻዬን /ታገል ሰይፉ

-------
ሰዎች ርቀው ካጠገቤ-
ዙሪያዬን ከቦኝ ፀጥታ
በፀጥታው መሐል ስጓዝ-
ናፍቆቴን ውጬ በዝምታ. . .
ቅጠሎች ተንሾካሾኩ-
ገባኝ እኔም ሀሜታቸው
ከብቸኝነት በርሃ-
ብቻውን ቀረ ማለታቸው፡፡
ጥላዬም ይህን ሰማና
በዝምታ ተከተለኝ
ሁሉም ቢከዱህ እንኳን
እኔ አልከዳህም እያለኝ. . .
እባክህ ተወኝ ጥላዬ
አትሞግተኝ በሽንገላ
ማየቴ አይቀርም ከቆየሁ-
አንተም ስትከዳኝ እንደሌላ…
---------
ታገል ሰይፉ(የካቲት 3-1986)
,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,

ብቻውን / ወንድዬ አሊ
-------
ብን . . . እብስ
ብን . . . እብስ
ከጥላው ተጣልቶ … ከራስ ተሰራርቆ
ከራስ ጠረን ሸሽቶ … እስትንፋስን ርቆ
በመብረቋ ደቆ
ብን . . . እብስ
ብን . . . እብስ
ሌት ቀን . . . ደንብዞ
በ'ጣ ተክሏ መሮ - ሕመሟን ደንዝዞ
ማመን . . . መተማመን
ቅዠቷን . . . ደንግጦ
ቀጋ ጡቷን . . . መጦ
ብን . . . እብስ
ብን . . . እብስ
አለኋችሁ ላይል … አለሁ ባይም አጥቶ
ጠሪ ባያገኝም … እሱም ለወይ ታክቶ
በሰው ጫካ መሐል … ቀልብያው ሸፍቶ
የመሐል አጠገብ … እሩቅ ተሰውሮ
ባይተዋርነትን … ሰቀቀኗን ነፍሮ
ነጠላውን ቀዞ
በቅንዓት … ነብዞ
ሌላ ምንም አይደል
ታሽቶ - መታሸቱ
ብን . . . እብስ ማለቱ
ብቻው ብቻ … ሲቀር
ብቻ ሲቀር አይደል!? … በብቸኝነቱ!
------
ወንድዬ አሊ፣ ወፌ ቆመች መጽሐፍ