2013 ሴፕቴምበር 20, ዓርብ

አላዋቂ ሳሚ . . . .! በ-ኄኖክ ስጦታው



የዚህ ጽሑፍ መነሻ ጳጉሜ 3 ቀን 2005ዓ.ም በዋልታ ኢንፎርሜሽን ድረ ገጽ ላይ “ሥነ-ጽሑፍ እና ትምክህተኝነት” በሚል ርዕር፣ “ቢላል” በሚል ብዕር ስም (ኋላ ላይ ማንነቱን የሚገልፅ ፍንጭ በመስጠት ማንነቱን የደረስኩበት ጸሐፊ) አማካኝነት የቀረበ ጅምላ ጨራሽ ዳሰሳ ነው፡፡

ርግጡን ለመናገር “ሥነ-ጽሑፍ እና ትምክህተኝነት” በተሰኘው ርዕስ ሥር ያለውን ጭብጥ ለመረዳት ጽሑፉን ደጋግሜ አንብቤዋለሁ፡፡ በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ድረ-ገጽ ላይ መውጣቱ ትኩረቴን ባይስበው ኖሮ ተራ የስም ማጥፋት ድርጊት ነው ብዬ ባለፍኩት፡፡ እንዲህም የተቆርቋሪነት ስሜቴን ባላንጸባረቅኩ፡፡ ሆኖም እንዳሰብኩት አልሆነም፡፡ እናም ለውይይት ይሆን ዘንድ በር ከፈትኩ፡፡

ርግጥ ነው ጽሁፉ “ሥነ-ጽሑፍ እና ትምክህተኝነት” ርዕሱ ነው፡፡ አላማው እና ጭብጡ ግን ከሥነ-ጽሑፍም ባሻገር የጸሐፊውን ትምክህት በግልፅ የሚያሳይ፡፡ ሙሉ ሀተታውን በዚህ አድራሻ ያገኙታል፡- http://www.waltainfo.com/index.php/2011-09-07-11-57-06/10279-2013-09-08-20-31-21

ሀተታውን በማነብበት ሰዓት የተሰማኝን በመግለጽ ወደዋናው ጉዳይ ልግባ፡፡

ተጀመረ!

ከርዕሱ እንደምንረዳው “ሥነ-ጽሑፍ እና ትምክህተኝነት” ደፋር ርዕስ ነው፡፡ ምን ለማለት ነው እንዲህ አይነት ርዕስ የመረጠው?? በሚል ውስጣዊ ውዝግብ ፈጥሮ የመነበብን ጉልበት ይፈጥራል፡፡ “ሥነ-ጽሑፍ እንዴት ትምክህተኛ ይሆናል?? ትምክህተኛ እንዲሆንስ ማነው የሾመው?? ሥነ-ጽሑፍ የጽሑፍ ውበት ሆኖ ሳለስ እንዴት በትምክተኝነት ይፈረጃል??” በሚሉ መሰረታዊ ጥያቄዎች እየተናጥኩ አነበብኩት፡፡ በመጀመሪያው ንባቤ ርዕሱና ጭብጡ ተጣረሱብኝ፡፡


ጉድ እኮ ነው፡፡ “አንድ ሰው የተወሰኑ ጸሐፍትን ለመተንኮስ እንዴት ዙሪያ ጥምጥም ይጋልባል??” ብዬ ራሴን ጠየቅኩ፡፡ ለጥቆም፣ “ከተወሰኑ ጸሐፍት ባሻገር አገራዊ አጀንዳ ማንሳቱ ካልቀረ እንደምንስ ጭፍን ግንዛቤውን ልብ በሚደልቅ ርዕስ ይጀምራል??” የሚል አንፃራዊ ጥያቄ ወጥሮ ያዘኝ፡፡ ጉዳዩን ለመረዳት ለሶስተኛ ጊዜ አነበብኩት፡፡ ይህኔ ግን የተረዳሁት ይህን ነው፡፡ “እንዴት እራሱን “ዋልታ” ነኝ ምሎ የሰየመ የመረጃ ማዕከል እንዲህ ያለ ተልካሻ የስም ማጥፋት ዘመቻ በድረ-ገፁ ላይ ,ሊያስነብበን ፈለገ??” ወደሚል ጥያቄ ተሸጋገርኩ፡፡

መልስ ምት!!

