2013 ኦክቶበር 30, ረቡዕ

የተዘጉ አንደበቶች ______(ኄኖክ ሥጦታው)

የተዘጉ አንደበቶች
______(ኄኖክ ሥጦታው)

1ኛው ቀን
ዓያት - ዓየችው
ዘጋት - ዘጋችው !
ቤቱ ገባ፤ ቤቷ ገባች
በሩን ዘጋ፤ በሯን ዘጋች!
መሸ ፤ ነጋ
2ኛው ቀን -
እሱም ወጣ፤ እሷም ወጣች
እሱም ዓያት፤ እሷም ዓየች
ኮራ...ኮራች፤
እንዳላያት፤ እንዳላየች
ሄደ...ሄደች፡፡

3ኛው ቀን-
4ኛው ቀን-
5ኛው ወር-
6ኛው ወር...
ለውጥ የለም፤ ለውጥ አለ፤
ምንም የለም፤ ምንም አለ!
በተዘጉ አንደበቶች፣
ሊግባቡበት የቀለለ
የቀየሱት መንገድ አለ፡፡
በዝምታ ሚግባቡበት...
ፈጥረው ነበር
አንድ ነገር
ለሌላ ሰው ’ማይነገር፡፡
_____________________

ኄኖክ ሥጦታው - "-ሞት" የግጥም መጽሐፍ

አርዝም አደንድን ______(ኄኖክ ሥጦታው)


አርዝም አደንድን
______(ኄኖክ ሥጦታው)

ስሜት ልጓ በጠሰ፤ አስማት ዋለ ለምንዝር
በአርዝም አደንድን ድግምት፣ አቅም ተሰዋ ለግትር፡፡
መሰዋቱ ባልከፋ፣ ለዚያችኛዋ (‹‹ቂንጥር››)
አስማት ስሜት ታቅፎ፣ ካሸነፈው ያስማት ቀመር
ወንድነቱን ክዷልና ቀድሞውንም ወንድ አልነበር፡፡
______________
23-08-2005.

ኄኖክ ሥጦታው - "-ሞት" የግጥም መጽሐፍ

የቆሻሻ ወደብ ______(ኄኖክ ሥጦታው)

የቆሻሻ ወደብ
______(ኄኖክ ሥጦታው)

የስልጣኔ ዝቅጥ መጣያ፣ የጥራጊያቸው ወደብ ነን፤
የጣሉትን የምንለቅም፣ ካልጣሉልን የምንለምን፤
ፈረስም ነን ለነዚሁ፣ እንዳሻቸው የሚያደርጉን፤
ካሻቸው የሚለጉሙ፣ ካሻቸውም የሚጋልቡን፤
ካሻቸው የሚጭኑ፤ ካሻቸውም የሚዋጉብን፡፡

የገደልም ማሚቶዎች ነን፤ የጮኹትን የምንደግም፤
በለኮሱት ስንቃጠል፤ በቃ ሲሉን የምንከስም!

በስማ በለው ተብትበውን፣በቁሳቸውእንዳጨቁን፣
ስንዳክር ዳናው ጠፍቶን፣ እስከ መቼ እንዘልቃለን!?

ሲጋልቡን ስንጋለብ፣ የጫኑንን ስንሸከም፤
የጣሉትን ስንለቅም፣ የሚሉትን ስንደግም!
እንደ አራስ ልጅ በሰው ጀርባ
እስከ መቼስ እንዘልቃለን!?
እስከ መቼስ እንከርማለን!?
______________
መስከረም 2005.

ኄኖክ ሥጦታው - "-ሞት" የግጥም መጽሐፍ