2013 ፌብሩዋሪ 24, እሑድ

እንዳይነግርህ አንዳች እውነት ! - ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን


እንዳይነግርህ አንዳች እውነት ! - ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን

ደንስ ጎበዝ ! ደንስ ጀግና
ክራቫትህን አውልቅና
ሃሳብህን ልቀቀውና
ኮትክን ሸሚዝክን ጣልና
ርገጥ ፣ ጨፍር ፣ ደንስ ጀግና !

ያን የሙዚቃህን ናዳ ፣ የኮንትራባሱን መብረቅ
ልቀቀውና ይድብለቅለቅ
ምድር በሆይታ ይጥለቅለቅ !
ምንም-ምንም እንዳታስብ ፣ ሁሉን-ሁሉን እንድትረሳ
ደንስ ! ካካታው ይነሳ
ጨፍር ፣ ወለሉ እስኪበሳ ....

ሃይ-ሃይ ! ዋይ ! ሃይ-ሃይ ! በልበት
የጃዝ ፋንፋር አንኳኳበት
ራስክን እንዳታስብበት ፤
ሆ ! በል እሪ ! በል ምታበት
ፎክርበት ፣ አቅራራበት
አናፋበት ፣ ሸልልበት
የሲቃ ሳቅ አስካካበት
ሆያ-ሆዬ ! በል ጩኽበት
ኡኡታህ መንኮራኩርክን ፣ እስኪያሰጥመው አጓራበት
ጭንቅላትክን ግዘፍበት ፣ ውቀጥበት ፣ ውገርበት ፣ ....
ዝግ ብሎማ ያሰበ እንደሁ ፣ ይነግርሃል አንዳች እውነት !
-----------
ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን