2014 ጁላይ 7, ሰኞ

"የሃብታም ልጅ " ፍለጋ

በኄኖክ ስጦታው

አብሮ አደጌ ነበር። አብረን ብናድግም ቅሉ፣ አብረን ግን አንድም ቀን ቁም ነገር ተጫውተን አናውቅም። እንደው ርግጫ ወደጨዋታ ከተጠጋጋም፣ ከተጫወትነው ትዝ የሚለኝ "ሹሌ" ብቻ ነው።

ዛሬ ይህ ሰው ያደኩበት መንደር "እግረኛ ትራፊክ" ሆኗል።

በየመንደሩ አያሌ እግረኛ ትራፊኮች አሉ። እንኴን አብሮ አደጋቸውን በመልክ የሚያውቁትን በፈለጣ የሚቀጡ።

ርግጥ ነው፤ የፈለጣ ቴክኒኮች "በስማ በለው" ከአንዱ ፈላጭ ወአሌላው ይተለፋሉ። ( እንደ ስነቃል በፅሑፍ አልሰፈሩም።)

የትውልድ መንደሬ አስቁሞ ፈላጭ ከየት መጣ ሳይባል ከች አለ። (መንገድ ዘጋብኝ ማለት ይቀላል መሰል!)

ፈገግታው ልዩ ነበር። (በናፍቆት የጦዘ ፈገግታ :D ) ፊቱ ላይ ያለው ፈገግታ… "ይሸጣል!" የሚል ማስታወቂያ ቢለጠፍበት የሸማቹን አጀብ አስቤ "አማተብኩ"።

ሰላምታ ተለዋውጠን፣ የፈገግታው ወላፈን በርዶ፣ እጅ ለእጅ መወዛወዛችን ጋብ ብሎ… ከዚህ ሁሉ በዋላ መንገድ ጀምረን ለጨዋታው አዝማች ፣ "ኑሮ እንዴት ነው?" ስለው… ፊቱ በመቅፅፈት ተፈጠፈጠ። (እደዚህ ዓይነት ተለዋዋጭ ፊት ማግኘት መታደል ነው¡)

"ምነው?" ብዬ ጠየቅኩት።

"ምን እዚህ አገር ላይ እየኖርክ ለብቻህ ለውጥ አታጣውም።…" አለና ለመጀመሪያ ጊዜ የምር የሚመስል ጨዋታ ያመጣ መሰለኝ። ቀጠለ:– "መቼስ ላንተ አልነግርህም፤ ዘመኑን ታውቀዋለህ፤ ካለው ተወለድ፤ ወይም ካለው ተጠጋ። ካልሆነ ግን በእንጀራ አባት እንደኔ ስትሰቃይ ትኖራለህ… " አለኝ።

(የሰበቡ ድምዳሜ ፈለጣ ነውና ዘለልኩት) ከሃብታም ቤተሰብ ተወልዶ ድህነቱን የሚያምን እርሱ ሃብታም እንደሆነ አምናለሁ።

የሃብት መለኪያው ባለን እና ፣ እንዳይኖረን ባረግነው እንጂ፣ በኖረን እና በእንዳይኖር ባረግነው ግብአት አይሰፈርም።

በመሰረቱ ሃብት ያከቸው ሃብታም ቢባል ቅሬታ የለኝም። "የሃብታም ልጅ" መባል ግን ከአድናቆትነቱ ይበልጥ ስድብነቱ ያመዝንብኛል። ያልሆነ፤ ግን ሆነዋል ከተባሉት የተወለደ በመወለድ ብቻ ያለው መመቻመች "የወራሽነት" መብት ነውና "እጩ ወራሽ" ቢባል ይመጥነዋል…


አብሯደጌ ቅፈላውን ገፋበት። "… አየህ፣ ሥራ የለም። ብራሞችም እኛ ችስታዎችን አያስጠጉንም።…"

የገንዘብ የማጣት ችግርን ማስታገሻ ስሞች የኅብረተሰብ ውስጣዊ ማንነት መገለጫ ከመሆን አይድኑም። አንድ ብር ዋጋ እንደዛሬ በአንድ ሳንቲም ሳይተካ በፊት እነ "ሺ ብሬ" ተወልደዋል። የብሩ ዋጋ እየወረደ ሲመጣ ደግሞ እነ "ሚሊዮን" ተወለዱ። አሞሌ ጨው ብር በነበረበት ዘመን የኖሩ ሰዎችን መጠሪያ ስም ብናጣራ "አሞሌ" እና "አሞሊት" ተብለው የሚጠሩ አይታጡም።
★ ★
አንድ የመጨረሻው የድህነት ወለል በታች ተነስቶ ወደ ታላቅ "ቅንጦት" የተሸጋገረ አባት፣ በ14 ዓመት ልጁ ይህን ጥያቄ ተጠየቀ:— "ድህነት ምንድነው?"

