2013 ጁን 15, ቅዳሜ

ቆቅ እና “ማሽሟቀቅ” . . . ከሰማሁት ያስታወስኩትን ያህል - - ኄኖክ ስጦታው



በ1993 መጨረሻ ይመስለኛል፡፡ በሩሲያ ሳይንስና ባህል ማዕከል ገጣሚና ጋዜጠኛ ነቢይ መኮንን የትምህርት ቤት ትዝታውን አንስቶ ተሞክሮውን ያካፈለበት ላይ ሲናገረው የሰማሁት ነው፡፡ አማርኛ አስተማሪያቸው “ቆቅ” በሚል ርዕስ ሁለት መስመር ግጥም እንዲጽፉ አዘው ነው ነገርየው፡፡ ከተማሪዎቹ መካከል አንዱ አማርኛ ቋንቋ ሁለተኛ ቋንቋ ኖሮ የጻፈው ግጥም ለመምህሩ ሊገባቸው አልቻለም፡፡

 እዚያ ማዶ አነዲት ቆቅ
አየኋትኝ ስታሽሟቅቅ፡፡

ተማሪውን አስነስተው “ማሽሟቀቅ” ምን ማለት እንደሆነ ይጠይቁታል፡፡ መልሱን ሰምተው ማርክ ሊሰጡ መሰለኝ፡፡ ተማሪውም እንዲህ ብሎ መለሰ፡-

“እኔ ለራሴ አማርኛ ለማወቅ እያሽሟቀቅኩ ነው”

ታዲያ የቃሉን ፍቺ በቅርቡ (ቅርቡ ጊዜ ያኔ ነው) እንደተረዳው ነቢይ መኮንን ለዛ ባለው አንደበቱ ተናግሮ ነበር፡-
“ገዢው ፓርቲ እያሽሟቀቀብን እንደነበረ የገባኝ አሁን ነው” ብሎ ታዳሚውን አስፈግጓል፡፡(በነገራችን ላይ ይህች የቆቅ “ግጥም” ከግዜያት በኋላ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ “የነገር ጥግ” አምድ ስር  ማንበቤን አስታውሳለሁ)


ነቢይ መኮንን ለታዳሚዎቹ አንድ የግጥም ርዕስ ሰጠ፡፡ “ትዝታ” በሚል ሁለት ስንኝ ግጥም ጻፉ ፤ አለ፡፡ በብርሃን ፍጥነት አንድ ሰው ጽፎ ሰጠው፡፡ አነበበልን፡-

ትዝታሽ ዘወትር ወደኔ እየመጣ
ስለሚያስቸግረኝ ፖሊስ እጠራለሁ፡፡

(አንታራም ግጥም ይሉሀል እንዲህ ነው፡፡)

2013 ጁን 10, ሰኞ

“ነወር”፣ “ነውረኛ”፣ “ነዋሪ” - ኄኖክ ስጦታው

“ነወር”
“ነውረኛ”
“ነዋሪ” 
-
-
-
-

“ነወረ” ማለት . . . “አነወረ፣ አስነወረ፣ አሳፈረ፣ ነውረኛን አደረገ፣ ወይም ተነወረ፣ በነውር ነገር ተከሰሰ” ይለዋል ከሳቴ ብርሃን የአማርኛ መዝገበ ቃላት ፤ በተሰማ ሀብተ ሚካኤል ግጽው የተዘጋጀው፡፡ 

“ነውረኛን” ማለትን ሲፈታው ደግሞ፡- “ነውርን የተመላ፣ ነውርን ከመስራት የማያርፍ(ተነወረ፣ ነውረኛ ሆነ) ” 

“ነዋሪ” ማነው? ካላችሁ . . መልሱ. . . አንድም በመንግስቱ ኅልፈት ጥፋት የሌለበት፣ ሳይለዋወጥ ፣ ጊዜ ሳይወስነው የሚኖር አምላክ ነው፡፡ ሌላም፣ በሕይወት ሥጋ የሚኖር፣ ከቦታው የማይላወስ…. ባለበት ጠንቶ የሚኖር ነው፡፡ ስለዚህም ነው መሰል፣ “ነወር” ስንባል ፣ በተለምዶ “በእግዜር” እንላለን፡፡ 

አሁን አሁን እየተስተዋሉ ያሉት እውነታዎች ስንገመግም አንድ ትልቅ ቁም ነገር ትርጉም አልባ እየሆነ ለመሆኑ ማስረጃ መጥቀስ የማያሻው ጉዳይ ነው፡፡ በማሕበረሰቡ ድንጋጌ (ይህ ድንጋጌ በነዋሪዎች ቅቡልነት /ተለምዷዊ ስምምነት/ አቋም የያዘ ነጥብ ፤ በአብላጫው ተቀባይነት ድምፅ የፀደቀ፡፡) ? 

“ነወር” የሚለውን ቃል ስንበረብረው “ኖር” ከሚለው ቃል በተጨማሪ “ነውር” የሚል ተጻራሪ ፍቺ አቅፏል፡፡ /እንግዲህ እኔ እንደተረዳሁት ነው ትንታኔው/ . . . አንድም ለክብር አንድም ለተግሳጽ የምንጠቀምበት ይህ ባህል ከመጥፋት እንታደገው!

ኄኖክ ስጦታው