2012 ኖቬምበር 16, ዓርብ

ወና ልብ; የትዕግስት ዓለምነህ ግጥም


ወና ልብ
ከልቧ ሜዳ ላይ፤
ፀሐይ ወጥታ ብታይ፤
ባልታጠረ ግቢ፣ ባላስከበረችው፤
ቅጥር በሌለው ደጅ፣ ወና በተወችው፤
ውሃ እንዲያነሳላት፣ ቢከረክር ወዳ፤
ስንዴዋን አስጥታ፣ ወደ መንደር ሄዳ፤
ቤቷ ላይጨስበት፣ ላትጐልት ጉልቻ፤
ንፍሮም ላትቀቅል፣ ላትጋግር እንጐቻ፤
"እሽ..." ባልተባሉ፣ ዶሮዎች ተለቅሞ፤
አጋች በሌላቸው፣ እሪያዎች ተቅሞ፤
‘ባፋሽ ባጐንባሹ‘፣ እንዳልነበር ወድሞ፤

በጠበቃት ስጡ፣ ሰርክ ስትገናኝ፤
ከመጅ ከማሰሮ፣ በወግ ሳትሰናኝ፤
በዛለ ጉልበቷ፣ ብቻዋን አራግፋ፤
ከነግሳንግሱ፣ ዳውጃዋን አጥፋ፤
ቀኗ ሊመሽ ሲድህ፣ ስትገባ መጀቷ፤
ቆፈኑ ተሰማው የተራበ አንጀቷ፡፡

/ትዕግስት ዓለምነህ/
ጥቅምት 3 ቀን 2005 ዓ.ም.

እኔ’ና’ኔ


ይኼ ልቤ . . . አልታወቀ - ሔርሜላ ትጽፋለች!!


ይኼ ልቤ . . . አልታወቀ
መቼ አምልጦ እንደመጣ
መቼስ አመል እንዳወጣ
ቤትህ ደርሶ - ደጅ አንኳኩቶ
ሳይታሰብ - አፀድህን ዘልቆ ገብቶ
ሳይጠራ - ከእልፍኝህ ተሰይሞ
ሳይጋበዝ - ከማዕድህ ታድሞ
ሳይታይ - አብሮህ ከዋለ ካደረ
እኔን ትቶ ካንተ መኖር ከጀመረ
ሰ - ነ - በ - ተ
ግና . . . ተግባር እንደል'ም አልቀለለ
እግሬ ልቤን መች ተከተለ
ከደሳሳ ጎጆዬ በራፍ ቆሜ (በሙሉ ዓይኔ እንኳ ሳልደፍር)
የኮራ አፀድህን ሳይ አግድሜ
ዓይኖቼ ሊያዩህ እንደናፈቁ
ጣቶችህ ከእጆቼ እንደ'ልም እንደራቁ
ምን አለብህ . . . በኮራ የንጉስ ርምጃህ
በመንደሩ ተንጎማልለህ
የኔ እግር ብርክ ሳይታይህ
እንደዋዛ ታልፈኛለህ . . .
ባለሹመት አጀበ ብዙ
ገደብ የለሽ ዓለም ደርዙ
ቢያነቅፍህ 'ልነጠፍ' ባይ የማታጣ
መካችህ ብዙ ቢያጋጥምህ የሚቃጣ
እና ለምን . . . እንዴት ተብሎ
ዓይንህ ወደኔ 'ሚያይ አሽቆልቁሎ
ቊንዳላህ ቢፈተሸ - ቢመረመር ቆዳህ
የቆነጃጅት ቃል - ድሪ ጌጣጌጥህ
ዓይናቸው መዋያህ - ልባቸው ማደሪያህ
ታዲያ ማን ከአጀቡ ነጥሎ
ከዙሪያህ የዓይን አዋጁን አግልሎ
ያመላክትህ ክሳይ መልኬን
ባይንህ ያግባ ልጥፍ ዳሴን?
የኔን ዓለም ሞልተህ - መውጣትህ መንጋቱ
ሲሆንልኝ ኖረ - መግባትህ መምሸቱ
ባታስተውለኝም በዓለምህ ባልታይ
ከቤቴም ባይሞላ አዱኛ ወ ሲሳይ
ይህንን አውቃለሁ . . .
ንጉስ ከእረኚት ጋር - በፍቅር ወደቀ
መደምደሚያው ሆና - ሌላ ውበት ናቀ
ስለዚህ . . . እንዲህ ነው ጸሎቴ
ባጠገቤ ስታልፍ አንድ ናት መሻቴ
እንቅፋት በመታህ - በጣለህ ከእርሻዬ
ክፉኛ አንሸራቶህ - ውደቅ ከማሳዬ
ላንዲት ደቂቃ እንኳ - መኖሬን እንድታውቅ
ቁስልህን ለማከም - ኖራለሁ ስናፍቅ
June 2011


Hermy Writes