2013 ሜይ 3, ዓርብ

ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት /ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን/

ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት 
/ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን/
------------
አዬ፣ ምነው እመ ብርሃን? ኢትዮጵያን ጨከንሽባት?
ምነው ቀኝሽን ረሳሻት?
እስከመቼ ድረስ እንዲህ፣ መቀነትሽን ታጠብቂባት?
ልቦናሽን ታዞሪባት?
ፈተናዋን፣ ሰቀቀኗን፣ ጣሯን ይበቃል ሳትያት?
አላንቺእኮ ማንም የላት….
አውሮጳ እንዲሁ ትናጋዋን፣ በፋሽስታዊ ነቀርሳ
ታርሳ፣ ተምሳ፣ በስብሳ
ሂትለራዊ እባጭ ጫንቃዋን፣ እንደኮረብታ ተጭኗት
ቀና ብላ እውነት እንዳታይ፣ አንገቷን ቁልቁል ጠምዝዟት
ነፍሷን ድጦ ያስበረከካት
ሥልጡን፣ ብኩን፣ መፃጉዕ ናት፤ ….
እና ፈርቼ እንዳልባክን፣ ሲርቀኝ የኃይልሽ ውጋገን
አንቺ ካጠገቤ አትራቂ፣ በርታ በይኝ እመ ብርሃን
ቃል ኪዳኔን እንዳልረሳት፣ እንዳልዘነጋት ኢትዮጵያን፡፡
አዎን፣ ብቻዬን ነኝ ፈራሁ
እሸሸግበት ጥግ አጣሁ
እምፀናበት ልብ አጣሁ
እማማ ኢትዮጵያን መንፈሴ፣ ተፈትቶ እንዳይከዳት ሠጋሁ …
አዋጅ፣ የምሥራች ብዬ፣ የትብት ምግቤን ገድፌ
ከእናቴ ማኅፀን አርፌ
ከአፈርዋ አጥንቴን ቀፍፌ
ደሜን ከደሟ አጠንፍፌ
ከወዟ ወዜን ቀፍፌ
በሕፃ እግሬ ድሄባት፣ በህልም አክናፌ ከንፌ
እረኝነቴን በሰብሏ፣ በምድሯ ላብ አሳልፌ
ከጫጩት እና ከጥጃ፣ ከግልገል ጋር ተቃቅፌ፤
በጋው የእረኛ አደባባይ፣ ክረምት እንደወንዙ ፍሳሽ
በገጠር የደመና ዳስ፣ በገደል ሸለቆ አዳራሽ
ከቆቅ እና ከሚዳቋ፣ ከዥግራ ጠረን ስተሸሽ
በወንዝ አፋፍ ሐረግ ዝላይ፣ መወርወር መንጠልጠል ጢሎሽ
ከፍልፈል ጋር ሩጫ ስገጥም፣ ከቀበሮ ድብብቆሽ
ከናዳ ጫፍ ሣር አጨዳ፣ ለግት ላሜ ትንሽ ግጦሽ
ለጥጃዬ የሌት ግርዶሽ 
ለጥማድ በሬዎች ራት፣ ለማታቸው ትንሽ ድርቆሽ
ለግልገሌ ካውሬ ከለል
እማሳው ሥር ጎጆ መትከል
ለፀሐይ የሾላ ጠለል፣ ለዝናብ የገሳ ጠለል
ውሎ የንብ ቀፎ ማሰስ፣ ያበባ እምቡጥ ሲፈነዳ
የግጦሽ ሣር ሲለመልም፣ ሲሰማሩ ሰደድ ሜዳ
አዝመራው ጣል ከንበል ሲል፣ ከብቱ ለሆራ ሲነዳ
ፈረስ ግልቢያ ስሸመጥጥ፣ ከወፎች ዜማ ስቀዳ
ልቤ በንፋስ ተንሳፎ፣ በዋሽንት ዋይታ ሲከዳ …..
ያቺን ነው ኢትዮጵያ የምላት
እመ ብርሃን እረሳሻት?