የጽሑፉ ጭብጥ የማይነካካው ነገር የለም፡፡ ዓለም ስትፈጠር ጀምሮ የነበረውን የሥነ-ጽሑፍ ሂደት አሻሚ በሆነና በደፍናናው ሊነግረን ይሞክርና (መነሻውን አታውቅም ፣ አርፈህ ተቀመጥ እንዳንለው ነው መሰል¡) ነፃው ፕሬስ ፖለቲካዊ ተፅዕኖው ከአፍራሽ ፓርቲዎች ግፊት የመነጨ ነው ከማለት አንስቶ የግለሰቦችን ስም እየጠቀሰ “እከሌ ፀረ-ኢህአዴግ ነው፣ እከሌም ጨለምተኛ ነው ፣ እንቶኔ የቅንጅት ቅብርጥሶ ነው ፣ እከሌም የደርግ ወታደር ነበር . . .” የሚሉ ተልካሻ ሃሳቦችን አስደግፎ ከዓለም ዓቀፋዊ አጀንዳ ወደ አገራዊ አጀንዳ ፤ ከአገራዊ አጀንዳ ወደ ፖለቲካዊ አጀንዳ ፤ ከፖለቲካዊ አጀንዳ ወደ ግለ-ሰብዓዊ አጀንዳ፤ ከግለ-ሰብዓዊ አጀንዳ ወደ ግል ብሶት ይሸጋገርን እንዲያ ቀልባችንን የሳበውን ርዕስ የብሶት መወጫ ያደርገዋል፡፡

ከመጨረሻው ልጀምር!

ይህን ጭብጥ በ“የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ላይ የተቃጣ ጦር” ብዬ ሰይሜዋለሁ፡፡ የዚህ ጽሑፍ አጠናቃሪ፣ አቶ ሰለሞን ሽፈራው (ይቅርታ) አቶ “ቢላል” ፣ የደራሲያን ማህበሩ ያሉበትን መሰረታዊ ችግሮችን እና መፍትሔዎችን ከማመላከት ይልቅ ለርሳቸው የቀለላቸው፣ የማህበሩ አመራሮች እና አባላቶችን የፖለቲካ አቅዋም “በመናገር” በሌሎች ዘንድ ማሳጣት ነው፡፡

እዚህ ላይ እንዲሰመርበት የምፈልገው ነጥብ አለ፡፡ የዚህ መልስ ምት ጸሐፊ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር አይደለሁም፡፡ የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ አካል ግን ነኝ፡፡ እንደ ብዙ ገለልተኝ ጸሐፍት የኢትዮጵያን ደራሲያን ማኅበር እንቅስቃሴ ድክመት ግን ለባለሙያው ሊሰጠው ከሚችል ድጋፍ አንጻር እያነሳሁ ከሚተቹ ሰውች አንዱ እንደሆንኩ አረጋግጣለሁ፡፡ ታዲያ አቶ ሰለሞን (ይቅርታ) አቶ “ቢላል” በጻፉት ትችት ላይ ለምን ቅሬታዬን አሰማለሁ?? . . . ነገሩ ወዲህ ነው፡፡

በአንድ ሙያዊ ማኅበር የታቀፉ ሥራ አስፈጻሚዎችም ሆኑ አባላት የፖለቲካ አመለካከት የማኅበሩ ጉዳይ እንዳልሆነ አምናለሁ፡፡ እንዳልኩት አንድ ነገር ያስማማናል ብዬ አምናለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር እንደ ሙያ ማኅበርነቱ መሥራት ያለበትን እንዳልሠራ ርግጥ ነው፡፡ (ወዳኋላ ተመልሰን ከዚህ ቀደም በነበሩ አመራሮች የተሠሩትን ማተት የርዕሰ ጉዳዩን መስመር ያስታልና መጥቀሱ ፋይዳቢስ በመሆኑ አልፌዋለሁ፡፡)

የአቶ ቢላል ሃተታ በደራሲ ማህበሩ የሚስተዋለውን ከአቅም በታች ያለን አተገባበር በማስረጃ አስደግፎ በማቅረግ መፍትሔውን እንደማመላከት ፣ የአባላቱን የፖለቲካ አቅዋም ላይ በመዘበት የደራሲያንን ብቃት በአንቶ ፈንቶ የመንደር ወሬ ጭቃ መቀባቱን ግን እቃወማለሁ፡፡ ተቋውሜንም እንዲህ እቀጥላለሁ፡፡ ልብ በሉልኝ፡፡ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር አባል አይደሉም፡፡ አለመሆኔ ግን የአቶ ቢላል (ይቅርታ) የአቶ ሰለሞንን ጽሑፍ ከመቃወም አያግደኝም፡፡ እንድቃወም ያደረገኝ ምክንያትም ይሄው ሚዛን በማይደፋ ማስረጃ የተጻፈ ጽሑፍ ነው፡፡

“የሥነ-ጽሑፍ ትምክህተኝነት” በሚል ርዕስ የተጻፈው ይህ ሀተታ፣ ከመነሻው ጀምሮ የሚስተዋሉበት መሰረታዊ እርስ ራሳቸው የሚጣረሱ አሉባልታዎችን መሠረተ-ቢስነት ማጋለጥ ግድ ነውና!

