2012 ኦክቶበር 1, ሰኞ

ሞክሼ የአማርኛ ፊደላት እና የባለሙያዎች ማብራሪያ ክፍል ሁለት


ሞክሼ የአማርኛ ፊደላት

እና

የባለሙያዎች ማብራሪያ

ክፍል ሁለት




የሄኖክ ስብስብ(henoksitotaw65@gmail.com)


ታህሳስ 2005ዓ.ም

ውድ አንባቢዎች፤ ከዚህ በታች የምታነቡት ሀሳብ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ላይ የተነበቡ ሲሆን ምንጫቸውም ከየመጣጥፎቹ ግርጌ ይገኛል፡፡ ለዚህም ነው “ስብስብ” በሚል ለመግለፅ የተገደድኩት፡፡ በስብስብ መጣጥፎቹ ላይ የጨመርኩት አንዳች ነገር የለም፤ ምክንያቱም አላማዬ በሞክሼ ፊደላት እና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ ለመበየን ሳይሆን፣ እንደኔው ግራ ለተጋቡት ማጋራት ነውና፡፡


-5-

በዲ/ን ኅሩይ ባየ

   . . .ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው ዐበይት ሀብቶቿ ውስጥ አንዱ የራሷ የሆነ ፊደልና ቋንቋ እየተጠቀመች ለትውልድ ስታስተምር መኖሯ ነው፡፡ ለዚህም የፊደል፣ የቋንቋ ዕድገትና ሥልጣኔ ከፍተኛውን ድርሻ የምትይዘውና በር ከፋቿ የኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ዛሬም እንደ ጥንቱ የሆሄያቱ ታሪክ እንዳይረሳ መልክአቸው እንዳይጠፉ ለትውልዱ ታስተምራለች፡፡ ስለሆነም በዘንድሮው የመስቀል በዓል በመስቀል ዐደባባይ አራቱ ሆሄያት እንዳይረሱ ትኩረት እንደሚያሻቸው ጥሪ ቀርቧል፡፡

ሆሄ የሚለውን ቃል ፊደል ተብሎ ሲነገር እንሰማለን፤ በጽሑፍም እናነባለን፡፡ ፊደልን ፈደለ ጻፈ ካለው የግእዝ ግስ አውጥተን ጽሑፍ የሚለውን ትርጉም እናገኛለን፡፡ በሌላ አተረጓጐም ፊደል የሚለው ግስ ጠብቆ ሲነበብ ፈጠረ የሚለውን ትርጉም ያስገኛል፡፡ ፊደል ፈጣሪ /መፍጠሪያ/ መባሉም ቃላትን ስለሚያስገኝ ነው፡፡ አባቶቻችን “ዘእንበለ ፊደል ኢይትነገር ወንጌል.. ያለፊደል ወንጌል አትተረጐምም” ማለታቸው ለመጻፍም ሆነ ለማንበብ፤ ለመተርጐምም ሆነ ለማመስጠር ፊደላት ጉልሕ ድርሻ እንዳላቸው ሲያመለክቱ ነው፡፡

2012 ሴፕቴምበር 30, እሑድ

ሞክሼ የአማርኛ ፊደላት እና የባለሙያዎች ማብራሪያ ክፍል አንድ


ሞክሼ የአማርኛ ፊደላት
እና
የባለሙያዎች ማብራሪያ

ክፍል አንድ

የሄኖክ ስብስብ
ታህሳስ 2005ዓ.ም
{PDF}
ውድ አንባቢዎች፤ ከዚህ በታች የምታነቡት ሀሳብ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ላይ የተነበቡ ሲሆን ምንጫቸውም ከየመጣጥፎቹ ግርጌ ይገኛል፡፡ ለዚህም ነው “ስብስብ” በሚል ለመግለፅ የተገደድኩት፡፡ በስብስብ መጣጥፎቹ ላይ የጨመርኩት አንዳች ነገር የለም፤ ምክንያቱም አላማዬ በሞክሼ ፊደላት እና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ ለመበየን ሳይሆን፣ እንደኔው ግራ ለተጋቡት ማጋራት ነውና፡፡
-1-
የፊደል ዘር ይጠበቅ ባህሉም ይከበር
በፊታውራሪ አበበ ሥዩም ደስታ
በፊደሎቻችን ላይ ሦስት ሀ - ሐ - ኀ፣ ሁለት አ - ዐ -፣ ሁለት ሠ - ሰ ሁለት፣ ጸ - ፀ አሉ፡፡ እነዚህ ፊደሎች የራሳቸው የሆነ የስም አጠራርም አላቸው፤ ሀሌታው ሀ፣ ሐመሩ ሐ፣ ብዙኃን ኀ፣ ንጉሡ ሠ፣ እሳቱ ሰ፣ ጸሎት ጸ፣ ፀሐዩ ፀ ይባላሉ፡፡ በጽሑፍ የሚገቡበትን ተገቢ (ተስማሚ) ቦታም አላቸው፡፡ ለምሳሌ በሁለት ፊደሎች መጠቀም ይቻላል፡፡ ሀገር አገር ይህ ትክክለኛ አጻጻፍ ሲሆን፤ ነገር ግን ከዚህ ውጪ ሐገር፣ ኀገር ብሎ መጻፍ ግን ስሕተት ይሆናል፤ የሚከተሉትን ደግሞ እንመልከት፤

ሕገ መንግሥት፣ ሕገ ወጥ፣ ሕዝብ፣ ሕብረት፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ወዘተ. የመሳሰሉት አጻጻፋቸው ትክክል ነው፡፡ ከዚህ ልማዳዊ አሠራር ውጪ ህገ መንግሥት፤ ህገወጥ፤ ህዝብ፤ ህብረት፤ አቃቤ ህግ ስሕተታዊ አጻጻፍ ይሆናል፤ ሌላ ማስረጃ ቢፈለግ፤ ኃይለሥላሴ የሚለው ስም ሦስት የተለያዩ ፊደሎች ይዟል፡፡ የመጀመርያው ፊደል ብዙኀን - ኃ - ሲሆን፣ ከንጉሡ -ሥ- ሳድስ፣ ከእሳቱ -ስ- ሃምስን በመጻፍ እንዲካተት ተደርጓል፡፡ ሀይለ ስላሴ ብሎ ቢጻፍ ግን የፊደሎቻችን የአጻጻፍ ሥርዓት ማፋለስ ይሆናል፤ በአቦ ሰጡኝ ፊደሎቻችን አለቦታቸው መግባትም፣ መጻፍም የለባቸውም፡፡

በዓፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በማስታወቂያ ሚኒስቴር ረዳት ሚኒስትር የነበሩት የተከበሩ ብላታ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ የቅድሚያ ዓይነተኛ ሥራቸው የፊደሎች ዘሮች አለቦታቸው እንዳይጻፉ መጠበቅ ነበር፤ በዚያን ወቅት ተማሪ ሁኜ አልፎ አልፎ በጋዜጣ እንዲወጣልኝ አንድ አንድ ሐሳብ በማመንጨት እጽፍ ስለነበር ብዙ ጊዜ አርመውኛል፡፡

ከእሳቸው በተማርኩት ትምህርትና ባገኘሁት ልምድ አእምሮዬን አሻሽያለሁ፡፡ በቀድሞው የንጉሠ ነገሥቱ ዘመነ ሥርዓት የክፍል ሹም የመጀመርያ ሹመት ሆኖ ወደ ላይ እንደሚከተለው ይዘልቃል፡፡ ዲሬክተር ዋና ዲሬክተር፤ ረዳት ሚኒስትር ምክትል ሚኒስትር፣ ሚኒስትር ዲ-ኤታ፤ ሚኒስትር፡፡ ከምክትል ሚኒስትር ወደ ላይ ያሉት እስከ ሚኒስትር ማዕረግ የደረሱት ክቡር ይባላሉ፡፡ ከዚህ በታች ያሉትን ግን ክቡር አይባሉም፡፡ በተመሳሳይ ያሉትን ማለት ኮሚሽነሮች፤ ሌ/ጀኔራሎች፣ አምባሳደሮች ክቡር ይባላሉ፡፡ ሚኒስትሮች የነበሩ በዳሬክተርና በሥራ አስኪያጅነት ሥራ ቢመደቡ እንኳን የቀድሞውን የሚኒስትር ማዕረጋቸውና ክብራቸው አይቀነስባቸውም፡፡ ክቡር መባል አለባቸው፡፡ ሥርዓት ነውና፡፡ ይህንኑ መለመድ ይገባዋል፤ በወታደሩ ሹመት አሰጣጥ ግን ያለው ሥርዓት የተጠበቀ ስለሆነ መልካም ነው እላለሁ፡፡ ከዚሁ ሌላ የምለው አለኝ፡፡ ባሁኑ በኢሕአዴግ መንግሥት ዘመን አምባሳደር ነዋሪ የማዕረግ መጠሪያ ስም ሆኖአል፡፡ አንድ አምባሳደር የዲፕሎማሲውን ሥራ አቁሞ ሲዛወር ልክ በሥራው እንዳለ ተቆጥሮ “አምባሳደር” እየተባለ መጠራት የለበትም፡፡

ለምሳሌ በዓፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት አምባሳደርነት ተሹመው የነበሩት ክቡር አቶ ጋሻው ዘለቀ፣ ክቡር አቶ ዘነበ ኃይለ፣ ክቡር ልጅ መንበረ ያየህ ይራድ፤ ክቡር ፊታውራሪ መሐመድ ሲራጅ ብዙ ዘመን በአምባሳደርነት ሲሠሩ ቆይተው ተልእኮዋቸውን ፈጽመው ወደ አገራቸው ሲመለሱ አምባሳደር የሚል ቀርቶ በቀድሞ ስማቸው አቶ ተብለው ነበር የሚጠሩት፤ ይህንኑ ጠይቆ ለማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ፊታውራሪ የነበሩትም፤ ፊታውራሪ ተብለው ይጠራሉ፡፡ ዘላቂ ሆኖ ከሰው ጋር ቅጽል የማዕረግ ስም ሆኖ የሚያገለግል ነው፡፡ በራሴ ምሳሌ ልውሰድ፤ ከግርማዊ ጃንሆይ በአዋጅ የተሰጠኝ የማዕረግ ስም ፊታውራሪ ነው፤ በዚህ ምድራዊው ዓለም እስካለሁ ድረስ የምጠራበት ሲሆን፣ ከሞትኩም በኋላ እጠራበታለሁ፡፡ እንዲሁም በንጉሠ ነገሥቱ መልካም ፈቃድ የሚሰጠው የሥልጣንና ማዕረግ ተዋረድ ባላምባራስ፣ ግራዝማች፣ ቀኛዝማች ፊታውራሪ፣ ደጀዝማች፣ ቢትወደድ፣ ራስ ቢትወደድ፣ ልዑል ራስ፣ አልጋ ወራሽ፣ ንጉሥ ንጉሠ ነገሥት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ብላታ፣ ብላቴን ጌታ፣ ፀሐፊ ትዕዛዝ፣ ሊቀ መኳስ በሕይወት ሳሉ ይጠሩበታል፡፡ ከሞቱም በኋላ ስማቸውና ታሪካቸው በተነሣ ቁጥር ከመቃብር በላይ ሆኖ በማዕረጉ ስም ይጠሩበታል፡፡