አባት መልሱን ወዲያው አልተናገረም
ድህነትን ሳያውቅ ለኖረው ልጁ በተግባር ሊያስተምረው አሰበ። እናም በጉብኝት ሰበብ ገጠር ወደሚኖሩት ዘመዶቹ ዘንድ ላከው። ልጁ ከሳምንት በኋላ ሲመለስ :—

"እንዴት ነበር ጉብኝት?" ሲል ጠየቀው።

"በጣም ደስ የሚል ጊዜ ነበር " አለ ልጁ።

"እና ምን ተገነዘብክ? " አባት ሌላ ጥያቄ አስከተለ።

"የላከኝ አገር የሚኖሩት ሰዎች እኛ ከምንኖረው የተለየ አኗኗር አላቸው። እኛ በግንብ በታጠረ ጠባብ ግቢ ውስጥ በብዙ ዘበኛ አገልጋዮች ተከበን እንኖራለን፤ እነርሱ ግን በነፃነትና ባልታጠረ ሰፊ ቦታ ላይ ይኖራሉ። አንዱ የሌላው ጠባቂ እንጂ፣ እንደኛ ዘበኛ አይቀጥሩም።

"እኛ ሁለት ውሾች አሉን፤ እነርሱ ግን ብዙ አላቸው። እኛ ሚጢጢ የዋና ገንዳ ስንቦራጨቅ፤ እነርሱ ግን ትልቅ ወንዝ ውስጥ ይዋኛሉ። እኛ ከገበያ የምንገዛቸውን አትክልቶች ፤ እነርሱ ግን ከጓሮ ይቀጥፋሉ። …"

"እና ድህነት ምን እንደሆነ አሁን ተመለሰልህ? " አለ አባት።

"በሚገባ ተመልሶልኛል። እኛ ምን ያህል ድሆች እንደሆንን አውቄያለሁ" አለ ልጁ።

★ ★

አብሮ አደጌ በቀላሉ እንደማይፋታኝ ገብቶኛል። የጀመረውን ሃሳብ ሳይጨርስ ወደሌላው የሚሻገርበት ፍጥነት ይደንቃል።

"… የምሬን ነው፤ አንዷን ልጥጥ ካልተጃለስኩ ከዚህ ሲዖል አልወጣም!" አለ።

"ወንድሜ፤ ገንዘብ አይቶ ከመጃለስ፣ ቁልቋል ታቅፎ ማደር ይቀላል።"
★ ★

አቋራጭ መንገድ ፍለጋ ረጅምና አስቸጋሪውን መንገድ መጓዝ መርጧል። ጥገኝነት የሕይወት መንገዱ ነው። ከሰዎች የሚፈልገው ብዙ ነው። ለሰዎች የሚሰጠው ግን ምንም።

እጅግ ሀብት ካላቸው ቤተሰብ የተወለደ አንድ ወዳጅ አለኝ። —‘የሃብታም ልጅ‘ ሲሉት ይቆጣል። "የሚያኮራው ሃብታም መሆን ነው።" ይላል። ዋናው ጥያቄ ይህ ነው:— ጥገኛ ሃብታም፣ ወይስ ጥገኛ ድሃ?

ሕይወት ሙሉ ናት። የጥገኝነት ተፅእኖ ግን የሌሎችን እንጂ የራሳችንን እንዳናይ ጋርዶናል። ጥገኛ ምሑር፣ ጥገኛ ነጋዴ፣ ጥገኛ ባል፣ ጥገኛ ሚስት፣ ጥገኛ ተማሪ፣ ጥገኛ ተከራይ፣ የጥገኛ ጥገኛ ተጠጊ · · ·

ጥገኝነትን የሙጥኝ ያሉ ግንዛቤዎች በንሮ ዘዬያችን ውስጥ ሰልጥነውብናል። የስብሰባ አዳራሾች "የኔም ሃሳብ እከሌ እንዳለው ነው—" በሚሉ ተሰብሳቢዎች ይጨናነቃሉ። የሊቃውንት ስም ካልጠሩ ከእውቀት መዝገብ የሚፋቁና የሚጎድሉ የሚመስላቸው "ምሁራን" ከስራቸው አያሌዎችን "ይቀርፃሉ"። መሪ ቢቃዥም ባይቃዥም፣ ለራሳቸው ያልገባቸውን ለማስፈፀም የሚታትሩ ትጉህ ሸምዳጅ "አስፈፃሚ" ጥገኞችም "ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው¡"።

አዎ ጥገኞች ነን። ስንጠላ የጥላቻ፣ ስንወድም የውዴታ ጥገኛ ነን። ስንወለድ የወላጅ፣ ስናረጅም የልጆች ጥገኛ ነን። የተቃራኒ ዓለም ሰዎችም ነን። ቅሪት የቋጠረ እየፈራ፣ ቅሪት አልባው የሚጀግንበት። ለውጥ አልባ ጥገኞችም ነን። ስንወጣ የመውረድ፣ ስንወረደድ የመውጣት ውትብትብ ለመቀበል ያልበቃን ጥገኛ ድሆች።

ድሃው ማነው? ሃብታሙስ?

ድህነት የገንዘብ ከሆነ በሰለጠኑት አገራት ተሰደው ያሉ ወገኖች የመጨረሻውን ድሃ የማይሰራውን ስራ ሰርተው ሲመጡ ሃብታም የምንላቸው ለምንድነው? ሃብታም ስለነበሩ? ሃብታም ስለሆኑ? ወይስ እኛ ከእነርሱ በታች ድሃ ስለሆንን?

በፍፁም፤ ድህነት ስታስቲክ እንጂ እውነታ አይደለም። ሃብታምም ሆነ ድሃ ለቁጥር አይመቹም። "ከሃብታም" ጋር የተመሳሰሉ ድሆች "ከበርቴ" ይሰኛሉ። "ከድሃ" ጋር የተማሰሉም "ከበርቴዎች" እንዲሁ "ምንዱባን" ይባላሉ። የቱ ነው ትክክል? ቆጣሪው ወይስ ተቆጣሪው?

በእድሜ ዘመኑ ከፍሎ በማይጨርሰው ብድር ተዘፍቆ ሃብታም ከተሰኘው አባት ለተወለደ ልጅ ሃብት ምንድነው? እድሜ ዘመኑን ድህነቱን አምኖ በጠኔ ከሚጠበስ ቤተሰብ ለተወለደ ልጅስ ድህነት ምኑ ነው?