ጥያቄ 1

(ከዚህ በታች ለጻፍከው የቀረበ)

------------------------

“….የሀገራችን ስነፅሁፍ ዛሬም ከመቼውም ጊዜ በላይ ለጥላቻ ፖለቲካ ማራመጃ እየተደረገ እንደሚገኝ ተጨባጭ ማስረጃዎችን በዋቢነት እያጣቀስኩኝ ልቀጥል፡፡ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በዚህ ረገድ እያበረከተ ያለውን አሉታዊ አስተዋፅኦ ላስቀድምና ከዚያም ወደየአሁኖቹ “ደፋር” የግል ፕሬስ ውጤቶች እመለሳለሁ፡፡
በተለይም ከ1990ዎቹ መጀመሪያ ወዲህ በኢትዮጵያችን የስነፅሁፍ ታሪክ ውስጥ ተወልደው በማደግ ላይ ከሚገኙት ወጣት ደራሲያን መካከል፣ እንደለጌታ ከበደ አንዱ ነው፡፡ በዚህ መሰረትም የአንጋፋው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ዋና ፀሐፊ ሆኖ ከተመረጠ ከስምንት ዐመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ እናም ይሄው ወጣት ደራሲያችን የሙያ፣ ማብሀሩ የሰጠውን ስልጣን በመተገን ስነፅሁፋችንን ጭፍን ጥላቻ ለተጠናወተው የፅንፈኛ ተቃዋሚዎች ድብቅ ዓላማ ማስፈፀሚያ ሊያደርገው የማይፈነቅለው የትምክህተኝነት ድንጋይ፣ የማይቆፍረው የጠባብነት ጉድጓድ፣ እንደሌለው በተደጋጋሚ መታዘቤን እነሆ ከዚህ እንደሚከተለው በተጨባጭ ምክንያታዊነት አስደግፌ አወጋችሁ ዘንድ እገደዳለሁ፡፡
ለወትሮው በተለያዩ የፈጠራ ፅሁፎቹ (አጫጭርና ወጥ የልቦለድ ድርሰቶቹ) የምናውቀው እንደለጌታ ከበደ “ፍትሕ” በሚል ርዕስ ይታተም ከነበረው የምፅዓት ቀንን ናፋቂ የግል ጋዜጣ ጀምሮ እስከአሁኑ “ፋክት” መፅሔት ድረስ የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጋሻ ጃግሬ እንደሆነ የዘለቀ ቋሚ የፀረ ኢህአዲግ ፅሁፍ አቅራቢ፣ ወይም “አምደኛ” ከመሆኑም ባሸገር፣ የደራሲያን ማህበር ዋና ፀሐፊነቱን ተተግኖ የሚፈፅመው ደባ ግን ከሁሉም የከፋና “ሀይ!” ሊባል የሚገባው አስነዋሪ ተግባር ሆኖ ነው ያገኘሁት፤ እኔ በግሌ፡፡
ለዚህ አባባሌ የተሻለ አብነት ሊሆነኝ የሚችለው ደግሞ፣ ህዳር 27 ቀን 2004 ዓ/ም “የዓባይ ዘመን” በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በብሔራዊ ቴያትር አዳራሽ አዘጋጅቶት የነበረው የኪነጥበብ መድረክ ነው፡፡
እንደእኔ እምነት ከሆነ በዚያ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴሩ ክቡር አቶ አሚን አብዱልቃድር በክብር እንግድነት ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ኪነጥበባዊ ዝግጅት ላይ፣ መድረክ መሪ የነበረው እንደለጌታ ከበደ ያሳየው እጅግ በጣም ቅጥያጣ ንቀት፣ የእርሱን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አመራር አካላትና እንዲሁም ከበስተጀርባቸው ሆነው “ጎሽ..! የሚላቸውን ነውጥ ናፋቂ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጭምር የከፋ ትዝብት ላይ የሚጥል ቅንነት ማጣት ይመስለኛል፡፡ …..”

---------------------------

እኔ ምለው . . . ማኅበሩ የሚታማው በጥላቻ ፖለቲካ አራማጅነት ሳይሆን የገዢውን መንግስት በመደገፍ እንደሆነ ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው፡፡ ታዲያ ይህን መንገር የአባላትን የፖለቲካ አቅዋም እንዴት ከማኅበሩ ጋር ማቆራኘት ተቻለህ??

ለመሆኑ፣ በዚህ ጥላቻ በሚዘራ አመለካከትህ ላይ ሕገ-መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ከአገራቸው ሳይሰደዱ፣ የክስ እና ውክቢያ ተፅዕኖን ተቋቁመው እየጻፉ ያሉትን ጋዜጠኞችን በደፍናናው ማበሻቀጥ ከስም ማጥፋት ወንጀል ተለይቶ የሚታይ ይመስልሃልን?? (ወይስ አንተም ሃሳብ የመግለጽ መብትህን ለዘለፋ እያዋልከው ነው??)

ኧረ ለመሆኑ፣ “ፀረ-ኢህአዲግ ናቸው” ማለት በአንተ መዝገበ-ቃላት ትርጓሜው ምን ይሆን?? የሥርዓት ብልሹነትን ነቅሶ ማውጣትና ድክመትን ማተት ኢ-ልማታዊ ሊያስብልስ እንዴት ይቻለዋል?? ልማታዊ ጸሐፊ መሆን ማለት እኮ የግድ መልካሙን ነገር ብቻ መልሶ መላልሶ ማተት አይደለም፡፡ የመናገር ነፃነት በማንቆለጳጰስ ላይ ብቻ ይገደብ ያለውስ ማነው??

“ምጽዓት ቀን ናፋቂ” ብለህ ያበሻቀጥካቸው ጋዜጠኞች እንደ ተስፋይቱ ምድር ኢትዮጵያም “ማር እና ወተት የሚፈልቅባት አገር ናት” ለምን አላሉም ብለህ ከሆነ ተሳስተሃል፡፡ እንኳን ከፊል ዲሞክራሲን ቆንጥራ በምታቀርበው አገራችን ቀርቶ የዲሞክራሲና መልካም አገዛዝ ማማ ላይ ተፈናጠናል በሚሉት ያደጉት አገራትም ብልሹ አሰራርን ተቃውመው የሚዘግቡ ጋዜጠኞች ይህ ስያሜ አልተሰጣቸውም፡፡

ጥያቄ 2
------------------------

“….ህዳር 27 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር “በራሱ ተነሳሽነት” እንዳዘጋጀው እያንዳንዱ የአመራር አካላት በነቂስ የተናገረለትን ያን የድበበቆሸ መድረከ በአጋፋሪነት እንዲመራ በዝግጅት ኮሚቴው መመረጡን አስቀድሞ የነገረኝ ዋና ፀሐፊው እንዳለ ጌታ ከበደ፣ የዶ/ር በድሉን ማንነት ለታዳሚው ያስተዋወቀበት የወገንተኝነት ስሜትና አኔ መጨረሻ ላይ ወደ መድረከ ወጥቼ “ተወራራሽ ሕልሞች” በሚል ርዕስ የፃፍኩትን የህዳሴ ዘመን ግጥሜን ሳነብ ከየት እንደመጣሁ እንኳን ሊናገር አለመፈለጉ ምን ያህል ቅስሜን እነደሰበረውም በዚሀ አጋጣሚ ልገልፅለት እወዳለሁ፡፡….”

----------

ጸሀፊው (አቶ ሰለሞን) ይቅርታ (ቢላል) . . . ስለ ኢትዮጵያ ደራሲያን ሲያትት . . . እራሱን የማኅበሩ አባል እንደሆነ ጠቅሶ እንደ ሙያ ማኅበር ያለበትን ድክመት ሳይጠቅስ፣ የፖለቲካ አቅዋም እንደ አጀንዳ ማንሳቱ ለምን አስፈለገ?? “እከሌ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ነው፣ እንቶኔ “ፍትህ” ላይ ይጽፋል፣ በድሉ ‹እውነት ማለት . . .› የሚለው ግጥሙ ጨለምተኛ ነው፣ አባይ ግድብን አስመልክቶ በተዘጋጀ መድረክ ላይ ልማት የሚያደናቅፍ ግጥም አነበበ፣ . . . እንዳለጌታ “. . . ወደ መድረከ ወጥቼ “ተወራራሽ ሕልሞች” በሚል ርዕስ የፃፍኩትን የህዳሴ ዘመን ግጥሜን ሳነብ ከየት እንደመጣሁ እንኳን ሊናገር አለመፈለጉ ምን ያህል ቅስሜን እነደሰበረውም በዚሀ አጋጣሚ ልገልፅለት እወዳለሁ፡፡” ማለትን ምን አመጣው??

የዚህ ሁሉ ሃተታ ፍፃሜ የጽሑፉን ጭብጥ የግል ቂም ከማስመሰል የዘለለ ፋይዳውስ ምንድነው??

እጅግ በሥራቸው አንቱ ያልናቸውን ጸሐፊያን ላይ ክብረ-ነክ በሆነ መንገድ ድንገት ተነስቶ መዘርጠጡ በራሱ ትምክህት አይደለምን??